ኦሪት ዘሌዋውያን 26:27-46

ኦሪት ዘሌዋውያን 26:27-46 አማ05

“ይህም ሁሉ ተፈጽሞባችሁ እኔን መቃወም ብትቀጥሉና ለእኔም ባትታዘዙ፥ በእናንተ ላይ በቊጣ እነሣለሁ፤ በእናንተ ላይ የማመጣውንም ቅጣት ካለፈው ሰባት ጊዜ የበለጠ እንዲሆን አደርጋለሁ። ስለዚህም ከመራባችሁ ጽናት የተነሣ የገዛ ልጆቻችሁን ለመብላት ትገደዳላችሁ። በየኰረብታው ላይ ያሉአችሁን መስገጃዎች እደመስሳለሁ፤ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁንም አፈራርሳለሁ፤ ሬሳዎቻችሁንም በወደቁት ጣዖቶቻችሁ ላይ እጥላለሁ፤ ፈጽሞ እጸየፋችኋለሁ፤ ከተሞቻችሁንም ውድማ አደርጋለሁ የማምለኪያ ስፍራዎቻችሁንም አፈራርሳለሁ መሥዋዕታችሁንም አልቀበልም። ምድራችሁን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ በወረራ የያዛትም ጠላት ጥፋትዋን አይቶ በፍርሃት ይንቀጠቀጣል። በእናንተም ላይ ጦርነት አምጥቼ በባዕዳን አገሮች ሁሉ እበትናችኋለሁ፤ ሰይፍንም አስመዝዝባችኋለሁ፤ ምድራችሁ ሰው አልባ፥ ከተሞቻችሁም ውድማ ይሆናሉ፤ እናንተ በጠላቶቻችሁ አገር በምትኖሩባቸው ዓመቶች ሁሉ ምድራችሁ ባዶ ስለምትሆን ሰንበቶችን ታከብራለች፤ ከዚያ በኋላ ምድሪቱ ዕረፍት አድርጋ በሰንበቶች ትደሰታለች። እናንተ በነበራችሁባት ጊዜ በሰንበቶቻችሁ ያላገኘችውን ዕረፍት አሁን ሰው አልባ በሆነችበት ጊዜ ዐረፈች። “ከስደት የቀሩት ሁሉ ነፋስ የሚነካውን የቅጠል ኮሽታ በሰሙ ቊጥር በድንጋጤ በርግገው እንዲሸሹ አደርጋለሁ፤ በጦርነት ላይ ልክ ጠላት እንደሚያሳድዳቸው ያኽል ሆነው ይሸሻሉ፤ ምንም ዐይነት ጠላት በአጠገባቸው ሳይኖር ተደናቅፈው ይወድቃሉ፤ ማንም ሳያሳድዳቸው ከጠላት እንደሚሸሹ ሆነው አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ተሰነካክለው ይወድቃሉ፤ ማንኛውንም ጠላት ተቋቊማችሁ ለመዋጋት አትችሉም። በአሕዛብ መካከል ትጠፋላችሁ፤ በጠላቶቻችሁም ምድር ተውጣችሁ ትቀራላችሁ። በጠላቶቻችሁ ምድር ከሞት ተርፋችሁ የምትቀሩት ጥቂቶቻችሁ፥ በራሳችሁና በቀድሞ አባቶቻችሁ ኃጢአት ምክንያት መንምናችሁ ትቀራላችሁ። “ነገር ግን የእናንተ ዘሮች የራሳቸውን ኃጢአት፥ እንዲሁም በእኔ ላይ ያመፁትንና የተቃወሙኝን የቀድሞ አባቶቻቸውን ኃጢአት ይናዘዛሉ፤ እነርሱን ተቃውሜ ወደ ጠላቶቻቸው አገር እንዲሰደዱ አደረግሁ፤ ሆኖም እልኸኛ ልባቸው በትሕትና ተሰብሮ ከኃጢአታቸው ቢታረሙ፥ ከያዕቆብ፥ ከይስሐቅና ከአብርሃም ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስባለሁ፤ ምድሪቱንም ለሕዝቤ ለመስጠት የሰጠሁትን የተስፋ ቃል አድሳለሁ። ከሕዝብዋ ባዶ የሆነችው ምድር ውድማ ሆና ሰንበቶችን ታከብራለች፤ እነርሱም ሥርዓቴን ስላልተቀበሉና ሕጌን ስላላከበሩ፥ በኃጢአታቸው ምክንያት ቅጣቱን በሙሉ ይቀበላሉ። ይሁን እንጂ በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ እንኳ እስከ መጨረሻ አልተዋቸውም ወይም አልደመስሳቸውም፤ ይህማ ቢሆን ኖሮ ከእነርሱ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን እስከ መጨረሻ ባልጠበቅሁም ነበር፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝ። ነገር ግን አምላካቸው እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ካወጣኋቸው ከአባቶቻቸው ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ስለ እነርሱ አስታውሳለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” እግዚአብሔር በእርሱና በእስራኤል ሕዝብ መካከል በሙሴ አማካይነት በሲና ተራራ ላይ የሰጣቸው ደንቦች፥ ሥርዓቶችና ሕጎች እነዚህ ናቸው።