ትንቢተ ኢዩኤል 2
2
አንበጦች የጌታን ቀን መምጣት ማመልከታቸው
1በጽዮን መለከት ንፉ! በተቀደሰው ተራራውም
ላይ የእሪታ ድምፅ አሰሙ!
የጌታ ቀን መምጫ ስለ ተቃረበ
በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ።
2ያ ቀን የጨለማና የጭጋግ ቀን፥
የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው፤
የጧት ፀሐይ ወገግታ በተራሮች ላይ እንደሚያንሰራፋ፥
ታላቅና ኀያል የአንበጣ መንጋ በየቦታው ይንሰራፋል።
ይህን የሚመስል ነገር ከዚህ በፊት አልታየም፤
ከእንግዲህ ወዲህም ምን ጊዜም ቢሆን አይታይም።
3እነርሱ በፊታቸው የሚገኘውን ተክል ሁሉ እንደ እሳት ይበላሉ፤
እንደ ነበልባልም ያቃጥላሉ።
ገና ያልደረሱበት፥ በፊታቸው ያለው ምድር፥
እንደ ዔደን የአትክልት ቦታ የለመለመ ነው፤
እነርሱ ያለፉበት ምድር ግን
የወደመ በረሓ ይሆናል፤
ከእነርሱ የሚያመልጥ ምንም ነገር አይገኝም።
4መልካቸው ፈረስ ይመስላል፤
ግልቢያቸውም እንደ ጦር ፈረስ ነው።
5እንደ ሠረገላ ድምፅ እያሰሙ
በተራሮች ጫፍ ላይ ይዘላሉ፤
ገለባን እንደሚያቃጥል እሳትም፥
ሁሉን ነገር ያቃጥላሉ፤
ለጦርነት እንደ ተዘጋጀ ብርቱ ሠራዊት በሰልፍ ይተማሉ። #ራዕ. 9፥7-9።
6እነርሱን በሚያዩበት ጊዜ ሕዝቦች ይርበደበዳሉ፤
የሰውም ሁሉ ፊት በፍርሃት ይገረጣል።
7እንደ ጦረኞች ይጋፈጣሉ፤
እንደ ተዋጊዎችም ቅጽርን ይዘላሉ፤
ሁሉም ቀጥ ብለው ወደ ፊት ይጓዛሉ፤
በማመንታት አቅጣጫቸውን አይለውጡም።
8አንዱ ከሌላው ጋር አይጋፋም፤
እያንዳንዱ መስመሩን አይለቅም፤
የጠላትን መሣሪያ ደምስሰው ያልፋሉ፤
ምንም የሚያግዳቸው የለም።
9ከተማውን ይወራሉ፤
በከተማውም ቅጽር ላይ ይሮጣሉ፤
እየዘለሉ በቤቶች ላይ ይወጣሉ፤
እንደ ሌባም በመስኮት ይገባሉ።
10በፊታቸው ምድር ትንቀጠቀጣለች፤
ሰማይም ይናወጣል፤
ፀሐይና ጨረቃም ይጨልማሉ፤
ከዋክብትም ብርሃን የማይሰጡ ይሆናሉ። #ራዕ. 8፥12።
11እግዚአብሔር እንደ ነጐድጓድ ያለ ድምፁን በሠራዊቱ ላይ ያሰማል፤
ሠራዊቱ ምንኛ ብዙ ነው!
ትእዛዙን የሚቀበሉ ከቊጥር በላይ ናቸው፤
በእርግጥም የእግዚአብሔር ቀን ታላቅ ነው፤
በጣም አስፈሪ ስለ ሆነ በዚያ ቀን ማን ችሎ ይቆማል? #ራዕ. 6፥17።
የንስሓ ጥሪ
12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “አሁንም ቢሆን
በጾም፥ በለቅሶና በሐዘን
በፍጹም ልባችሁ ወደ እኔ ተመለሱ።
13ሐዘናችሁን ለመግለጽ ልብሳችሁን መቅደድ ብቻ በቂ አይደለም፤
ይልቅስ ልባችሁንም በመስበር ንስሓ ግቡ”
እግዚአብሔር አምላካችሁ ቸር፥ መሐሪ፥ ለቊጣ የዘገየ፥
በዘለዓለማዊ ፍቅር የበለጸገና
ለቅጣት የዘገየ በመሆኑ
ወደ እርሱ ተመለሱ።
14ምናልባት እግዚአብሔር አምላካችሁ ቊጣውን መልሶ፥
በረከቱን ይሰጣችሁ ይሆናል፤
እናንተም በዚያን ጊዜ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር
የእህልና የመጠጥ ቊርባን ታቀርባላችሁ።
15በጽዮን ተራራ ላይ መለከት ንፉ!
ሕዝቡን ለመንፈሳዊ ስብሰባ ጥሩ!
ጾምንም ዐውጁ!
16ሕዝቡን ሁሉ በአንድነት ሰብስባችሁ፥
ለተቀደሰ ጉባኤ አዘጋጁ፤
ሽማግሌዎችን ጥሩ፤
ልጆችንና ጡት የሚጠቡ ሕፃናትን ጭምር ሰብስቡ፤
ሙሽራዎችም ሳይቀሩ ከጫጒላቸው ይውጡ።
17እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ካህናት፥
በመሠዊያውና በመተላለፊያው መካከል ሆነው ያልቅሱ፤
“ጌታ ሆይ! ለሕዝብህ ራራ፤
አሕዛብ አምላካችሁ የት አለ? በማለት
እንዲንቁንና እንዲዘባበቱብን አታድርግ” ይበሉ።
እግዚአብሔር ሕዝቡን መልሶ እንደሚያቋቊማቸው የሰጠው ተስፋ
18እግዚአብሔር ስለምድሪቱ ባለው ቅንአት፥
ለሕዝቡ ራራላቸው፤
19ስለዚህም እንዲህ አላቸው፦
“እነሆ እህል፥ የወይን ጠጅና የወይራ ዘይት
እስክትጠግቡ ድረስ እሰጣችኋለሁ፤
ከእንግዲህ ወዲያ አሕዛብ
መዘባበቻ እንዲያደርጉአችሁ አልፈቅድም።
20ከሰሜን የሚመጣባችሁን የአንበጣ መንጋ
ከእናንተ አርቅላችኋለሁ፤
ወደ በረሓና ወደ ምድረ በዳም አባርርላችኋለሁ፤
ግንባር ቀደም የሆኑትን ወደ ሙት ባሕር፥
በስተኋላ ያሉትን ወደ ሜዲቴራኒያን ባሕር እሰድላችኋለሁ፤
በዚያም በድናቸው ይከረፋል፤
በእርግጥ እኔ እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አድርጌላችኋለሁ።
21“ምድር ሆይ አትፍሪ፤
እግዚአብሔር ስላደረገልሽ ታላቅ ነገር ደስ ይበልሽ!
ሐሤትም አድርጊ።
22እናንተም የምድር እንስሶች አትፍሩ፤
የምትሰማሩባቸው መስኮች ለምልመዋል፤
ዛፎችም አፍርተዋል፤
የበለሱና የወይኑ ፍሬ እጅግ የበዛ ሆኖአል።
23“እናንተ የጽዮን ሕዝብ ሆይ!
በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤
ሐሤትም አድርጉ፤
እርሱ በትክክል ፈርዶ
እንደ ወትሮው በበጋና በክረምት ወራት
በቂ ዝናብ ሰጥቶአችኋል።
24አውድማዎች በእህል ምርት የተሞሉ ይሆናሉ፤
የወይን ጠጅና የወይራ ዘይትም
በመጥመቂያ ጒድጓዶች ሞልተው ይትረፈረፋሉ።
25ለዘመናት እንደ ትልቅ ሠራዊት የላክሁባችሁ እንደ ውሽንፍር የሚገርፉ አንበጦች፥
ኲብኲባዎች፥ ተምቾችና የሚርመሰመሱ አንበጦች
የፈጁባችሁን ሰብል እተካላችኋለሁ።
26ብዙ በልታችሁ ትጠግባላችሁ፤
ብዙ አስደናቂ ነገር ያደረግኹላችሁን
እኔን እግዚአብሔር አምላካችሁን ታመሰግናላችሁ፤
ሕዝቤ ከእንግዲህ ወዲህ ኀፍረት አይደርስባቸውም።
27ሕዝቤ ሆይ! እኔ በመካከላችሁ እንዳለሁ፥
አምላካችሁም እኔ ብቻ እንደ ሆንኩና
ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቃላችሁ፤
ሕዝቤ ከእንግዲህ ወዲህ ኀፍረት አይደርስባቸውም።”
የጌታ ቀን
28እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከዚህ በኋላ መንፈሴን
በሰው ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤
ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤
ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፤
ወጣቶቻችሁም ራእይ ያያሉ። #ሐ.ሥ. 2፥17-21።
29እንዲሁም በእነዚያ ቀኖች፥
በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቼ ላይ
መንፈሴን አፈሳለሁ።
30“በሰማይና በምድር፥ ድንቅ ነገሮችን አሳያለሁ፤
ደምና እሳት፥ የጢስ ዐምድም ይታያል።
31ታላቁና አስፈሪው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት
ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ደም ትመስላለች፤ #ማቴ. 24፥29፤ ማር. 13፥24-25፤ ሉቃ. 21፥25፤ ራዕ. 6፥12-13።
32የእግዚአብሔርንም ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፤
እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ከጽዮን ተራራና
ከኢየሩሳሌም መዳን ይገኛል፤
ከሚድኑትም መካከል እግዚአብሔር የጠራቸው ይገኙበታል።” #ሮም 10፥13።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢዩኤል 2: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997