ትንቢተ ዮናስ 1
1
የዮናስ አለመታዘዝ
1እግዚአብሔር ለአሚታይ ልጅ ለዮናስ የገለጠለት የትንቢት ቃል ይህ ነው፦ #2ነገ. 14፥25። 2“ተነሥተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ እኔ የሕዝብዋን ክፋት ተመልክቼአለሁ። ድምፅህንም ከፍ አድርገህ እርስዋን በመገሠጽ ተናገር።” 3ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ለመኰብለል አስቦ ወደ ተርሴስ ለመሄድ ተነሣ፤ ወደ ኢዮጴም ወርዶ ከዚያ ወደ ተርሴስ የምትጓዝ መርከብ አገኘ፤ ለጒዞ የሚያስፈልገውንም ዋጋ ከከፈለ በኋላ ወደ መርከቢቱ ገባ፤ ሐሳቡም ከእግዚአብሔር ለመሸሽ ነበር።
4እግዚአብሔር ግን በባሕሩ ላይ ከባድ ነፋስን አስነሣ፤ በባሕሩም ላይ የተቀሰቀሰው ማዕበል ብርቱ ከመሆኑ የተነሣ መርከቢቱ ልትሰበር ተቃረበች፤ 5መርከበኞቹም እጅግ ስለ ፈሩ እያንዳንዱ ወደ አምላኩ ጮኸ፤ የመርከቢቱን ክብደት ለመቀነስ አስበው በውስጥዋ የነበረውን ዕቃ እያወጡ ወደ ባሕር ጣሉ፤ ዮናስ ግን በመርከቢቱ ታችኛ ክፍል ወርዶ በመተኛቱ በከባድ እንቅልፍ ላይ ነበር።
6የመርከብ አዛዡም ወደ እርሱ ቀርቦ “እንዴት ትተኛለህ? ኧረ እባክህ ተነሥና ወደ አምላክህ ጸልይ፤ ምናልባት ራርቶልን ሕይወታችንን ያድን ይሆናል” አለው።
7በመርከቢቱ ውስጥ የነበሩትም ሁሉ እርስ በርሳቸው “በዚህ አደጋ ላይ እንድንወድቅ ምክንያት የሆነው ማን እንደ ሆነ ለማወቅ ኑ ዕጣ እንጣጣል” ተባባሉ። ዕጣም ተጣጣሉ፤ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወጣ። 8ስለዚህ ዮናስን “እስቲ ንገረን! ይህ ሁሉ አደጋ የመጣብን በማን ምክንያት ይመስልሃል? ለመሆኑ ሥራህ ምንድን ነው? ከወዴት መጣህ? አገርህስ የት ነው? የየትኛው ሕዝብ ወገን ነህ?” አሉት።
9ዮናስም “እኔ ዕብራዊ ነኝ፤ የብስንና ባሕርን የፈጠረውን የሰማይ አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ” ሲል መለሰላቸው። 10አስቀድሞ በነገራቸው መሠረት ዮናስ ከእግዚአብሔር ፊት የኰበለለ መሆኑን ዐወቁ፤ ስለዚህም በጣም ፈርተው “ይህን ያደረግኸው ለምንድን ነው?” አሉት። 11የባሕሩም ማዕበል እየበረታ በመሄዱ መርከበኞቹ “ይህ ማዕበል ጸጥ እንዲል በአንተ ላይ ምን ብናደርግ ይሻላል?” ሲሉ ጠየቁት።
12ዮናስም “ይህ ማዕበል በእናንተ ላይ የመጣው በእኔ በደል ምክንያት እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ እኔን አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፤ ማዕበሉም ጸጥ ይልላችኋል” አላቸው።
13መርከበኞቹ ግን ባላቸው ኀይል ሁሉ እየቀዘፉ መርከቢቱን ወደ ዳር ለማድረስ ሞከሩ፤ ሆኖም ማዕበሉ እጅግ በርትቶ ስለ ነበር ይህን ማድረግ አልቻሉም። 14ስለዚህ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! የዚህ ሰው ሕይወት እንዲጠፋ ብናደርግ አታጥፋን፤ አንተ የፈቀድከውን ስላደረግህ ንጹሕ ደም እንዳፈሰስን አድርገህ አትቊጠርብን!” በማለት ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 15ከዚህ በኋላ ዮናስን አንሥተው ወደ ባሕር ጣሉት፤ የባሕሩም ማዕበል ጸጥ አለ። 16በዚህም ሁኔታ መርከበኞቹ እግዚአብሔርን እጅግ ስለ ፈሩ መሥዋዕት አቀረቡ፤ ስእለትንም ተሳሉ።
17አንድ ትልቅ ዓሣ ዮናስን እንዲውጥ ከእግዚአብሔር ታዘዘ፤ ስለዚህም ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ኖረ። #ማቴ. 12፥40።
Currently Selected:
ትንቢተ ዮናስ 1: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997