የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 10:13-37

ሉቃስ 10:13-37 NASV

“ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ታምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርገው ቢሆን ኖሮ፣ ገና ዱሮ ማቅ ለብሰው፣ ዐመድ ነስንሰው ንስሓ በገቡ ነበር። ነገር ግን በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፤ ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ልትዪ ነውን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ። “እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል፤ እናንተን የማይቀበል እኔን አይቀበልም፤ እኔንም የማይቀበል የላከኝን አይቀበልም።” ሰባ ሁለቱም ደስ እያላቸው ተመልሰው፣ “ጌታ ሆይ፤ አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዙልን” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እንግዲህ እባቡንና ጊንጡን እንድትረግጡ፣ በጠላትም ኀይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁም አንዳች ነገር አይኖርም። ይሁን እንጂ መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚያ ደስ አይበላችሁ፤ ስማችሁ ግን በሰማይ ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።” በዚያ ጊዜ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አድርጎ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ፤ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፤ ይህ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኗልና። “ሁሉም ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ደግሞም ወልድ ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፤ አብ ማን እንደ ሆነም ከወልድ በቀር፣ ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቅ የለም።” ወደ ደቀ መዛሙርቱም ዘወር ብሎ ለብቻቸው እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው፤ እላችኋለሁና፤ ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ለማየት ፈልገው አላዩም፤ የምትሰሙትንም ለመስማት ፈልገው አልሰሙም።” እነሆም አንድ ቀን፣ አንድ ሕግ ዐዋቂ ኢየሱስን ሊፈትነው ተነሥቶ፣ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” አለው። ኢየሱስም፣ “በሕግ የተጻፈው ምንድን ነው? እንዴትስ ታነብበዋለህ?” ሲል መለሰለት። ሰውየውም መልሶ፣ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህና በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል” አለው። ኢየሱስም፣ “በትክክል መልሰሃል፤ አንተም እንደዚሁ አድርግ፤ በሕይወት ትኖራለህ” አለው። ሰውየውም ራሱን ጻድቅ ለማድረግ ፈልጎ፣ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መልስ ሰጠው፤ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በወንበዴዎች እጅ ወደቀ፤ ልብሱንም ገፍፈው ደበደቡት፤ በሞት አፋፍ ላይ ጥለውት ሄዱ። አንድ ካህን በአጋጣሚ በዚያው መንገድ ቍልቍል ሲወርድ አየውና ገለል ብሎ ዐለፈ። ደግሞም አንድ ሌዋዊ እዚያ ቦታ ሲደርስ አየውና እርሱም ገለል ብሎ ዐለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን እግረ መንገዱን ሲሄድ ሰውየው ወዳለበት ቦታ ደረሰ፤ ባየውም ጊዜ ዐዘነለት፤ ቀርቦም ቍስሎቹ ላይ ዘይትና የወይን ጠጅ አፍስሶ አሰረለት፤ በራሱም አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማረፊያ ቤት ወሰደው፤ በዚያም ተንከባከበው። በማግስቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለማረፊያ ቤቱ ባለቤት ሰጠና፣ ‘ይህን ሰው ዐደራ አስታምመው፤ ከዚህ በላይ የምታወጣውንም ወጭ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ’ አለው። “እንግዲህ፣ ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው የትኛው ይመስልሃል?” ሕግ ዐዋቂውም፣ “የራራለት ነዋ” አለ። ኢየሱስም፣ “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” አለው።