ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ተአምራት፥ በጢሮስና በሲዶና ተደርገው ቢሆን ኖሮ በዚያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የሐዘን ልብስ ለብሰውና ዐመድ ላይ ተቀምጠው፥ ገና ዱሮ ንስሓ በገቡ ነበር። ስለዚህ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ቅጣቱ ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም! እስከ ሰማይ ከፍ ለማለት ፈልገሻልን? ታዲያ ወደ ሲኦል ትወርጂአለሽ።” እንደገናም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል፤ እናንተን የማይቀበል እኔን አይቀበልም፤ እኔን የማይቀበልም የላከኝን አይቀበልም፤” አላቸው። ሰባ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከተላኩበት በጣም ደስ ብሎአቸው ተመለሱ፤ ወደ ኢየሱስም ቀርበው፦ “ጌታ ሆይ! በአንተ ስም አጋንንት እንኳ ታዘውልናል” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ተወርውሮ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁት፤ እነሆ! እባብንና ጊንጥን እንድትረግጡ፥ የጠላትንም ኀይል ሁሉ እንድትቋቋሙ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁ ምንም ነገር የለም። ነገር ግን ስማችሁ በሰማይ መዝገብ ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ እንጂ አጋንንት ስለ ታዘዙላችሁ አትደሰቱ።” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በቅዱስ መንፈሱ ተደስቶ እንዲህ አለ፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ! ይህንን ነገር ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ላልተማሩት ስለ ገለጽክላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎ፥ አባት ሆይ፥ ይህን ለማድረግ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኖአል። “ሁሉ ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ወልድ ማን መሆኑን ከአብ በቀር ማንም የሚያውቅ የለም፤ እንዲሁም አብ ማን መሆኑን ከወልድ በቀር ወይም ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድለት ሰው በቀር ሌላ ማንም የሚያውቅ የለም።” ቀጥሎም ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መለስ ብሎ ለብቻቸው እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ የተባረኩ ናቸው። በእውነቱ ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ለማየት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አላዩም፤ እናንተ የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አልሰሙም።” አንድ ቀን አንድ የሕግ መምህር ወደ ኢየሱስ መጣ፤ ሊፈትነውም ፈልጎ “መምህር ሆይ! የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባኛል?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም “በሕግ ምን ተጽፎአል? አንብበህስ እንዴት ትረዳዋለህ?” አለው። ሰውየውም “ሕጉማ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ኀይልህ፥ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ እንዲሁም ‘ጐረቤትህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፤’ ይላል” አለው። ኢየሱስም “በትክክል መልሰሃል፤ እንግዲህ አንተም ይህን አድርግ! የዘለዓለም ሕይወትንም ታገኛለህ” አለው። የሕግ መምህሩ ግን ራሱን ጻድቅ ለማድረግ ፈልጎ፥ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በመንገድ ላይ ሳለ ቀማኞች አግኝተውት ልብሱን ገፈፉት፤ ከደበደቡትም በኋላ ሊሞት ሲያጣጥር ጥለውት ሄዱ። እንደ አጋጣሚ አንድ ካህን በዚያ መንገድ ይሄድ ነበር፤ ተደብድቦ የተጣለውን ሰው ባየው ጊዜ ምንም ሳያደርግለት በሌላ በኩል አልፎ ሄደ። እንዲሁም አንድ ሌዋዊ በዚያ መንገድ ይሄድ ነበር፤ እርሱም ሰውየውን ባየው ጊዜ ምንም ሳያደርግለት በሌላ በኩል አልፎ ሄደ። አንድ ሳምራዊ ግን በዚያ በኩል ሲያልፍ ወደ ሰውየው መጣ፤ ባየውም ጊዜ ራራለት፤ ወደ እርሱም ቀርቦ ዘይትና የወይን ጠጅ በቊስሉ ላይ አፈሰሰ፤ በጨርቅም ጠምጥሞ አሠረለት፤ ከዚያም በኋላ በገዛ ራሱ አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ አንድ የእንግዶች ማደሪያ ቤት ወሰደው፤ በዚያም በልዩ ጥንቃቄ ተንከባከበው፤ በማግስቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ማደሪያው ባለቤት ሰጠና ‘ይህን ሰው በጥንቃቄ አስታምልኝ፤ ተጨማሪ ወጪ ብታደርግም በምመለስበት ጊዜ እከፍልሃለሁ፤’ አለው። “ታዲያ፥ ከእነዚህ ከሦስት ሰዎች፥ በቀማኞቹ ተደብድቦ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነለት የትኛው ይመስልሃል?” የሕግ መምህሩም “ያ የራራለትና የረዳው ነው፤” ሲል መለሰ፤ ኢየሱስም “እንግዲያውስ ሂድ፤ አንተም እንዲሁ አድርግ!” አለው።
የሉቃስ ወንጌል 10 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 10:13-37
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች