የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሰቈቃወ ኤርምያስ 3

3
በንስሓ የሚገኝ ተስፋ
1በአምላክ የቊጣ በትር መከራን ያየሁ እኔ ነኝ።
2ምንም ብርሃን ወደሌለበት ጨለማ መርቶ ወሰደኝ።
3ቀኑን ሙሉ እኔን ብቻ መላልሶ ቀጣኝ።
4ሥጋዬንና ቆዳዬን አስረጀ፤
አጥንቶቼንም ሰባበረ።
5ከበባ አድርጎ ምርር ባለ ሐዘንና ችግር ውስጥ ከተተኝ።
6ከብዙ ጊዜ በፊት እንደ ሞተ ሰው
በጨለማ ውስጥ እንድቀመጥ አስገደደኝ።
7እንዳላመልጥ ዙሪያዬን አጠረ፤
በከባድ ሰንሰለትም አሰረኝ።
8ለእርዳታ ጩኸቴን ባሰማም እንኳ አላዳምጥ አለኝ።
9መንገዴን በተጠረበ ድንጋይ ዘጋ፤
መተላለፊያዬንም አጣመመ።
10እርሱ ለእኔ
እንደሚሸምቅ ድብና እንደ ተደበቀ አንበሳ ነው።
11ከመንገዴ አውጥቶ ገነጣጠለኝ፤
ብቸኛም አደረገኝ።
12ቀስቱን ገትሮ
ለፍላጾች ዒላማ አደረገኝ።
13ፍላጻዎቹንም አስፈንጥሮ
ወደ ሰውነቴ ጠልቀው እንዲገቡ አደረገ።
14ለሕዝቤ ሁሉ መሳቂያ ሆንኩ፤
በዘፈናቸውም ቀኑን ሙሉ አፌዙብኝ።
15ከችግር የተነሣ ሕይወት እንዲመረኝ አደረገ፤
በእሬትም አጠገበኝ።
16ጥርሶቼ በጠጠር እንዲሰበሩና
ፊቴም በዐመድ ላይ እንዲደፋ አደረገ።
17ሕይወቴ ሰላም እንዲያጣ ተደረገ፤
ደስታም ምን እንደ ሆነ ረሳሁ።
18ስለዚህ፦ “ክብሬ ተለይቶኛል፤
ከእግዚአብሔር የምጠብቀውም ተስፋ ሁሉ
ተቋርጦአል” አልኩ።
19መከራዬንና ከርታታነቴን ማስታወስ
እንደ እሬትና እንደ ሐሞት ሆነብኝ።
20ስለዚህም ሁኔታ ሁልጊዜ ሳስብ
መንፈሴ ይጨነቃል፤
21ሆኖም ይህን አንድ ነገር በማስብበት ጊዜ
በተስፋ እሞላለሁ።
22ይኸውም ሳንጠፋ የቀረነው
የእግዚአብሔር ምሕረት ከቶ የማያቋርጥና
ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ ነው።
23እነርሱ በየማለዳው ይታደሳሉ፤
ስለዚህ የአንተ ታማኝነት ታላቅ ነው።
24የእኔ አለኝታ እግዚአብሔር ስለ ሆነ፥
እርሱን ብቻ ተስፋ አደርጋለሁ።
25እግዚአብሔር በተስፋ ለሚጠባበቁትና
እርሱን ለሚፈልጉ መልካም ነው።
26ሰው የእግዚአብሔርን አዳኝነት
ጸጥ ብሎ መጠበቁ መልካም ነው።
27ሰው በወጣትነቱ መከራን በትዕግሥት ቢቀበል
መልካም ነው።
28እግዚአብሔር መከራውን በሚአመጣበት ጊዜ
ጸጥ ብሎ ለብቻው ቢቀመጥ መልካም ነው።
29እንደገና ተስፋ ሊኖር ስለሚችል
ራሱን ዝቅ አድርጎ ያስገዛ።
30ለሚመታው ጒንጩን ይስጥ፤
ስድብንም ይቀበል።
31ይህን ሁሉ ቢያደርግ
እግዚአብሔር ለዘለዓለም አይተወውም።
32ምንም እንኳ ጭንቀት በሰው ላይ እንዲደርስ ቢፈቅድ
ከተትረፈረፈ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የተነሣ ይራራል።
33ይህም የሚሆነው እርሱ በራሱ ፍላጎት
በሰው ላይ ችግርንና ሐዘንን ስለማያመጣ ነው።
34የአገሪቱ እስረኞች ሁሉ
በግፍ በሚረገጡበት ጊዜ፥
35ልዑል እግዚአብሔር እያየ
ሰብአዊ መብት በሚጣስበት ጊዜ፥
36የአንድ ሰው ጉዳይ ፍትሕ በሚያጣበት ጊዜ
በውኑ ጌታ እነዚህን ነገሮች አያይምን?
37እግዚአብሔር አስቀድሞ የወሰነው ካልሆነ
በትእዛዙ አንድን ነገር ማስደረግ የሚችል ማነው?
38ደግም ሆነ ክፉ ነገር ተግባራዊ የሚሆነው
ልዑል እግዚአብሔር በሚናገረው መሠረት አይደለምን?
39ሰው በሕይወቱ እያለ በኃጢአት ምክንያት ሲቀጣ
የሚያጒረመርመው ለምንድን ነው?
40አካሄዳችንን መርምረን፤
ወደ እግዚአብሔር እንመለስ።
41በሰማይ ወዳለው አምላካችን
ልባችንንና እጃችንን እናንሣ።
42“አምላክ ሆይ! እኛ ኃጢአትና ዐመፅ ሠርተናል፤
አንተም ይቅር አላልከንም።
43“በቊጣ ተሞልተህ አሳደድከን
ያለ ርኅራኄ ገደልከን።
44ጸሎት አልፎ ሊገባ በማይችልበት
ራስህን ጥቅጥቅ ባለ ደመና ሸፈንክ።
መኖሪያህን በደመና ሸፈንክ።
45በሕዝቦች መካከል እንደ ጒድፍና ጥራጊ አደረግኸን።
46“ጠላቶቻችን ሁሉ አፋቸውን ከፈቱብን
47ፍርሀትና ውድቀት
እንዲሁም ጥፋትና ውድመት በእኛ ላይ ደረሱ።
48በሕዝቤ ላይ በደረሰው ጥፋት ምክንያት
እንባ ከዐይኖቼ እንደ ወንዝ ውሃ ይጐርፋል።
49“እንባዬ ያለማቋረጥ ይፈስሳል።
50ይህም የሚሆነው
እግዚአብሔር ከሰማይ ወደ ታች ተመልክቶ
እስኪያይ ድረስ ነው።
51በከተማዬ ውስጥ ባሉት ወጣት ሴቶች ላይ
የደረሰውን ክፉ ዕድል በማየቴ የመረረ ሐዘን ደረሰብኝ።
52“ያለ ምክንያት የሚጠሉኝ ጠላቶቼ
እንደ ወፍ አጠመዱኝ።
53ከነሕይወቴ ጒድጓድ ውስጥ ወርውረው
የጒድጓዱን አፍ በድንጋይ ዘጉብኝ።
54ውሃ ከእራሴ በላይ ሞልቶ ሲፈስ
የምሞትበት ጊዜ የተቃረበ መሰለኝ።
55“እግዚአብሔር ሆይ!
በጥልቅ ጒድጓድ ውስጥ ሆኜ፥
ስምህን ጠራሁ።
56ጆሮህን ወደ እኔ መልስ፤ ለእርዳታም ድረስልኝ”
የሚለውን ልመናዬን ሰምተሃል፤
ስለዚህ ዕረፍትን ስጠኝ።
57በጠራሁህ ጊዜ ወደ እኔ ቀርበህ
“አትፍራ!” አልከኝ።
58“ጌታ ሆይ!
የእኔን ጉዳይ ተከታትለህ ሕይወቴን አዳንክ።
59እግዚአብሔር ሆይ!
በእኔ ላይ የደረሰውን በደል ሁሉ አይተሃልና
ፍትሕን ስጠኝ።
60ጠላቶቼ በእኔ ላይ ያላቸውን የበቀል ስሜትና
ያቀዱትን ሤራ አይተሃል።
61“እግዚአብሔር ሆይ!
በእኔ ላይ የሰነዘሩትን ስድባቸውንና
ያቀዱትንም ሤራ ሰምተሃል።
62ቀኑን ሙሉ ጠላቶቼ በእኔ ላይ
ይንሾካሾካሉ፤ ያጒረመርማሉም።
63ተቀምጠውም ሆነ ቆመው በቅኔ
በእኔ ላይ በአሽሙር የሚሳለቁ መሆናቸውን ተመልከት።
64“አምላክ ሆይ! ለፈጸሙት ተግባር የሚገባቸውን ዋጋ ስጣቸው።
65ርግማንህ በእነርሱ ላይ ይሁን!
ተስፋ እንዲቈርጡም አድርጋቸው!
66እግዚአብሔር ሆይ!
በቊጣህ አሳዳቸው፤ ከሰማያትም በታች ደምስሳቸው!”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ