መጽሐፈ ኢዮብ 4

4
የመጀመሪያው ውይይት
(4፥1—14፥22)
ኤሊፋዝ
1የቴማን አገር ሰው የሆነው ኤሊፋዝ እንዲህ ሲል መለሰ፦
2“ኢዮብ ሆይ! አንድ ሰው ደፍሮ ቢናገርህ
በትዕግሥት ታዳምጣለህን?
ነገር ግን ከመናገር ማን ይቈጠባል?
3ብዙ ሰዎችን አስተምረሃል፤
የደከሙትንም እጆች አበርትተሃል።
4ቃሎችህ የሚሰናከሉትን ይደግፉ ነበር፤
የሚብረከረኩትንም ጒልበቶች ታበረታ ነበር።
5አሁን ግን ችግር ስለ መጣብህ
ተስፋ ቢስ ሆነሃል፤
ችግሩም ስለ በረታብህ
ተስፋ ቈርጠሃል።
6አምላክህን መፍራትህ መተማመኛህ፥
ትክክለኛ መንገዶችህም፥
ተስፋህ አይደለምን?
7ንጹሕ ሰው ሆኖ መከራ የደረሰበት፥
ቀጥተኛ ሰው ሆኖ ሳለ የተደመሰሰ
እንዳለ እስቲ አስብ።
8እኔ እንዳስተዋልኩት
ክፋትን የሚያርሱና መከራን የሚዘሩ
ያንኑ ይሰበስባሉ።
9በእግዚአብሔር እስትንፋስ ይጠፋሉ፤
በቊጣውም ማዕበል ይደመሰሳሉ።
10ክፉዎች እንደ አንበሳ ያገሣሉ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ይጮኻሉ፤
እግዚአብሔር ግን ጥርሳቸውን ይሰባብራል።
11አንበሳ አድኖ የሚበላውን ሲያጣ እንደሚሞት እነርሱም ይሞታሉ፤
የአንበሳይቱም ደቦሎች እንደሚበተኑ የእነርሱም ልጆች ይበተናሉ፤
12“ከዕለታት አንድ ቀን ምሥጢራዊ መልእክት ወደ እኔ መጣ፤
ይህንንም መልእክት በሹክሹክታ ሰማሁት።
13ሰዎች ከባድ እንቅልፍ በሚይዛቸውና
በሚያስጨንቅ የሌሊት ቅዠት ጊዜ፥ #ኢዮብ 33፥15።
14ፍርሀትና መርበድበድ ይዞኝ፥
አጥንቶቼ ሁሉ እንዲንቀጠቀጡ አደረገ።
15የነፋስ ሽውታ በፊቴ ላይ አለፈ፤
ከድንጋጤ የተነሣ ጠጒሬ ተንጨፍርሮ ቆመ።
16በዚያም አንድ ነገር ቆሞ አየሁ፤
ትኲር ብዬ ብመለከትም
ምን እንደ ሆነ ለማወቅ አልቻልኩም።
ከዚያ በኋላ ጸጥ ካለው ስፍራ
እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ፦
17‘በእግዚአብሔር ፊት
ጻድቅ ሆኖ ሊገኝ የሚችል ሰው አለን?
ወይስ በፈጣሪው ፊት
ንጹሕ የሚሆን ሰው ይገኛልን?
18እግዚአብሔር በአገልጋዮቹ የማይተማመንባቸው ከሆነ፥
በመላእክቱ እንኳ ስሕተት የሚያገኝባቸው ከሆነ፥
19ታዲያ፥ ምስጥ ሳይበላቸው የሚፈርሱ
መሠረታቸው ዐፈር በሆነና
ከሸክላ በተሠራ ቤት ውስጥ በሚኖሩትማ ላይ እንዴት ይተማመንባቸዋል?
20በጠዋትና በማታ መካከል ይሰባበራሉ፤
ሳይታወቅ ለዘለዓለም ይጠፋሉ።
21ካስማው እንደ ተነቀለ ድንኳን
ያለ ጥበብ ይሞታሉ።’ ”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ