ሰቈቃወ ኤርምያስ 1

1
የኢየሩሳሌም መከራና ሐዘን
1በአንድ ወቅት በሕዝብ ተሞልታ የነበረችው ከተማ
እንዴት ብቸኛ ሆነች!
በሕዝቦች መካከል ታላቅ የነበረችው
እንዴት ባል እንደ ሞተባት ሴት ሆነች!
በአውራጃዎች መካከል ልዕልት የነበረችው፥
አሁን እርስዋ እንደ ባሪያ ሆነች።
2በሌሊት እጅግ ታለቅሳለች፤
እንባዋ በጒንጮችዋ ላይ ይወርዳል፤
ከአፍቃሪዎችዋ ሁሉ
እርስዋን የሚያጽናና አንድ እንኳ የለም፤
ወዳጆችዋ የነበሩ ሁሉ ከድተዋታል፤
በጠላትነትም ተነሥተውባታል።
3የይሁዳ ሕዝብ ከጭንቀትና ከከባድ የባርነት ሥራ በኋላ ወደ ምርኮ ተወሰዱ፤
አሁን እነርሱ በሕዝቦች መካከል ሲኖሩ
ዕረፍት አያገኙም፤
እነርሱ በጭንቀት ውስጥ እያሉ
አሳዳጆቻቸው ደረሱባቸው።
4ማንም ሰው በዓላቱን ለማክበር ስለማይመጣ
የጽዮን መንገዶች ጭር ይላሉ፤
በሮችዋ ሁሉ ባዶ ናቸው፤
ካህናትዋ ይቃትታሉ
ልጃገረዶችዋ በሐዘን ይጨነቃሉ
የጽዮንም ዕድል ፈንታ የመረረ ይሆናል።
5ከኃጢአትዋ ብዛት የተነሣ
እግዚአብሔር ችግር እንዲደርስባት አደረገ፤
ጠላቶችዋ ገዢዎችዋ ሆነዋል፤
ልጆችዋም በጠላት ተማርከው ተወስደዋል
ጠላቶችዋ ግን ተሳክቶላቸዋል።
6የኢየሩሳሌም ክብር ሁሉ ጠፍቶአል፤
መሪዎችዋ መሰማሪያ እንዳጡ ዋልያዎች ናቸው፤
አሳዳጆቻቸው ሲያባርሩአቸው
ጒልበታቸው እስኪዝል ድረስ ሸሹ።
7የኢየሩሳሌም ሕዝብ በቀድሞ ጊዜ የነበሩአቸውን የከበሩ ነገሮች
በችግራቸውና በጭንቀታቸው ቀን ያስታውሳሉ፤
እነርሱም በጠላት እጅ በወደቁ ጊዜ፥
አንድም ረዳት ባልነበራቸው ጊዜ፥
ጠላቶቻቸው የከተማቸውን ውድቀት ተመልክተው ተሳለቁባቸው።
8ኢየሩሳሌም ከባድ ኃጢአት ሠርታለች፤
መሳለቂያም ሆናለች፤
ዕርቃንዋን ስላዩአት የሚያከብሩአት ሁሉ ይንቁአታል፤
እርስዋ ራስዋ እየቃተተች ፊትዋን ታዞራለች።
9አደፍዋ በቀሚስዋ ላይ ይታያል፤
ለወደፊት ምን እንደሚደርስባት አላሰበችም፤
አወዳደቅዋ የሚያሰቅቅ ነው፤
የሚያጽናናት ከቶ የለም፤
ጠላቶችዋ ድል ስላደረግዋት፥
መከራዋን እንዲመለከትላት ወደ እግዚአብሔር ጸለየች።
10የኢየሩሳሌም ሕዝብ ጠላቶች ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የሕዝቡን ሀብት ዘረፉ፤
ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ እንዳይገቡ
የተከለከሉ አሕዛብ እንኳ
ቤተ መቅደስዋን ሲወሩ ታዩ።
11ሕዝብዋ ምግብ ማግኘት ፈልገው ይቃትታሉ፤
በሕይወት ለመኖር ሲሉ
ሀብታቸውን ሁሉ በምግብ ይለውጣሉ፤
የኢየሩሳሌም ሕዝብ “እግዚአብሔር ሆይ! ተመልከተን!
ውርደታችንን ሁሉ እይልን!” እያሉ ይጮኻሉ።
12እግዚአብሔር ጽኑ ቊጣውን በእኛ ላይ ባወረደበት ቀን
በእኛ ላይ እንደ ደረሰው ያለ መከራ
የደረሰበት ሰው ያለ እንደ ሆነ
እናንተ አላፊ አግዳሚዎች
እስቲ እዩ ተመልከቱ!
ይህ ሁኔታ ለእናንተ ቀላል ነውን?
13“ከላይ እሳት ላከ፤
እሳቱም ወደ አጥንታችን ዘለቀ፤
ለእግራችን መረብ ዘረጋ፤
ወደ ኋላም መለሰን፤
ሕሊናችንን አስቶ ቀኑን ሙሉ ሰውነታችን እንዲዝል አደረገ።
14“በደሎቼ በጫንቃዬ ላይ ታስረዋል፤
እነርሱም በጣም ከባድ ስለ ሆኑ ኀይል አሳጡን፤
ልንቋቋማቸው ለማንችላቸው ጠላቶቻችን አሳልፎ ሰጠን።
15“እግዚአብሔር ወታደሮቻችንን ከእኛ አስወገደ፤
የጐልማሶቻችንን ኀይል ለማድቀቅ የጦር ሠራዊት ላከብን፤
እግዚአብሔር ባልተደፈረችው ከተማ የሚኖረውን ሕዝባችንን
በወይን መጭመቂያ እንደሚረገጥ የወይን ዘለላ ረገጣቸው።
16“ጠላት ድል ስላደረገ ልጆቻችን ብቸኞች ሆነዋል፤
የሚያበረታታን አጽናኝ ከእኛ ስለ ራቀ፥
እንባ እያፈሰስን እናለቅሳለን።
17“ጽዮን እጆችዋን ትዘረጋለች፤
ነገር ግን ማንም የሚያጽናናት የለም፤
ጐረቤቶቹ ሁሉ የያዕቆብ ዘር ጠላቶች እንዲሆኑ እግዚአብሔር አዟል።
ኢየሩሳሌምም በመካከላቸው እንደ ርኩስ ነገር ሆናለች።
18“በትእዛዙ ላይ ያመፅሁ ስለ ሆነ፥
እግዚአብሔር ባደረገው ነገር እውነተኛ ነው፤
እናንተ ሕዝቦች ሁሉ አድምጡ ሥቃዬንም ተመልከቱ፤
ወጣቶች ወንዶችና ሴቶች ልጆቼ ተማርከው ተወስደዋል።
19“ጓደኞቼን ጠራሁ፤
እነርሱ ግን አታለሉኝ።
ሕይወታቸውን ለማትረፍ ምግብ በመሻት ላይ ሳሉ
ካህናቱና መሪዎቹ ሁሉ በከተማይቱ መንገዶች ሞቱ።
20“እግዚአብሔር ሆይ!
ራሴ እንዴት እንደ ተበጠበጠ ተመልከት!
በአንተ ላይ ስላመፅሁ ሆዴ ተሸበረ፤ ልቤም ተሰበረ፤
በመንገድም ሆነ በቤት ውስጥ ሕዝቤ እያለቀ ነው።
21“ጠላቶቼ ሁሉ ማንም የሚያጽናናኝ ሰው በሌለበት
እንዴት እንደምቃትትና እንደምቸገር ሰሙ፤
አንተ ያደረግኸው መሆኑንም ዐውቀው ተደሰቱ፤
በእነርሱ ላይ ልታመጣባቸው የወሰንከውን ቀን አምጣና
እንደ እኔ ይሁኑ።
22“ ክፉ ሥራቸውን ሁሉ ተመልከት፤
በበደሎቼ ሁሉ ምክንያት በእኔ ላይ እንዳደረግኸው በእነርሱም
ላይ አድርግ ዘወትር ስለምቃትት ልቤ እየደከመብኝ ነው።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ