ኢያሱ 24:14-31
ኢያሱ 24:14-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩት፤ በእውነትና በቅንነትም አምልኩት፤ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ፥ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን ሌሎች አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርንም አምልኩ። እግዚአብሔርን ታመልኩ ዘንድ ባትወድዱ ግን፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት፥ ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞሬዎናውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ እርሱ ቅዱስ ነውና።” ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ፥ “እግዚአብሔርን ትተን ሌሎች አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ፤ እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር ያወጣን፥ በዐይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ፥ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ነውና። እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱም የተቀመጡትን አሞሬዎናውያንን ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና እኛ እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ኢያሱም ሕዝቡን፥ “እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፤ ብታስቀኑት መተላለፋችሁንና ኀጢአታችሁን ይቅር አይልም። እግዚአብሔርን ትታችሁ ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ መልካምን ባደረገላችሁ ፋንታ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፤ ያጠፋችሁማል” አላቸው። ሕዝቡም ኢያሱን፥ “እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን” አሉት። ኢያሱም ሕዝቡን፥ “እንድታመልኩት እናንተ እግዚአብሔርን እንደ መረጣችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ” አላቸው፤ እነርሱም፥ “ምስክሮች ነን” አሉ። እርሱም፥ “አሁን እንግዲህ በእናንተ ዘንድ ያሉትን ሌሎች አማልክት አርቁ፤ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አቅኑ” አላቸው። ሕዝቡም ኢያሱን፥ “አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ ቃሉንም እንሰማለን” አሉት። በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ በሴሎም በእስራኤል አምላክ ድንኳን ፊት ሕግንና ፍርድን ሰጣቸው። ኢያሱም ይህን ቃል ሁሉ በእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ጻፈው፤ ኢያሱም ታላቁን ድንጋይ ወስዶ በእግዚአብሔር ፊት በነበረችው በአሆማ ዛፍ በታች አቆማት። ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ፥ “ይህች ድንጋይ በእናንተ ላይ ምስክር ናት፤ እርስዋ፥ ዛሬ እንደ ነገራችሁ በእግዚአብሔር ዘንድ የተባለውን ሁሉ ሰምታለችና በኋላ ዘመን አምላኬን እግዚአብሔርን ብትክዱት ይህች ድንጋይ ምስክር ትሆንባችኋለች” አላቸው። ኢያሱም ሕዝቡን አሰናበተ፤ ሁሉም ወደየቦታቸው ገቡ። እንዲህም ሆነ፤ ከዚህ ነገር በኋላ የእግዚአብሔር አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ። በተራራማውም በኤፍሬም ሀገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ዳርቻ በተምናሴራ ቀበሩት። በዚያም ከግብፅ በወጡ ጊዜ እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእስራኤልን ልጆች በገልገላ የገረዘባቸውን የድንጋይ ባልጩቶችን እርሱን በቀበሩበት መቃብር ከእርሱ ጋር ቀበሩ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ። ኢያሱ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ከኢያሱም በኋላ በነበሩት ለእስራኤልም ያደረገውን የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ ባወቁት በሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ፥ እስራኤል እግዚአብሔርን አመለኩ።
ኢያሱ 24:14-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፤ በፍጹም ታማኝነትም ተገዙለት። የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶና በግብፅ ያመለኳቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ። እግዚአብሔርን ማምለክ የማያስፈልግ መስሎ ከታያችሁ ግን፣ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶ ካመለኳቸው አማልክት ወይም በምድራቸው የምትኖሩባቸው አሞራውያን ከሚያመልኳቸው አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ከዚያም ሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሌሎችን አማልእክት ለማምለክ ብለን እግዚአብሔርን መተው ከእኛ ይራቅ። እኛንና የቀደሙ አባቶቻችንን ከዚያ ከጦርነት ምድር ከግብፅ ያወጣን፣ በፊታችንም እነዚያን ታላላቅ ምልክቶች ያደረገ ማነው? ራሱ አምላካችን እግዚአብሔር አይደለምን? በጕዟችን ላይና ባለፍንባቸውም ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የጠበቀን እርሱ ነው። እንዲሁም እግዚአብሔር በምድሪቱ የሚኖሩትን አሞራውያንን ጨምሮ ሕዝቦችን ሁሉ ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እኛም እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ አምላካችን ነውና።” ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፤ እርሱ ቅዱስ አምላክና፤ ቀናተኛም አምላክ ነው፤ ዐመፃችሁን ወይም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልም። እግዚአብሔርን ትታችሁ ባዕዳን አማልክትን የምታመልኩ ከሆነ፣ መልካም ነገር ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፤ ያጠፋችኋልም።” ሕዝቡ ግን ኢያሱን፣ “የለም! እኛ እግዚአብሔርን እናመልካለን” አሉት። ከዚያም ኢያሱ፣ “እንግዲህ እግዚአብሔርን ለማምለክ መርጣችኋልና በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ” አላቸው። እነርሱም፣ “አዎን ምስክሮች ነን” ሲሉ መለሱ። ኢያሱም፣ “እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር መልሱ” አላቸው። ሕዝቡም ኢያሱን፣ “እኛ አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ እንታዘዝለታለንም” አሉት። በዚያን ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ የሚመሩበትንም ደንብና ሥርዐት እዚያው ሴኬም ሰጣቸው። ኢያሱም እነዚህን ቃሎች በእግዚአብሔር የሕግ መጽሐፍ ጻፋቸው፤ ትልቅ ድንጋይም ወስዶ በባሉጥ ዛፍ ሥር፣ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ስፍራ አጠገብ አቆመው። ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ፣ “እነሆ፤ ይህ ድንጋይ፣ እግዚአብሔር የተናገረንን ሁሉ ሰምቷል፣ በእኛም ይመሰክርብናል፤ እናንተም በአምላካችሁ ዘንድ እውነተኞች ሆናችሁ ባትገኙ ምስክር ይሆንባችኋል” አላቸው። ከዚያም ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ ወደየርስቱ እንዲሄድ አሰናበተ። ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ የነዌ ልጅ ኢያሱ በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ። በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በምትገኘው፣ ከገዓስ ተራራ በስተ ሰሜን ባለችው በራሱ ርስት በተምናሴራ ቀበሩት። ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ ከኢያሱም በኋላ በሕይወት በኖሩትና እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ሁሉ በሚያውቁት ሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን አመለኩ።
ኢያሱ 24:14-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፥ በፍጹምም በእውነተኛም ልብ አምልኩት፥ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፥ እግዚአብሔርንም አምልኩ። እግዚአብሔርንም ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን። ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ፦ እግዚአብሔርን ትተን ሌሎችን አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ፥ እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር ያወጣን፥ በዓይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ነውና። እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱ የተቀመጡትን አሞራውያን ከፊታችን አሳደደ፥ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና እግዚአብሔርን እናመልካለን። ኢያሱም ሕዝቡን፦ እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፥ መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም። እግዚአብሔርን ትታችሁ እንግዶችን አማልክት ብታመልኩ፥ መልካም ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፥ ያጠፋችሁማል አላቸው። ሕዝቡም ኢያሱን፦ እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን አሉት። ኢያሱም ሕዝቡን፦ እንድታመልኩት እናንተ እግዚአብሔርን እንደ መረጣችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ አላቸው፥ እነርሱም፦ ምስክሮች ነን አሉ። እርሱም፦ አሁን እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን እንግዶች አማልክት አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አዘንብሉ አላቸው። ሕዝቡም ኢያሱን፦ አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፥ ድምፁንም እንሰማለን አሉት። በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ በሴኬምም ሥርዓትና ፍርድ አደረገላቸው። ኢያሱም ይህን ቃል ሁሉ በእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ጻፈ፥ ታላቁንም ድንጋይ ወስዶ በእግዚአብሔር መቅደስ አጠገብ ከነበረችው ከአድባሩ ዛፍ በታች አቆመው። ኢያሱም ለሕዝቡ፦ እነሆ፥ የተናገረንን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ሰምቶአልና ይህ ድንጋይ ይመሰክርብናል፥ እንግዲህ አምላካችሁን እንዳትክዱ ይህ ምስክር ይሆንባችኋል አላቸው። ኢያሱም ሕዝቡን በእያንዳንዱ ወደ ርስቱ ሰደደ። እንዲህም ሆነ፥ ከዚህ ነገር በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ አሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ። በተራራማው በኤፍሬም አገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ዳርቻ በተምናሴራ ቀበሩት። ኢያሱ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ከኢያሱም በኋላ በነበሩት ለእስራኤልም ያደረገውን የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ ባወቁት በሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ፥ እስራኤል እግዚአብሔርን አመለኩ።
ኢያሱ 24:14-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢያሱ ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔርን አክብሩት፤ በፍጹም ቅንነትና በታማኝነት አገልግሉት፤ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶና በግብጽ ይሰግዱላቸው የነበሩትን ባዕዳን አማልክት አስወግዳችሁ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ፤ እርሱን ማምለክ መልካም መስሎ ካልታያችሁ ግን የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ በነበሩበት ጊዜ ያመልኩአቸው የነበሩትን ወይም አሁን በምድራቸው የምትኖሩባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደሆን የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤተሰቤ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ሕዝቡም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “እግዚአብሔርን ትተን ሌሎች ባዕዳን አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ! አምላካችን እግዚአብሔር አባቶቻችንንና እኛን ከግብጽ ባርነት አውጥቶናል፤ ያደረገውን ተአምራት ሁሉ አይተናል፤ ሕዝቦችን ሁሉ አልፈን በመጣንበት ጊዜ በሰላም ጠብቆናል፤ እግዚአብሔር ሕዝቦችን እንዲሁም በምድሪቱ የሚኖሩትን አሞራውያንን ሁሉ ከፊታችን አባሮልናል፤ ስለዚህም እርሱ አምላካችን ስለ ሆነ እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ኢያሱም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ቅዱስና ቀናተኛ አምላክ ስለ ሆነ፥ እናንተ እርሱን ማገልገል አትችሉም፤ የምትሠሩትን ዐመፅና ኃጢአት ሁሉ ይቅር አይልም፤ እርሱን ትታችሁ ባዕዳን አማልክትን ብታመልኩ፥ ደግ ያደረገላችሁ ቢሆንም እንኳ ተመልሶ እርሱ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፤ ያጠፋችሁማል።” ሕዝቡም ለኢያሱ “ይህ ከቶ አይደረግም! እኛ እግዚአብሔርን እናመልካለን” አሉት። ኢያሱም “እንግዲህ እግዚአብሔርን ለማምለክ ስለ መምረጣችሁ ራሳችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ” ሲል ነገራቸው። እነርሱም “አዎ፤ ምስክሮች ነን፤” አሉ። እርሱም “እንግዲያውስ በመካከላችሁ የሚገኙትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አድርጉ” አላቸው። ከዚህም በኋላ ሕዝቡ ኢያሱን “እኛ አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፥ ትእዛዞችንም እንፈጽማለን” አሉት። በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን ገባ፤ በዚያም በሴኬም የሚመሩበትን ሕግና ሥርዓት ሰጣቸው፤ ኢያሱም እነዚህን ትእዛዞች በእግዚአብሔር የሕግ መጽሐፍ ጻፈ፤ ከዚያም በኋላ አንድ ትልቅ ድንጋይ ወስዶ በእግዚአብሔር መቅደስ አጠገብ በሚገኘው የወርካ ዛፍ ሥር አቆመው፤ ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር የነገረንን ቃል ሁሉ ስለ ሰማ ይህ ድንጋይ በእኛ ላይ ምስክር ነው፤ ስለዚህም አምላካችሁን ብትክዱ በእናንተ ላይ ምስክር ይሆንባችኋል።” ከዚህ በኋላ ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ አሰናበተ፤ እያንዳንዱም ወደየርስት ይዞታው ተመልሶ ሄደ። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ በአንድ መቶ ዐሥር ዓመት ዕድሜው ሞተ። እስራኤላውያንም ከጋዓሽ ተራራ በስተሰሜን በኩል በምትገኘው በኮረብታማይቱ በኤፍሬም አገር የራሱ የኢያሱ ርስት በሆነችው በቲምናትሴራሕ ቀበሩት። ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ሁሉ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን አመለኩ፤ ከእርሱም ሞት በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ድንቅ ነገር ሁሉ በዐይናቸው ያዩት ሽማግሌዎች እስከ ኖሩበት ዘመን ድረስ እርሱኑ በማምለክ ኖሩ።
ኢያሱ 24:14-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“እንግዲህ አሁን ጌታን ፍሩ፥ በፍጹም ቅንነትና ታማኝነት አገልግሉት፤ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ በግብጽም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፥ ጌታንም አምልኩ። ጌታንም ማገልገል ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያገለገሉአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታገለግሉ እንደሆነ፥ የምታገለግሉትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን ጌታን እናገለግላለን።” ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ፦ “ጌታን ትተን ሌሎችን አማልክትን ማገልገል ከእኛ ይራቅ፤ እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብጽ ምድር ያወጣን፥ በዓይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ ጌታ አምላካችን ነውና። ጌታ አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱ የተቀመጡትን አሞራውያን ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና ጌታን እናገለግላለን።” ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና ጌታን ማገልገል አትችሉም፤ መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም። ጌታን ትታችሁ እንግዶችን አማልክት ብታመልኩ፥ መልካም ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፥ ያጠፋችኋልም።” ሕዝቡም ኢያሱን፦ “እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ጌታን እናገለግላለን” አሉት። ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “እንድታገለግሉት እናንተ ጌታን እንደ መረጣችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ፤” እነርሱም፦ “ምስክሮች ነን” አሉ። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “አሁን እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን እንግዶች አማልክት አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ጌታ አዘንብሉ።” ሕዝቡም ኢያሱን፦ “ጌታ አምላካችንን እናገለግላለን፥ ድምፁንም እንሰማለን” አሉት። በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ በሴኬምም ሥርዓትና ፍርድ አደረገላቸው። ኢያሱም እነዚህን ቃላት በጌታ ሕግ መጽሐፍ ጻፈ፤ ታላቁንም ድንጋይ ወስዶ በጌታ መቅደስ አጠገብ ከነበረችው ከአድባሩ ዛፍ በታች አቆመው። ኢያሱም ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ የተናገረንን የጌታን ቃል ሁሉ ሰምቶአልና ይህ ድንጋይ ይመሰክርብናል፤ እንግዲህ አምላካችሁን እንዳትክዱ ይህ ምስክር ይሆንባችኋል።” ኢያሱም እያንዳንዱን ሰው ሕዝቡን ወደ ርስቱ እዲሄድ አደረገ። እንዲህም ሆነ፤ ከዚህ ነገር በኋላ የጌታ ባርያ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ። በተራራማው በኤፍሬም አገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ግዛት በተምና-ሴራ ቀበሩት። ኢያሱ በኖረበት ዘመን ሁሉ፥ ከኢያሱም በኋላ በነበሩት ለእስራኤልም ያደረገውን የጌታን ሥራ ሁሉ ባወቁት በሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ፥ እስራኤል ጌታን አገለገሉ።