የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 24:14-31

መጽሐፈ ኢያሱ 24:14-31 አማ05

ኢያሱ ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔርን አክብሩት፤ በፍጹም ቅንነትና በታማኝነት አገልግሉት፤ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶና በግብጽ ይሰግዱላቸው የነበሩትን ባዕዳን አማልክት አስወግዳችሁ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ፤ እርሱን ማምለክ መልካም መስሎ ካልታያችሁ ግን የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ በነበሩበት ጊዜ ያመልኩአቸው የነበሩትን ወይም አሁን በምድራቸው የምትኖሩባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደሆን የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤተሰቤ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ሕዝቡም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “እግዚአብሔርን ትተን ሌሎች ባዕዳን አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ! አምላካችን እግዚአብሔር አባቶቻችንንና እኛን ከግብጽ ባርነት አውጥቶናል፤ ያደረገውን ተአምራት ሁሉ አይተናል፤ ሕዝቦችን ሁሉ አልፈን በመጣንበት ጊዜ በሰላም ጠብቆናል፤ እግዚአብሔር ሕዝቦችን እንዲሁም በምድሪቱ የሚኖሩትን አሞራውያንን ሁሉ ከፊታችን አባሮልናል፤ ስለዚህም እርሱ አምላካችን ስለ ሆነ እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ኢያሱም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ቅዱስና ቀናተኛ አምላክ ስለ ሆነ፥ እናንተ እርሱን ማገልገል አትችሉም፤ የምትሠሩትን ዐመፅና ኃጢአት ሁሉ ይቅር አይልም፤ እርሱን ትታችሁ ባዕዳን አማልክትን ብታመልኩ፥ ደግ ያደረገላችሁ ቢሆንም እንኳ ተመልሶ እርሱ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፤ ያጠፋችሁማል።” ሕዝቡም ለኢያሱ “ይህ ከቶ አይደረግም! እኛ እግዚአብሔርን እናመልካለን” አሉት። ኢያሱም “እንግዲህ እግዚአብሔርን ለማምለክ ስለ መምረጣችሁ ራሳችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ” ሲል ነገራቸው። እነርሱም “አዎ፤ ምስክሮች ነን፤” አሉ። እርሱም “እንግዲያውስ በመካከላችሁ የሚገኙትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አድርጉ” አላቸው። ከዚህም በኋላ ሕዝቡ ኢያሱን “እኛ አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፥ ትእዛዞችንም እንፈጽማለን” አሉት። በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን ገባ፤ በዚያም በሴኬም የሚመሩበትን ሕግና ሥርዓት ሰጣቸው፤ ኢያሱም እነዚህን ትእዛዞች በእግዚአብሔር የሕግ መጽሐፍ ጻፈ፤ ከዚያም በኋላ አንድ ትልቅ ድንጋይ ወስዶ በእግዚአብሔር መቅደስ አጠገብ በሚገኘው የወርካ ዛፍ ሥር አቆመው፤ ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር የነገረንን ቃል ሁሉ ስለ ሰማ ይህ ድንጋይ በእኛ ላይ ምስክር ነው፤ ስለዚህም አምላካችሁን ብትክዱ በእናንተ ላይ ምስክር ይሆንባችኋል።” ከዚህ በኋላ ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ አሰናበተ፤ እያንዳንዱም ወደየርስት ይዞታው ተመልሶ ሄደ። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ በአንድ መቶ ዐሥር ዓመት ዕድሜው ሞተ። እስራኤላውያንም ከጋዓሽ ተራራ በስተሰሜን በኩል በምትገኘው በኮረብታማይቱ በኤፍሬም አገር የራሱ የኢያሱ ርስት በሆነችው በቲምናትሴራሕ ቀበሩት። ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ሁሉ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን አመለኩ፤ ከእርሱም ሞት በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ድንቅ ነገር ሁሉ በዐይናቸው ያዩት ሽማግሌዎች እስከ ኖሩበት ዘመን ድረስ እርሱኑ በማምለክ ኖሩ።