መጽሐፈ ኢዮብ 9

9
ኢዮብ
1ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦
2“አዎ! እኔ ይህ እውነት መሆኑን ዐውቃለሁ፤
ነገር ግን ሰው በእግዚአብሔር ፊት፥
እንዴት ጻድቅ መሆን ይችላል? #ኢዮብ 4፥17።
3ከእርሱስ ጋር ማን ሊከራከር ይችላል?
እርሱ አንድ ሺህ ጥያቄዎች ቢጠይቅ
ከእነርሱ አንዱን እንኳ መመለስ የሚችል የለም።
4እግዚአብሔር ጠቢብና ኀያል ነው፤
ማነው እርሱን ተቋቊሞ ያልተሸነፈ?
5ሳይታሰብ በድንገት ተራራዎችን ያናውጣል፤
በቊጣውም ይገለባብጣቸዋል።
6እግዚአብሔር ምድርን ከቦታዋ ያንቀጠቅጣል፤
ምሰሶችዋንም ያነቃንቃል።
7ፀሐይ እንዳትወጣ ሊያደርግ ይችላል፤
ከዋክብትም እንዳያበሩ ያደርጋል።
8ማንም ሳያግዘው ሰማይን የዘረጋ እርሱ ነው፤
እርሱ በባሕር ሞገድ ላይ ይራመዳል።
9ድብ፥ ኦሪዮንና፥ ፕልያዲስ የተባሉትን ከዋክብት፥
እንዲሁም በደቡብ በኩል ያሉትን የከዋክብት
ክምችቶች በሰማይ ላይ ያኖራቸው እግዚአብሔር ነው። #ኢዮብ 38፥31፤ አሞጽ 5፥8።
10እርሱ የሚያደርጋቸውን ድንቅ ነገሮች
መርምረን ልናስተውል አንችልም፤
እርሱም የሚፈጽማቸውን ተአምራት
ልንቈጥራቸው አንችልም።
11“እግዚአብሔር በአጠገቤ ቢያልፍ አላየውም፤
ወደ እኔም ቢቀርብ ለይቼ አላውቀውም፤
12የፈለገውን ቢወስድ ማንም አይከለክለውም፤
‘ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?’ ብሎ ሊጠይቀው
የሚደፍርም የለም።
13እግዚአብሔር ከቊጣው አይመለስም፤
ረዓብ የተባለው የባሕር አውሬ ረዳቶች እንኳ
በእግሩ ሥር ይንበረከካሉ።
14ታዲያ፥ እኔ ለእርሱ መልስ መስጠት እንዴት እችላለሁ?
ከእርሱ ጋር ለመከራከርስ ምን ቃላት አገኛለሁ?
15ንጹሕ ሆኜ ብገኝ እንኳ፥
ፈራጁ አምላክ እንዲምረኝ እለምነዋለሁ እንጂ
መልስ ልሰጠው አልደፍርም።
16የእርሱን ስም ብጠራና መልስ ቢሰጠኝም እንኳ
አቤቱታዬን ያዳምጣል ብዬ አላምንም።
17በዐውሎ ነፋስ ያደቀኛል
ያለ ምክንያትም ቊስሌን ያበዛል።
18ትንፋሽ እስካገኝ እንኳ ፋታ አይሰጠኝም፤
ሕይወቴን በሥቃይ ሞልቶታል።
19ባለኝ ኀይል ልታገለው እንዳልል፥
በኀይል እርሱን የሚቋቋም የለም፤
ተሟግቼ እረታዋለሁ እንዳልል፥
እርሱን ወደ ፍርድ ሸንጎ ሊያቀርበው የሚችል የለም።
20እኔ ንጹሕና እውነተኛ ነኝ፤ ነገር ግን አነጋገሬ በደለኛ ያደርገኛል፤
የምናገራቸው ንግግሮች ሁሉ ይፈርዱብኛል።
21ምንም እንኳ ፍጹም ብሆን
ስለ ራሴ አላስብም
ሕይወቴንም እጸየፈዋልሁ።
22እግዚአብሔር ፍጹሙንና በደለኛውን ስለሚያጠፋ
ምንም ልዩነት የለም
ያልሁት ስለዚህ ነው።
23በአደጋ ሰው ሲቀሠፍ
እርሱ በንጹሕ ሰው ችግር ይሳለቃል።
24ምድር በክፉ ሰዎች እጅ ተላልፋ ስትሰጥ
እርሱ የዳኞችን ዐይን ይሸፍናል፤
ይህን ያደረገ እግዚአብሔር ካልሆነ
ታዲያ፥ ማነው?
25“የዕድሜዬ ቀኖች ከሯጭ ይልቅ የፈጠኑ ናቸው
ምንም ደስታ ሳላይ ያልፋሉ።
26እነርሱም ከደንገል እንደ ተሠራ ታንኳ ይሮጣሉ፤
እንደ ነጣቂ ንስርም ይፈጥናሉ።
27ሮሮዬን ልርሳ፥
ፊቴንም ማጥቈር ትቼ ፈገግታ ላሳይ ብል፥
28እግዚአብሔር ንጹሕ አድርጎ እንደማይቈጥረኝ ስለማውቅ፥
መከራና ሥቃይ ይመጣብኛል ብዬ እፈራለሁ።
29እንግዲህ በደለኛ ሆኜ ከተቈጠርኩ፥
በከንቱ መድከሜ ለምንድን ነው?
30ሰውነቴን በሳሙና ባጥብ፥
እጄንም በእንዶድ ባጸዳ
31ይህም ሁሉ ሆኖ
አንተ ወደ አዘቅት ትጥለኛለህ፤
የገዛ ልብሴ እንኳ ይጸየፈኛል።
32እርሱ እንደ እኔ ሰው ስላልሆነ፥
ወደ ፍርድ ሸንጎ ሄደን፥
እንፋረድ ልለው አልችልም።
33-34ከጀርባዬ እግዚአብሔር በትሩን እንዲያነሣና
ግርማውም እንዳያስፈራኝ እጁን በሁለታችን ላይ
የሚያኖር ዳኛ በመካከላችን ምነው በተገኘ!
35እኔ ሰዎች እንደሚያስቡኝ ስላልሆንኩ
እርሱን ሳልፈራው በተናገርኩት ነበር።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ