እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ትሰግዱላቸው ዘንድ ማናቸውንም ዐይነት ጣዖቶች አትሥሩ፤ እንዲሁም ምስል ወይም ሐውልት ወይም የተቀረጸ የድንጋይ ዐምድ አታቁሙ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ ሰንበቶቼን ጠብቁ፤ መቅደሴን አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “በሕጌ ብትመሩና ትእዛዞቼንም ብትጠብቁ፥ ምድራችሁ በሰብል፥ ዛፎቻችሁም በፍሬ የተሞሉ ይሆኑ ዘንድ ዝናብን በወቅቱ እልክላችኋለሁ። ሰብላችሁም እጅግ የበዛ ከመሆኑ የተነሣ ገና መከር መሰብሰብ ሳትጨርሱ፥ የወይን ዘለላ የምትቈርጡበት ጊዜ ይደርሳል፤ የወይን ዘለላም ቈርጣችሁ ሳትጨርሱ እህል የምትዘሩበት ወቅት ይደርሳል፤ ለምግብ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ታገኛላችሁ፤ በምድራችሁም በሰላም ትኖራላችሁ። “በምድራችሁ ሰላምን እሰጣችኋለሁ፤ ማንንም ሳትፈሩ ያለ ስጋት ትተኛላችሁ፤ አደገኞች የሆኑ አራዊትን ከምድራችሁ አስወግዳለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ጦርነት በዚያ አይኖርም። ጠላቶቻችሁን ታሳድዳላችሁ፤ በፊታችሁም በጦርነት ያልቃሉ፤ ከእናንተ አምስቱ መቶውን ጠላት ያሸንፋሉ፤ አንድ መቶው ደግሞ ዐሥሩን ሺህ ድል ይነሣሉ፤ ጠላቶቻችሁም በጦርነት ያልቃሉ። ፊቴን በምሕረት ወደ እናንተ እመልሳለሁ፤ ዘራችሁን አበዛለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ። ገና ያለፈውን ሰብል በመብላት ላይ እያላችሁ፥ ለአዲሱ ሰብል ቦታ ማስለቀቅ ይኖርባችኋል። እኔም መኖሪያዬን በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ አልጸየፋችሁም። እኔ ከእናንተ ጋር እሄዳለሁ፤ አምላካችሁ እሆናለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ። በባርነት እንዳትገዙ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ ተጭኖአችሁ የነበረውን የባርነት ቀንበር ሰብሬ፥ ቀና ብላችሁ እንድትሄዱ አድርጌአለሁ።” እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ነገር ግን እኔን ባትሰሙና እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ ባትፈጽሙ፥ ትእዛዞቼን ባትጠብቁ፥ ሕግጋቴን ብትንቁ፥ ቃል ኪዳኔን ብታፈርሱና ሥርዓቶቼን ብትጸየፉ፥ የሚከተለውን አመጣባችኋለሁ፦ ታላቅ ድንጋጤን፥ ክሳትን፥ ዐይንን የሚያፈዝና ሰውነትን የሚያመነምን የንዳድ በሽታ አመጣባችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁ የሚበሉት ስለ ሆነ ዘራችሁን በከንቱ ትዘራላችሁ። ፊቴን በቊጣ እመልስባችኋለሁ፤ በጠላቶቻችሁም ትሸነፋላችሁ የሚጠሉአችሁም ይገዙአችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ። “ይህም ሁሉ ከደረሰባችሁ በኋላ እንኳ የማትታዘዙኝ ከሆናችሁ፥ በእናንተ ላይ የማመጣውን ቅጣት ሰባት ጊዜ እጥፍ እንዲበዛ አደርገዋለሁ። እልኸኛ ትዕቢታችሁን አዋርዳለሁ፤ ሰማይን እንደ ብረት አጠንክሬ ዝናብ እንዳይዘንብ አደርጋለሁ፤ ምድርንም በድርቅ መትቼ እንደ ነሐስ የጠጠረች አደርጋለሁ። ምድራችሁ ሰብልን ዛፎቻችሁም ፍሬን ስለማይሰጡ በከንቱ ትደክማላችሁ። “እኔን በመቃወም ከቀጠላችሁና እኔን የማትሰሙኝ ከሆነ፥ እንደ ኃጢአታችሁ ብዛት ሰባት ጊዜ እጥፍ የሆነ መቅሠፍት አመጣባችኋለሁ። በመካከላችሁ አደገኞች አራዊትን እልካለሁ፤ እነርሱም ልጆቻችሁን ይገድላሉ፤ ከብቶቻችሁንም ያወድማሉ፤ ከእናንተ ጥቂት ሰዎች ብቻ ስለሚቀሩ ጐዳናዎቻችሁ ሁሉ ሰው አልባ ይሆናሉ። “ይህ ሁሉ ቅጣት ከተፈጸመባችሁ በኋላ ባትሰሙኝና እኔን በመቃወም ብትጸኑ፥ በእናንተ ላይ በቊጣ ተመልሼ ካለፈው ሰባት እጥፍ በበረታ ሁኔታ እቀጣችኋለሁ። ከእኔ ጋር የገባችሁትን ቃል ኪዳን በማፍረሳችሁ እናንተን ለመቅጣት ጦርነት አመጣባችኋለሁ፤ በከተሞቻችሁ ብትሰበሰቡም ሊፈወስ የማይችል በሽታ በመካከላችሁ እልካለሁ፤ ለጠላቶቻችሁም እጃችሁን ለመስጠት ትገደዳላችሁ። ምግብ እንድታጡ በማደርግበት ጊዜ እንጀራችሁን ዐሥር ሴቶች በአንድ ምጣድ ይጋግራሉ፤ ምግባችሁንም መጥነው ያቀርቡላችኋል፤ እናንተም በልታችሁ አትጠግቡም።
ኦሪት ዘሌዋውያን 26 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 26:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች