እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንድ ሰው ከሥጋ ደዌ በሽታ ከዳነ በኋላ የሚፈጸምለት የመንጻት ሥርዓት ይህ ነው፦ ንጹሕ መሆኑ በሚነገርለት ቀን ወደ ካህኑ እንዲቀርብ ይደረግ፤ ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጪ አውጥቶ ይመርምረው፤ በሽታው የተፈወሰ ከሆነ፥ ካህኑ ንጹሕ የሆኑ ሁለት ወፎችና የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ቊራጭ፥ ቀይ የግምጃ ክርና የሂሶጵ ቅጠል ጨምሮ እንዲያመጣ ይዘዘው። ከዚህም በኋላ ካህኑ ከወፎቹ አንዱን ንጹሕ የምንጭ ውሃ ባለበት ጐድጓዳ የሸክላ ዕቃ ላይ እንዲታረድ ይዘዝ፤ ሌላውንም ወፍ ወስዶ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ቊራጭ፥ ከቀዩ ከፈይ ክርና ከሂሶጱ ቅጠል ጋር በአንድነት ቀድሞ በታረደው ወፍ ደም ውስጥ ይንከረው፤ ደሙንም ከሥጋ ደዌ በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይርጭ፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅለታል፤ በሕይወት ያለውንም ወፍ ወደ ሜዳ እንዲበር ይለቀዋል። ከበሽታው የነጻው ሰው ልብሱን ያጥባል፤ ጠጒሩን ሁሉ ይላጫል፤ ሰውነቱንም ይታጠባል፤ ከዚያም በኋላ የነጻ ሆኖ ወደ ሰፈር ይገባል፤ ነገር ግን እስከ ሰባት ቀን ከራሱ ድንኳን ውጪ መቈየት አለበት። በሰባተኛውም ቀን እንደገና ራሱን፥ ጢሙን፥ ቅንድቡንና በሌላውም ሰውነት ላይ ያለውን ጠጒር ሁሉ ተላጭቶ ልብሱን በውሃ ይጠብ፤ ሰውነቱንም ይታጠብ፤ ከዚያም በኋላ የነጻ ይሆናል። “በስምንተኛውም ቀን ምንም ነውር የሌለባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና አንድ ዓመት የሆናት አንዲት ቄብ ያምጣ፤ ከዚህም ጋር በወይራ ዘይት የተለወሰ ሦስት ኪሎ ግራም ዱቄትና የሊትር አንድ ሦስተኛ የሆነ የወይራ ዘይት ያምጣ። ካህኑም ሰውየውን ካመጣቸው ከእነዚህ ሁሉ መባዎች ጋር ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወስዶ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባል፤ ከዚህም በኋላ ካህኑ ተባዕት ከሆኑት ከሁለቱ የበግ ጠቦቶች አንዱን የሊትር አንድ ሦስተኛ ከሆነው የወይራ ዘይት ጋር ወስዶ የበደል ስርየት መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል። ካህኑ ይህን በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጎ ያቀርበዋል። ጠቦቱንም ለኃጢአት ስርየት መሥዋዕትና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች በሚታረዱበት ቅዱስ ስፍራ ያርደዋል፤ ይህንንም የሚያደርግበት ምክንያት የበደል ዕዳ መሥዋዕት ልክ ለኃጢአት ስርየት እንደሚቀርበው መሥዋዕት የካህኑ ድርሻ ሆኖ ስለሚሰጥ ነው፤ እርሱም እጅግ የተቀደሰ ነው። ካህኑም ከጠቦቱ ደም ጥቂት ወስዶ የነጻ መሆኑን በሚያስታውቅለት ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንና የቀኝ እግሩን አውራ ጣቶች ይቀባ። ካህኑ ከወይራው ዘይት ጥቂት ወስዶ በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያፍስስ፤ በቀኝ እጁ ጫፍ እያጠቀሰ ከእርሱ ጥቂቱን በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው። በእጁ መዳፍ ላይ ካለውም ዘይት ጥቂት ወስዶ የነጻ መሆኑን ለማስታወቅ የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፥ የቀኝ እጁንና የቀኝ እግሩን አውራ ጣቶች ይቀባ፤ በእጁ መዳፍ ላይ የተረፈውንም ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያፍስሰው፤ በዚህም ዐይነት ካህኑ በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል። “ከዚህም በኋላ ካህኑ ለኃጢአት ስርየት መሥዋዕት በማቅረብ የመንጻትን ሥርዓት ይፈጽማል፤ ቀጥሎም ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርበውን እንስሳ ያርዳል፤ እርሱንም ከእህል መባ ጋር በመሠዊያው ላይ አኑሮ ያቃጥለዋል፤ በዚህ ዐይነት ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ ያም ሰው ንጹሕ ይሆናል። “ሰውየው ይህን ሁሉ ለማምጣት የማይችል ድኻ ከሆነ፥ በመወዝወዝ ለኃጢአት ማስተስረያ ይሆንለት ዘንድ ለበደል መሥዋዕት የሚሆን አንድ ጠቦት ያምጣ፤ ከዚሁም ጋር በወይራ ዘይት የተለወሰ አንድ ኪሎ የላመ ዱቄት ለእህል መባ ያምጣ፤ እንዲሁም የሊትር ሲሶ የሆነ የወይራ ዘይት ያቅርብ፤ እንዲሁም ችሎታው በሚፈቅድለት መጠን ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት ዋኖሶች፥ አንዱን ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያመጣል፤ የመንጻትን ሥርዓት በሚፈጽምበት በስምንተኛው ቀን እነዚህን ሁሉ አምጥቶ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ለካህኑ ይሰጣል። ካህኑም የበጉን ጠቦትና የወይራውን ዘይት ተቀብሎ በእግዚአብሔር ፊት የመወዝወዝ መሥዋዕት አድርጎ ያቀርበዋል። ካህኑ ይህን ለበደል ስርየት መሥዋዕት የቀረበውን የበግ ጠቦት ይረድ፤ ከደሙም ትንሽ ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮ ጫፍ፥ የቀኝ እጁንና የቀኝ እግሩን አውራ ጣቶች ይቀባ፤ ካህኑ ከዘይቱ ትንሽ በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያፈሳል፤ በቀኝ እጁ ጣት እያጠቀሰ ከዚያ ጥቂቱን በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ ይረጫል፤ በእጁ ካለው ጥቂት ዘይት ወስዶ በበደል ስርየት መሥዋዕቱ ደም እንዳደረገው በሚነጻው ሰው በቀኝ ጆሮ የቀኝ እጁ አውራ ጣት መዳፍ ላይና በቀኝ እግሩ አውራ ጣት ላይ ያስነካዋል። በእግዚአብሔር ፊት ለማስተሰረይ ካህኑ በእጁ ላይ የተረፈውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያፈስሳል። የሚነጻውም ሰው ከዋኖስ ወይም ከርግብ እርሱ የሚችለውን አንዱን ያቅርብ፤ አንዱን ለኃጢአት መስዋዕት ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፥ ከዚህም ጋር የእህል መባ ያቅርብ፤ ካህኑም ለሚነጻው ሰው በእግዚአብሔር ፊት ያስተስርይለት። ከሥጋ ደዌ በሽታ ለመንጻት የተመደበውን መሥዋዕት በድኽነቱ ምክንያት ማቅረብ ለማይችል ሰው የሚፈጸመው ሥርዓት ይህ ነው።” እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ወደምሰጣችሁ ወደ ከነዓን ምድር በምትገቡበት ጊዜ በዚያ አገር በሚገኝ በአንድ ቤት ውስጥ ሻጋታ ሳሠራጭ፥ የሻጋታው ምልክት በራሱ ቤት ውስጥ መኖሩን የተገነዘበ ማንም ሰው ሄዶ ለካህኑ ‘በቤቴ ሻጋታ መሰል ነገር አለ’ ብሎ ይንገር፤ ካህኑም ሄዶ የሻጋታውን ዐይነት ከመመርመሩ በፊት በቤቱ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ እንዲወጣ ትእዛዝ ይስጥ፤ አለበለዚያ በቤቱ ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ካህኑ ወደ ቤት ገብቶ ይመርምር፤ የሻጋታውን ዐይነት በሚመረምርበት ጊዜ ግድግዳውን እየቦረቦሩ የሚበሉት አረንጓዴ ወይም ቀይ ዐይነት ዝንጒርጒር ምልክቶች ቢታዩበት፥ ከዚያ ቤት ወጥቶ ለሰባት ቀን እንዲዘጋ ያድርገው። በሰባተኛው ቀን ተመልሶ መጥቶ እንደገና ይመርምረው፤ የሻጋታው ምልክት ተስፋፍቶ ቢገኝ፥ የሻጋታው ምልክት ያለባቸው ድንጋዮች ተፈልፍለው ወጥተው ከከተማው ውጪ በሚገኘው በረከሰ ጒድፍ ማከማቻ እንዲጣሉ ይዘዝ። ከዚያም በኋላ የውስጡ ግድግዳ ሁሉ እንዲፋቅና ምርጊቱ ሁሉ ተቀርፎ ከከተማ ውጪ በሚገኘው በረከሰ ጒድፍ መጣያ እንዲጣል ያድርግ። ከዚህም በኋላ በእነዚያ በቀድሞዎቹ ድንጋዮች ምትክ ሌሎች አዳዲስ ድንጋዮች ተገንብተው ቤቱ በአዲስ ጭቃ ይመረግ። “ድንጋዮቹ ተወግደው፥ ግድግዳው ተፍቆ፥ ምርጊቱም ተነሥቶ ቤቱ በዐዲስ ጭቃ ተመርጎ ከታደሰ በኋላ የሻጋታው ምልክት እንደገና ቢታይ፥ ካህኑ ሄዶ ይመልከተው፤ የሻጋታው ዐይነት የሚስፋፋና የማይለቅ ሻጋታ ስለ ሆነ ቤቱ ርኩስ ነው። ስለዚህ መፍረስ አለበት፤ ድንጋዮቹ እንጨቱና ምርጊቱ ሁሉ ከከተማ ውጪ ተወስዶ በረከሰ ጒድፍ ማከማቻ ስፍራ ይጣል፤ ከተዘጋ በኋላ ወደዚያ ቤት የገባ ሰው ሁሉ እስከ ምሽት ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ በዚያ ቤት ውስጥ የተኛ ወይም ምግብ የተመገበ ቢኖር ልብሱን ይጠብ። “ቤቱ እንደገና ታድሶ ከተለሰነ በኋላ ካህኑ መጥቶ በሚመለከትበት ጊዜ ሻጋታው የመስፋፋት ምልክት የማያሳይ ሆኖ ከተገኘ ግን የሻጋታው ምልክት ጨርሶ ስለ ጠፋ ያ ቤት ንጹሕ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። ቤቱንም ለማንጻት ሁለት ወፎች፥ ጥቂት የሊባኖስ ዛፍ እንጨት፥ የቀይ ከፈይ ክርና የሂሶጵ ቅጠል ይውሰድ። ከወፎቹ አንዱን ንጹሕ የምንጭ ውሃ ባለበት የሸክላ ዕቃ ላይ ይረደው፤ ከዚያም በኋላ የሊባኖሱን ዛፍ እንጨት፥ የሂሶጱን ቅጠል፥ የቀዩን ከፈይ ክርና በሕይወት ያለውን ወፍ በታረደው ወፍ ደምና በምንጩ ውሃ ውስጥ ይንከረው፤ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይርጨው። በዚህም ዐይነት ካህኑ ያንን ቤት በወፉ ደም፥ በንጹሑ ውሃ፥ ሕይወት ባለው ወፍ፥ በሊባኖሱ ዛፍ እንጨት በሂሶጱ ቅጠልና በቀዩ የከፈይ ክር እንዲነጻ ያደርገዋል። ከዚያም በኋላ በሕይወት ያለውን ወፍ ከከተማ ውጪ ወደ ሜዳ እንዲበር ይለቀዋል፤ በዚህም ዐይነት ለቤቱ የማንጻት ሥርዓት ይፈጽማል፤ ቤቱም ንጹሕ ይሆናል። “እነዚህም ለማንኛውም ተላላፊ ለሆነ የሥጋ ደዌ በሽታ፥ ለእከክ የሥርዓት መመሪያዎች ናቸው። በልብስና በቤት ላይ የሚወጣ ሻጋታን፥ እባጭን፥ ሽፍታንና ቋቊቻን ለማንጻት የወጡ ሕጎች ናቸው። እነዚህ ሥርዓቶች አንድን ነገር ንጹሕ መሆኑን ወይም አለመሆኑን የሚወስኑ ናቸው።”
ኦሪት ዘሌዋውያን 14 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 14:1-57
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos