መጽሐፈ ኢዮብ 3:1-10

መጽሐፈ ኢዮብ 3:1-10 አማ05

ከዚህ በኋላ ኢዮብ መናገር ጀመረ፤ የተወለደበትን ቀን እንዲህ ሲል ረገመ፦ “የተፀነስኩበት ሌሊት፥ የተወለድኩበትም ቀን የተረገመ ይሁን! ያ ቀን ወደ ጨለማ ይለወጥ፤ የሰማይ አምላክ አያስበው፤ ብርሃን ከቶ አይታይበት። በጭጋግና በድቅድቅ ጨለማ የተሸፈነ ይሁን፤ ደመና ረቦበት ጨለማ ብርሃኑን ይዋጠው፤ ያን ሌሊት ድቅድቅ ጨለማ ይሸፍነው፤ ከዓመቱ ቀኖች ጋር አይቈጠር፤ ከወሮቹም ውስጥ ገብቶ አይታሰብ። ያ ሌሊት ባዶ ይሁን፤ የደስታም ድምፅ አይሰማበት። ሌዋታንን መቀስቀስ የሚችሉና ቀኖችን የሚረግሙ አስማተኞች ያን ቀን ይርገሙት። የዚያ ሌሊት አጥቢያ ኮከቦች ይጨልሙ፤ የብርሃን ተስፋ አይገኝበት፤ የንጋትም ጮራ አይፈንጥቅበት። ችግርን ከዐይኖቼ ለመሸሸግ የማሕፀን በሮችን በእኔ ላይ ስላልዘጋ ያ ቀን የተረገመ ይሁን።