የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 11

11
ስለ ጸሎት
(ማቴ. 6፥9-137፥7-11)
1አንድ ቀን ኢየሱስ በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፤ ጸሎቱንም ባበቃ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፥ “ጌታ ሆይ! ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት እንዳስተማራቸው፥ አንተም እኛን መጸለይ አስተምረን!” አለው።
2ኢየሱስም “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ አላቸው፤
‘[በሰማይ የምትኖር] አባታችን ሆይ!
ስምህ ይቀደስ!
መንግሥትህ ትምጣ!
3የዕለት እንጀራችንን በየቀኑ ስጠን!
4እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፥
በደላችንን ይቅር በልልን፤
ወደ ፈተናም አታግባን’ [ከክፉ አድነን እንጂ።]”
5ቀጥሎም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ለምሳሌ ከእናንተ አንዱ ወዳጅ ኖሮት፥ ያ ወዳጁ በእኩለ ሌሊት ወደዚያ ወደ ወዳጁ ቤት ሄዶ፥ ‘ወዳጄ ሆይ፥ እባክህ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፤ 6ወዳጄ የሆነ አንድ ሰው ከሩቅ መንገድ መጥቶብኝ የማቀርብለት ምንም ምግብ የለኝም!’ ቢለው 7ታዲያ፥ ያ ወዳጁ ከውስጥ ሆኖ፥ ‘እባክህ አታስቸግረኝ! በሩ ተቈልፎአል፤ ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ ተኝተዋል፤ ስለዚህ ተነሥቼ የፈለግኸውን እንጀራ ልሰጥህ አልችልም፤’ ይለዋልን? 8ምንም እንኳ ስለ ወዳጅነቱ ተነሥቶ ሊሰጠው ባይፈልግ ስለ ነዘነዘው ተነሥቶ የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል እላችኋለሁ።
9“ስለዚህ እኔም እናንተን የምላችሁ ይህን ነው፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ 10የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ መዝጊያ ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል። 11ከእናንተስ አባት ሆኖ፥ ልጁ [ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው ማን ነው?] ዓሣስ ቢለምነው በዓሣ ፈንታ እባብ ይሰጠዋልን? 12ወይስ ዕንቊላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? 13እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ነገር መስጠትን ካወቃችሁ በሰማይ የሚኖር አባታችሁማ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!”
ኢየሱስና ብዔልዜቡል
(ማቴ. 12፥22-30ማር. 3፥20-27)
14አንድ ቀን ኢየሱስ የማያናግር ጋኔን ከአንድ ድዳ ሰው ያስወጣ ነበር፤ ጋኔኑም በወጣ ጊዜ ድዳው ሰው መናገር ጀመረ፤ ሕዝቡም በዚህ ነገር እጅግ ተደነቁ። 15አንዳንዶች ግን “አጋንንትን የሚያስወጣው የአጋንንት አለቃ በሆነው በብዔልዜቡል ነው፤” አሉ። #ማቴ. 9፥34፤ 10፥25።
16ሌሎች ደግሞ ሊፈትኑት ፈልገው ከሰማይ አንድ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። #ማቴ. 12፥38፤ 16፥1፤ ማር. 8፥11። 17ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “አንድ መንግሥት ተከፋፍሎ እርስ በርስ የሚለያይ ከሆነ፥ ያ መንግሥት ይጠፋል፤ እንዲሁም አንድ ቤተሰብ እርስ በርሱ ከተለያየ ይወድቃል። 18ስለዚህ ሰይጣን እርስ በርሱ የሚለያይ ከሆነ የእርሱ መንግሥት እንዴት ጸንቶ መቆም ይችላል? እናንተ ግን ‘እርሱ አጋንንትን የሚያስወጣ በብዔልዜቡል ነው፤’ ትሉኛላችሁ። 19ታዲያ፥ እኔ አጋንንትን በብዔልዜቡል የማስወጣ ከሆንኩ ልጆቻችሁስ በማን ያስወጡአቸዋል? ስለዚህ የገዛ ልጆቻችሁ እንኳ ይፈርዱባችኋል። 20እንግዲህ እኔ አጋንንትን በእግዚአብሔር ኀይል የማስወጣ ከሆነ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መምጣትዋን ዕወቁ።
21“አንድ ኀይለኛ ሰው የጦር መሣሪያ ይዞ ቤቱን የሚጠብቅ ከሆነ ንብረቱ በደንብ ይጠበቅለታል፤ 22ነገር ግን ከእርሱ የበለጠ ኀይለኛ ሰው መጥቶ ካሸነፈው የተማመነበትን የጦር መሣሪያ ይወስድበታል ንብረቱንም ሁሉ ዘርፎ ያካፍላል።
23“ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ እኔን ይቃወማል፤ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ይበትናል። #ማር. 9፥40።
የርኩስ መንፈስ በሰው ውስጥ ተመልሶ መግባት
(ማቴ. 12፥43-45)
24“ርኩስ መንፈስ ከሰው ውስጥ በወጣ ጊዜ የሚያርፍበት ቦታ በመፈለግ ውሃ በሌለበት በደረቅ ምድር ሁሉ ይዞራል፤ የሚያርፍበት ቦታ ካላገኘ ግን ‘ወደወጣሁበት ቤቴ ተመልሼ ልሂድ’ ይላል። 25ተመልሶ ሲመጣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። 26ከዚህ በኋላ ሄዶ ከእርሱ ይብስ የከፉ ሌሎች ሰባት አጋንንት ይዞ ይመጣል፤ ቀድሞ እርሱ በነበረበት ቤትም ገብተው በዚያ ይኖራሉ፤ የዚያም ሰው የመጨረሻ ሁኔታ ከመጀመሪያው ይልቅ የባሰ ይሆናል።”
እውነተኛ በረከት
27ኢየሱስ ይህን በሚናገርበት ጊዜ አንዲት ሴት ከሕዝቡ መካከል ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “አንተን ወልዳ ያጠባች እናት የተባረከች ናት፤” አለች።
28ኢየሱስ ግን “የተባረኩስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው በሥራ ላይ የሚያውሉት ናቸው፤” አላት።
የዮናስ ምልክትነት
(ማቴ. 12፥38-42) #ማቴ. 16፥4ማር. 8፥12
29ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ መጥተው በተሰበሰቡ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ይህ ትውልድ ክፉ ትውልድ ነው፤ ምልክት ለማየት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም። 30ነቢዩ ዮናስ ለነነዌ ከተማ ሰዎች ምልክት እንደ ነበረ እንዲሁም የሰው ልጅ ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል። #ዮናስ 3፥4። 31የደቡብ ንግሥት በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ በእርሱ ላይ ትፈርዳለች፤ እርስዋ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከዓለም ዳርቻ መጥታለች፤ ነገር ግን እነሆ፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ፤ #ዘሌ. 27፥30። 32እንዲሁም የነነዌ ከተማ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው በእርሱ ላይ ይፈርዱበታል፤ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት በሰሙ ጊዜ በኃጢአታቸው ተጸጽተው ንስሓ ገብተዋል፤ ነገር ግን እነሆ፥ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።”
የሰውነት መብራት
(ማቴ. 5፥156፥22-23)
33ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “መብራት አብርቶ በስውር ቦታ የሚያስቀምጠው፥ ወይም እንቅብ የሚደፋበት ማንም የለም፤ ይልቅስ ሰዎች ወደ ውስጥ ሲገቡ እንዲታያቸው ከፍ አድርጎ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል። 34የሰውነትህ መብራት ዐይንህ ነው፤ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ ሰውነትህ ሁሉ በብርሃን የተሞላ ይሆናል፤ ዐይንህ ግን ታማሚ ከሆነ መላ ሰውነትህ ሁሉ ጨለማ ይሆናል። 35ስለዚህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ እንዳይሆን ተጠንቀቅ። 36እንግዲህ ሰውነትህ ሁሉ ምንም ጨለማ ሳይኖርበት በብርሃን የተሞላ ከሆነ ሁለመናህ ደማቅ መብራት ለአንተ እንደሚያንጸባርቅ ዐይነት ብሩህ ይሆናል።”
ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን መወገዛቸው
(ማቴ. 23፥1-36ማር. 12፥38-40)
37ኢየሱስ ይህን በሚናገርበት ጊዜ አንድ ፈሪሳዊ ምሳ ጋበዘው፤ ወደ ፈሪሳዊው ቤት ገብቶ ምሳ ለመብላት ወደ ማእድ ቀረበ። 38ኢየሱስ ምሳ ከመብላቱ በፊት እጁን ስላልታጠበ ፈሪሳዊው ተደነቀ። 39ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ “እናንተ ፈሪሳውያን የብርጭቆውንና የሳሕኑን ውጪውን አጥርታችሁ ታጥባላችሁ፤ በውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶባችኋል። 40እናንተ ሞኞች! የውጪውን የፈጠረ አምላክ የውስጡንስ አልፈጠረምን? 41በብርጭቋችሁና በሳሕናችሁ ውስጥ ያለውን ለድኾች ስጡ፤ ከዚህ በኋላ ሁሉ ነገር ንጹሕ ይሆንላችኋል።
42“እናንተ ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! በአንድ በኩል ከአዝሙድና ከጤናዳም፥ ከልዩ ልዩ ጥቃቅን አትክልቶችም ዐሥራት ታወጣላችሁ፤ በሌላ በኩል ግን ትክክለኛ ፍርድንና የእግዚአብሔርን ፍቅር ትተዋላችሁ፤ ያንን ስታደርጉ ይህንን መተው አልነበረባችሁም።
43“እናንተ ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! በምኲራብ ውስጥ በክብር ወንበር ላይ መቀመጥ ትወዳላችሁ፤ እንዲሁም በአደባባይና በገበያ ቦታ ሰው ሁሉ እጅ እንዲነሣችሁ ትፈልጋላችሁ። 44ሰዎች ሳያውቁ በላዩ የሚሄዱበትን ምልክት የሌለውን መቃብር ስለምትመስሉ ወዮላችሁ!”
45ከሕግ መምህራኑም አንዱ ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ፥ ይህንን ስትል እኛንም መስደብህ ነው!” አለው።
46ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “እናንተም የሕግ መምህራን ወዮላችሁ! በሰው ላይ ከባድ ሸክም ትጭናላችሁ፤ እናንተ ግን ሸክሙን በጣታችሁ እንኳ አትነኩትም። 47እንዲሁም አባቶቻችሁ ለገደሉአቸው ነቢያት መቃብሮቻቸውን በማስጌጥ የምትሠሩ ስለ ሆናችሁ ወዮላችሁ! 48እንግዲህ አባቶቻችሁ ለገደሉአቸው ነቢያት መቃብሮቻቸውን በማሠራታችሁ እናንተ የክፉ ሥራቸው ተባባሪዎችና ምስክሮች ናችሁ። 49በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ ትላለች፤ ‘ነቢያትንና ሐዋርያትን ወደ እነርሱ እልካለሁ፤ አንዳንዶችን ይገድላሉ፤ የቀሩትንም ያሳድዳሉ፤ 50ዓለም ከተፈጠረች ጀምሮ ለፈሰሰው የነቢያት ደም፥ ይህ ትውልድ በፍርድ ይጠየቅበታል።’ 51በእርግጥ እነግራችኋለሁ፤ ከአቤል ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ መካከል እስከ ተገደለው እስከ ዘካርያስ ድረስ ስለ ፈሰሰው ደም ይህ ትውልድ በፍርድ ይጠየቅበታል።
52“እናንተ የሕግ መምህራን ወዮላችሁ! የዕውቀት በር መክፈቻ የሆነውን የእውነት ቊልፍ ይዛችኋል፤ ነገር ግን እናንተ ራሳችሁ አልገባችሁበትም፤ መግባት የሚፈልጉትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።”
53ኢየሱስ ከዚያ ቦታ ሊሄድ በተነሣ ጊዜ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ይቃወሙትና ብዙ ጥያቄም ያቀርቡለት ጀመር፤ 54ይህንንም ያደረጉት በንግግሩ ሊያጠምዱት ፈልገው ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ