ኦሪት ዘሌዋውያን 27
27
ለእግዚአብሔር የቀረበውን ስጦታ መዋጀት
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2“ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ አንድ ሰው ለእግዚአብሔር ስእለት ተስሎ ሲፈጸምለት፥ ያ የተሳለው ስለት ሰውን ለመስጠት ከሆነ የመዋጀት ዋጋው እንደ ገመትከው ሆኖ እንደሚከተለው ይሁን፦ 3በቤተ መቅደሱስ በታወቀው ሚዛን ልክ ዕድሜው ከኻያ እስከ ሥልሳ ለሆነ ወንድ 600 ግራም የሚመዝን ጥሬ ብር ይሁን፤ 4በዚሁ ዕድሜ ክልል ለምትገኝ ሴት ሠላሳ ጥሬ ብር ይሁን፤ 5ከአምስት እስከ ኻያ ዓመት ለሆነው ወንድ ኻያ ጥሬ ብር ይሁን፤ በዚሁ ዕድሜ ክልል ላለች ሴት ዐሥር ጥሬ ብር ይሁን፤ 6ዕድሜው ከአንድ ወር እስከ አምስት ዓመት ለሆነ ወንድ አምስት ጥሬ ብር፥ በዚሁ ዕድሜ ክልል ውስጥ ለምትገኝ ሴት ሦስት ጥሬ ብር ይሁን፤ 7ዕድሜው ከስድሳ ዓመት በላይ ለሆነው ወንድ ዐሥራ አምስት ጥሬ ብር፤ ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት በላይ ለሆናት ሴት ዐሥር ጥሬ ብር ይሁን።
8“ስእለት ያደረገው ሰው ይህን ተመን ለመክፈል የማይችል ሆኖ ከተገኘ ያ ለስጦታ የቀረበውን ሰው ወደ ካህኑ ያምጣው፤ ካህኑም ያ ሰው የሚችለውን ያኽል ገምቶ ዝቅተኛ ዋጋ ያስከፍለው።
9“ስእለቱ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበው እንስሳ ከሆነ አይዋጅም፤ ለእግዚአብሔር የቀረበው መባ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናል። 10ሰውየውም ለዚያ እንስሳ ሌላ ምትክ ማቅረብ አይገባውም፤ ምትክ አቅርቦ በተገኘ ጊዜ ግን ሁለቱም እንስሶች ለእግዚአብሔር የተለዩ ይሁኑ። 11ስጦታው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሆኖ ለመቅረብ ተቀባይነት የሌለው ንጹሕ ያልሆነ እንስሳ ከሆነ ግን ሰውየው እንስሳውን ወደ ካህኑ ያምጣ፤ 12ካህኑም የእንስሳውን መልካምነት ወይም መጥፎነት ገምቶ ዋጋውን ይወስን፤ ያም ዋጋ የመጨረሻ ይሆናል፤ 13ባለቤቱም እንስሳውን መልሶ ለመግዛት ቢፈልግ በዋጋው ላይ በመቶ ኻያ እጅ ይጨምር።
14“አንድ ሰው ቤቱን ለእግዚአብሔር የተለየ ስጦታ አድርጎ ሲያቀርብ ካህኑ የቤቱን መልካምነትና መጥፎነት ገምቶ ዋጋውን ይወስን፤ ያም ዋጋ የመጨረሻ ይሆናል። 15ባለንብረቱ ያንን ቤት መልሶ ለመግዛት ቢፈልግ ግን በዋጋው ላይ በመቶ ሃያ እጅ ይጨምር።
16“አንድ ሰው ከመሬቱ ከፍሎ ለእግዚአብሔር የተለየ ስጦታ አድርጎ ቢያቀርብ፥ ዋጋው መሬቱ በሚቀበለው ዘር መጠን ይወሰን፤ ይኸውም ለእያንዳንዱ ኪሎ ግራም ገብስ ተቀባይ መሬት ኀምሳ ጥሬ ብር ይክፈል። 17መሬቱን የኢዮቤልዩ ዓመት እንዳለፈ ወዲያውኑ ለይቶ የሰጠ ከሆነ ሙሉውን ዋጋ መክፈል ይኖርበታል። 18መሬቱን የሰጠው የኢዮቤልዩ ዓመት ካለፈ ዘግይቶ ከሆነ ግን ካህኑ እስከ ተከታዩ የኢዮቤልዩ ዓመት ያለውን ቀሪ ጊዜ በመገመት ዋጋው እንዲቀነስ ያድርግ። #ዘኍ. 18፥14። 19መሬቱን የሰጠው ሰው እንደገና መልሶ ለመግዛት ቢፈልግ በዋጋው ላይ በመቶ ኻያ እጅ ጨምሮ ይክፈል። 20የቀድሞው ባለ ንብረት መሬቱን ከእግዚአብሔር እንደገና ከመዋጀቱ በፊት ለሌላ ሰው ሸጦት ቢገኝ ግን ያንን መሬት እንደገና መልሶ የመዋጀት መብቱን ያጣል፤ 21ይህ ለቀድሞ ባለቤቱ ለመመለስ የማይችለው መሬትም በተከታዩ በኢዮቤልዩ ዓመት ለእግዚአብሔር የተለየ ቀዋሚ ንብረት እንደ ሆነ ይቀራል፤ እርሱም የካህኑ ድርሻ ይሆናል።
22“አንድ ሰው ከሌላ ሰው የገዛውን መሬት ለእግዚአብሔር የተለየ ስጦታ አድርጎ ቢያቀርብ፥ 23ካህኑ ገምግሞ እስከ ተከታዩ የኢዮቤልዩ ዓመት ያለውን ዋጋ ይተምን፤ ሰውየውም በዚያኑ ዕለት ዋጋውን ይክፈል፤ ገንዘቡም ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ ይሆናል። 24በኢዮቤልዩ ዓመት መሬቱ ቀድሞ ለሸጠው ባለ ንብረት ወይም ለዘሩ ይመለሳል።
25“ዋጋቸው ሁሉ የሚተመኑት በቤተ መቅደሱ የሰቅል ሚዛን መሠረት ሲሆን አንዱ ሰቅል ሃያ ጌራ (0.6 ግራም) ነው።
26“በኲር ሆኖ የሚወለድ እንስሳ ቀድሞውኑ የእግዚአብሔር ስለ ሆነ ማንም ሰው የበጎ ፈቃድ ስጦታ አድርጎ ሊያቀርበው አይችልም፤ እንቦሳም ሆነ የበግና የፍየል ግልገሎች አስቀድመው ለእግዚአብሔር የተለዩ ናቸው፤ 27ንጹሕ ያልሆነ የእንስሳ በኲር ግን በይፋ በታወቀው ዋጋ ላይ በመቶ ኻያ እጅ ተጨምሮበት እንደገና መዋጀት ይችላል፤ ባለቤቱ የማይዋጀው ከሆነ ግን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሌላ ሰው ይሸጥ።
28“አንድ ሰው የራሱን ሰውም ሆነ እንስሳን ወይም መሬትን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ እንዲሆን ካደረገው በኋላ ፈጽሞ ሊሸጠውም ሆነ መልሶ ሊዋጀው አይገባውም። 29የሞት ፍርድ የተፈረደበት ሰው እንደገና ሊዋጅ ፈጽሞ አይገባውም፤ እንዲህ ዐይነቱ ሰው መገደል አለበት።
30“ምድሪቱ የምታስገኘው እህልም ሆነ ፍራፍሬ ከዐሥር አንዱ ለእግዚአብሔር የተለየ ነው። 31ከእርሱ ማንኛውንም ነገር መልሶ መዋጀት የሚፈልግ ሰው በይፋ በታወቀው ዋጋ ላይ በመቶ ኻያ እጅ ጨምሮ መግዛት ይችላል። 32ከቤት እንስሶች ከዐሥር አንዱ እጅ የእግዚአብሔር ድርሻ ነው፤ እንስሶች በሚቈጠሩበት ጊዜ ከዐሥር አንዱ ለእግዚአብሔር የተለየ ነው። 33ባለ ንብረቱ እንስሶቹ በየዐይነቱ በሚመድብበት ጊዜ ነውረኛውን ከደኅነኛው አይለይ፤ በእርሱም ሌላ ምትክ አያድርግ። በአንዱ እንስሳ ሌላ እንስሳ ተክቶ ቢገኝ ግን፥ ሁለቱም እንስሶች ለእግዚአብሔር የተለዩ ይሁኑ፤ እንደገና መዋጀትም የለባቸውም።” #ዘኍ. 18፥21፤ ዘዳ. 14፥22-29።
34ለእስራኤል ሕዝብ ይነግር ዘንድ ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ሳለ እግዚአብሔር የሰጠው ትእዛዞች እነዚህ ናቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 27: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997