የሉቃስ ወንጌል 13:31-35

የሉቃስ ወንጌል 13:31-35 አማ05

በዚያን ጊዜ አንዳንድ ፈሪሳውያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “ሄሮድስ ሊገድልህ ይፈልጋልና ከዚህ ወጥተህ ሂድ” አሉት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ሄዳችሁ ለዚያ ቀበሮ፦ ‘ዛሬና ነገ አጋንንትን አስወጣለሁ፤ በሽተኞችን እፈውሳለሁ፤ በሦስተኛው ቀንም ሥራዬን እጨርሳለሁ’ ይላል በሉት። ይሁን እንጂ ዛሬና ነገ ከነገ ወዲያም መንገዴን ወደ ኢየሩሳሌም መቀጠል አለብኝ፤ ነቢይ ከኢየሩሳሌም በቀር በሌላ ቦታ መሞት አይገባውም። “ኢየሩሳሌም! ኢየሩሳሌም ሆይ! አንቺ ነቢያትን የምትገድዪ፥ ወደ አንቺ የተላኩትንም መልእክተኞች በድንጋይ የምትወግሪ፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ ሥር እንደምትሰበስብ፥ እኔም ስንት ጊዜ ልጆችሽን መሰብሰብ ፈለግኹ! አንቺና ሕዝብሽ ግን እምቢ አላችሁ። ስለዚህ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀራል፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ ‘በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው’ እስክትሉ ድረስ ከቶ አታዩኝም።”