የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዮናስ 2

2
የዮናስ ጸሎት
1ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ እንዲህ ሲል ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤
2“እግዚአብሔር ሆይ! ተጨንቄ ሳለሁ ወደ አንተ ተጣራሁ፤
አንተም መለስክልኝ፤
ርዳታህን ለማግኘት ጥልቅ ከሆነው ከሙታን ዓለም
ወደ አንተ ጮኽኩ፤
አንተም ሰማኸኝ።
3ጥልቅ ወደ ሆነው ወደ ባሕር መሠረት ጣልከኝ፤
በዙሪያዬም ውሃ ከበበኝ፤
ማዕበልህና ሞገድህ በላዬ ላይ አለፉ።
4እኔ ከፊትህ የጠፋሁ ነኝ፤
ይሁን እንጂ ቅዱስ መቅደስህን እንደገና አያለሁ።
5ውሃ እስከ አንገቴ ድረስ አጠለቀኝ፤
ባሕርም ፈጽሞ አሰጠመኝ፤
በባሕር ውስጥም የበቀለው ሣር ቅጠል በራሴ ላይ ተጠመጠመብኝ።
6ወደ ተራራዎች ሥር ወረድኩ፤
ከዚያ በታች ባለው ምድርም ውስጥ
ለዘለዓለም ሊዘጋብኝ ነበር፤
አንተ ግን እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ!
እኔን ከጥልቁ ውሃ አውጥተህ ሕይወቴን ታድናለህ።
7ሕይወቴ እየተዳከመ በሄደ ጊዜ
እግዚአብሔርን አስታወስኩ፤
ወደ አንተ ወደ አምላኬ ጸለይኩ፤
ጸሎቴም ወደ ቤተ መቅደስህ ወደ አንተ መጣ።
8የሐሰት አማልክትን የተከተሉ ሁሉ፥
ለአንተ ያላቸውን ታማኝነት ትተዋል።
9ደኅንነት ከእግዚአብሔር ነው፤
ስለዚህ ከምስጋና መዝሙር ጋር መሥዋዕትን ለአንተ አቀርባለሁ፤
የተሳልኩትንም እሰጣለሁ።”
10ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ዓሣው ዮናስን በደረቅ ምድር ላይ ተፋው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ