ሉቃስ 14:1-24

ሉቃስ 14:1-24 NASV

አንድ ሰንበት ቀን፣ ኢየሱስ ምግብ ሊበላ ከፈሪሳውያን አለቆች አንዱ ወደ ነበረ ሰው ቤት በገባ ጊዜ፣ ሰዎች በዐይን ይከታተሉት ነበር። በዚያም በአካል ዕብጠት የሚሠቃይ አንድ ሰው ከፊት ለፊቱ ነበር። ኢየሱስም ሕግ ዐዋቂዎችንና ፈሪሳውያንን፣ “በሰንበት ቀን ሕመምተኞችን መፈወስ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም?” ሲል ጠየቃቸው፤ እነርሱ ግን ዝም አሉ። እርሱም ሰውየውን ይዞ ፈወሰውና አሰናበተው። ደግሞም፣ “ከእናንተ አንዱ፣ ልጁ ወይም በሬው በሰንበት ቀን ጕድጓድ ቢገባበት ፈጥኖ የማያወጣው ማን ነው?” አላቸው። እነርሱም ለዚህ አንዳች መልስ ሊያገኙ አልቻሉም። ኢየሱስ ተጋባዦቹ የክብር ስፍራ ሲመርጡ ተመልክቶ፣ እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ለእነርሱ ነገራቸው፤ “አንድ ሰው ሰርግ ቢጠራህ፣ በክብር ስፍራ አትቀመጥ፤ በክብር ከአንተ የሚበልጥ ሰው ተጠርቶ ከሆነ፣ ሁለታችሁንም የጋበዘው መጥቶ፣ ስፍራውን ‘ለዚህ ሰው ልቀቅለት’ ይልሃል፤ አንተም እያፈርህ ወደ ዝቅተኛው ስፍራ ትሄዳለህ። ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ ዝቅተኛውን ስፍራ አይተህ ተቀመጥ፤ ጋባዥህም ሲመጣ፣ ‘ወዳጄ ሆይ፤ ወደ ላይ ከፍ በል’ ይልሃል፤ አንተም በዚያ ጊዜ ዐብረውህ በማእድ በተቀመጡ ሰዎች ሁሉ ፊት ትከበራለህ። ምክንያቱም ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ራሱንም ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ከፍ ይላል።” ኢየሱስም የጋበዘውን ሰው ደግሞ እንዲህ አለው፤ “የምሳ ወይም የእራት ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ፣ በዐጸፋው እንዳይጋብዙህና ብድራትን እንዳይመልሱልህ፣ ወዳጆችህን ወይም ወንድሞችህን ወይም ዘመዶችህን ወይም ከበርቴ ጎረቤቶችህን አትጋብዝ። ነገር ግን ግብዣ ባዘጋጀህ ጊዜ ድኾችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ሽባዎችንና ዐይነ ስውሮችን ጥራ፤ ትባረካለህም። እነዚህ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ፣ በጻድቃንም ትንሣኤ ብድራትህ ይመለስልሃል።” ከኢየሱስ ጋራ በማእድ ከተቀመጡት መካከል አንዱ ይህን ሰምቶ “በእግዚአብሔር መንግሥት ቀርቦ ከማእድ የሚበላ ምስጉን ነው” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንድ ሰው ትልቅ ግብዣ አዘጋጅቶ ብዙ ሰው ጠራ፤ የግብዣውም ሰዓት በደረሰ ጊዜ የተጋበዙትን እንግዶች፣ ‘እነሆ፤ ሁሉም ነገር ተዘጋጅቷልና ኑ’ ብሎ እንዲጠራ ባሪያውን ላከባቸው። “ነገር ግን ሁሉም የየራሳቸውን ምክንያት ይፈጥሩ ጀመር፤ አንደኛው፣ ‘ገና አሁን መሬት ስለ ገዛሁ ሄጄ ማየት አለብኝ፤ እባክህ፣ ይቅርታ አድርግልኝ’ አለው። “ሌላውም፣ ‘ዐምስት ጥማድ በሬዎች ገዝቻለሁ፤ እነርሱን ልፈትናቸው ስለ ሆነ እባክህ ይቅርታ አድርግልኝ’ አለ። “ሌላው ደግሞ፣ ‘ገና ሙሽራ ስለ ሆንሁ ልመጣ አልችልም’ አለ። “ባሪያውም ተመልሶ መጥቶ ይህንኑ ለጌታው ነገረው። በዚህ ጊዜ የቤቱ ጌታ ተቈጥቶ አገልጋዩን፣ ‘ቶሎ ብለህ ወደ ከተማው አውራ ጐዳናዎችና መተላለፊያ መንገዶች ውጣ፤ ድኾችንና አካለ ስንኩሎችን፣ ዐይነ ስውሮችንና ዐንካሶችን ወደዚህ አስገባቸው’ አለው። “ባሪያውም፣ ‘ጌታዬ፤ ያዘዝኸው ሁሉ ተፈጽሟል፤ ገና አሁንም ቦታ አለ’ አለው። “ጌታውም ባሪያውን፣ ‘ወደ ጐዳናዎች እና በዐጥሮች መካከል ወዳሉ መንገዶች ውጣ፤ ቤቴም እንዲሞላ ያገኘኸውን ሁሉ በግድ አምጥተህ አስገባ፤ እላችኋለሁና ከተጋበዙት ከእነዚያ ሰዎች መካከል አንድ ሰው እንኳ ግብዣዬን አይቀምስም አለው።’ ”