ሰቈቃወ ኤርምያስ 2
2
እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ላይ ያመጣው ቅጣት
1እግዚአብሔር በቊጣው ጽዮንን ምንኛ አዋረዳት!
ወደ ሰማይ ከፍ ብላ የነበረችውን
የእስራኤልን መመኪያ ወደ ምድር ጣላት፤
በቊጣው ቀን የእግሩ ማሳረፊያ መሆንዋን
ሊያስታውስ አልፈቀደም።
2ጌታ የእስራኤልን መኖሪያ ሁሉ ያለ ምሕረት አጠፋ፤
በቊጣውም የይሁዳን ሕዝብ ምሽግ አፈረሰ፤
መንግሥትዋንና ባለ ሥልጣኖቿን ወደ ምድር ጥሎ አዋረደ።
3በኀይለኛ ቊጣው የእስራኤልን ኀይል ሁሉ አዳከመ፤
ጠላትም እያየ ለእነርሱ የሚሰጠውን ድጋፍ አቋርጦ፥
በያዕቆብም ዘር ላይ እንደሚንበለበል እሳት ቊጣውን አቀጣጠለ፤
ቊጣው ጐረቤቶቹንም ሁሉ አወደመ።
4እንደ ጠላት ቀስቱን ገተረ፤
በቀኝ እጁ የያዘውን በእኛ ላይ አነጣጠረ፤
በኢየሩሳሌም ከተማ የምንመካባቸውን ሁሉ ገደለ፤
ቊጣውንም እንደ እሳት አቀጣጠለ።
5እግዚአብሔር እንደ ጠላት እስራኤልን አጠፋ፤
ቤተ መንግሥቶችዋን አወደመ፤
ምሽጎችዋን አፈራረሰ፤
በይሁዳ ሕዝብም ለቅሶና ዋይታን አበዛ።
6መቅደሱን በአትክልት ቦታ ውስጥ እንዳለ መጠለያ አወደመ፤
እግዚአብሔር በጽዮን በዓሎችንና ሰንበቶችን አስቀረ፤
በኀይለኛ ቊጣውም ንጉሡንና ካህኑን አዋረደ።
7እግዚአብሔር መሠዊያውን ናቀ፤ መቅደሱንም ተወ፤
የቤተ መንግሥቶችዋን ቅጽሮች ለጠላት አሳልፎ ሰጠ፤
በበዓላት ቀን እንደሚደረገው
በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከፍተኛ ድምፅ ተሰማ።
8እግዚአብሔር የኢየሩሳሌምን ከተማ ቅጽር ለማፍረስ ወስኖ ገመዱን ዘረጋ፤
ከማጥፋት አልተመለሰም፤
የመጠበቂያ ግንቡና ቅጽሩ ተፈረካከሱ፤
በአንድነትም ፈረሱ።
9የቅጽር በሮች ከመሬት በታች ተቀበሩ፤
መወርወሪያዎቻቸውም ተሰባብረው ወደቁ፤
ንጉሡና መሳፍንቱ አሁን በአሕዛብ መካከል በስደት ላይ ናቸው፤
የኦሪት ሕግ ትምህርት ከእንግዲህ ወዲህ አይሰጥም፤
ነቢያትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእይ አይገለጥላቸውም።
10የኢየሩሳሌም ከተማ ሽማግሌዎች ጸጥ ብለው በምድር ላይ ተቀመጡ፤
እነርሱ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው ማቅ ለበሱ፤
የኢየሩሳሌም ልጃገረዶች አንገታቸውን ደፉ።
11ሕዝቤ ስለ ተፈጀ፥
ሕፃናት በከተማይቱ መንገዶች ላይ ስለሚዝለፈለፉ፥
ዐይኖቼ በለቅሶ ደከሙ፤
አንጀቴ ተንሰፈሰፈ፤ ተስፋም ቈረጥሁ።
12በጦር ሜዳ እንደ ቈሰለ ወታደር
በከተማው መንገዶች እየተዝለፈለፉ
በእናታቸው ክንድ ላይ ሆነው፥
“ምግብና ውሃ!” እያሉ እያለቀሱ፥
ሕይወታቸው ያልፋል።
13ምን ልበላችሁ? ከምንስ ጋር ላነጻጽራችሁ?
የተወደደችው ከተማ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ!
እንዳጽናናችሁ ከምን ጋር ላመሳስላችሁ?
በተለይ የኢየሩሳሌም ከተማ ሕዝብ ሆይ!
የሚደርስባችሁ ጥፋት እንደ ባሕር መጠኑ ሰፊ ስለ ሆነ፥
ማን ሊፈውሳችሁ ይችላል?
14የእናንተ ነቢያት ሐሰተኛና አታላይ ራእይ አይተውላችኋል፤
ሐሰተኛና አሳሳች ትንቢት ተናገሩ እንጂ፥
ዕድል ፈንታችሁን ለመለወጥ በደላችሁን አላጋለጡም።
15“ፍጹም ውብ ናት የሚሏት የዓለም መደሰቻ የነበረችው ከተማ ይህች ናትን?”
እያሉ በመንገድ የሚያልፉ ሁሉ
በኢየሩሳሌም ላይ እጃቸውን እያጨበጨቡ
ራሳቸውን በመነቅነቅ አሽሟጠጡ።
16ጠላቶቻችሁ ሁሉ በእናንተ ላይ አፋቸውን ይከፍታሉ፤
ያሽሟጥጣሉ ጥርሳቸውን ያፋጫሉ፤ እንዲህ ሲሉም ይጮኻሉ፦
“ደመሰስናቸው! እሰይ ይህ የምንመኘው ቀን ነበር!
በመጨረሻም አየነው።”
17እግዚአብሔር ያሰበውን ፈጸመ፤
ቀድሞ የተናገረውን ቃል ተግባራዊ አደረገ፤
ከረጅም ጊዜ በፊት በወሰነው መሠረት ያለ ርኅራኄ አፈራረሰ፤
ጠላት በእናንተ ላይ ደስ እንዲሰኝ አደረገ፤
የጠላቶቻችሁንም ኀይል አበረታ።
18በኢየሩሳሌም ቅጥር ውስጥ የምትኖሩ ሕዝብ ሆይ!
ወደ እግዚአብሔር ጩኹ!
ዕንባችሁም ሌሊትና ቀን እንደ ጐርፍ ይውረድ፤
በፍጹም ዕረፍት አታድርጉ፤ ለዐይኖቻችሁም ፋታን አትስጡ።
19እናንተ ሌሊቱን በሙሉ ተነሥታችሁ ጩኹ፤
በልባችሁ የሚሰማችሁን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ፊት አቅርቡ፤
በየመንገዱ ማእዘን በራብ ለሚዝለፈለፉ ልጆቻችሁ ሕይወት
በጸሎት እጆቻችሁን ወደ እግዚአብሔር አንሡ።
20ጌታ ሆይ! ተመልከት!
ከአሁን ቀደም እንደዚህ የጨከንክበት ሕዝብ አለ ወይ?
ሴቶች የወለዱአቸውንና ያሳደጓቸውን ሕፃናት ይብሉን!
በጌታ ቤተ መቅደስ ውስጥስ ካህናትና ነቢያት ይገደሉን!
21ወጣቶችና ሽማግሌዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ሞተው በየመንገዱ ዳር ወደቁ፤
ወጣቶች ወንዶችና ሴቶች በጠላት ሰይፍ ተጨፈጨፉ፤
በቊጣህ ቀን ያለ ምሕረት እንዲታረዱ አደረግህ።
22የበዓል ቀን ይመስል ጠላቶቼን ከየቦታው ጋብዘሃል፤
በቊጣህ ቀን አንድም ያመለጠ ወይም በሕይወት የተረፈ የለም፤
ወልጄ ያሳደግኋቸውን ጠላቴ ፈጃቸው።
Currently Selected:
ሰቈቃወ ኤርምያስ 2: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997