የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 3

3
ኢዮብ የተወለደበትን ቀን መርገሙ
ኢዮብ
1ከዚህ በኋላ ኢዮብ መናገር ጀመረ፤ የተወለደበትን ቀን እንዲህ ሲል ረገመ፦
2-3“የተፀነስኩበት ሌሊት፥
የተወለድኩበትም ቀን የተረገመ ይሁን!
4ያ ቀን ወደ ጨለማ ይለወጥ፤
የሰማይ አምላክ አያስበው፤
ብርሃን ከቶ አይታይበት።
5በጭጋግና በድቅድቅ ጨለማ የተሸፈነ ይሁን፤
ደመና ረቦበት ጨለማ ብርሃኑን ይዋጠው፤
6ያን ሌሊት ድቅድቅ ጨለማ ይሸፍነው፤
ከዓመቱ ቀኖች ጋር አይቈጠር፤
ከወሮቹም ውስጥ ገብቶ አይታሰብ።
7ያ ሌሊት ባዶ ይሁን፤
የደስታም ድምፅ አይሰማበት።
8ሌዋታንን መቀስቀስ የሚችሉና ቀኖችን የሚረግሙ
አስማተኞች ያን ቀን ይርገሙት። #3፥8 ሌዋታን፦ ይህ በጥንት ዘመን አዞ የሚመስል ትልቅ አውሬ ነው።
9የዚያ ሌሊት አጥቢያ ኮከቦች ይጨልሙ፤
የብርሃን ተስፋ አይገኝበት፤
የንጋትም ጮራ አይፈንጥቅበት። #ኤር. 20፥14-18።
10ችግርን ከዐይኖቼ ለመሸሸግ
የማሕፀን በሮችን በእኔ ላይ ስላልዘጋ ያ ቀን የተረገመ ይሁን።
11“ምነው በእናቴ ማሕፀን ሳለሁ ውሃ ሆኜ በቀረሁ!
ከማሕፀን ስወጣስ ለምን አልጠፋሁም?
12ጒልበቶች እኔን ለመቀበል፥
ጡቶችም እኔን ያጠቡ ዘንድ ለምን ተገኙ?
13አሁን በሰላም በተጋደምኩ፥
አንቀላፍቼም ዕረፍት ባገኘሁ ነበር።
14አሁን ፈርሰው የሚታዩትን ለራሳቸው ከገነቡት
የምድር ነገሥታትና አማካሪዎች ጋር
አንቀላፍቼ ዕረፍት ባገኘሁ ነበር።
15ቤቶቻቸውን በወርቅና በብር ከሞሉ መሳፍንት ጋር አብሬ በተኛሁ ነበር፤
16ወይስ ለምን በመሬት ውስጥ እንደ ተቀበረ ጭንጋፍ
የቀንን ብርሃን ፈጽሞ እንዳላየ ሕፃን አልሆንኩም?
17በዚያ ክፉዎች አስቸጋሪነታቸው ይቀራል፤
በአድካሚ ሥራም የኖሩ ያርፋሉ።
18እስረኞች እንኳ ሰላም ያገኛሉ፤
የአሠሪዎቻቸውን የቊጣ ድምፅ ከመስማት ይድናሉ።
19ታናናሽና ታላላቅ ሰዎች በአንድነት ይገኛሉ፤
ባሪያዎችም በዚያ ከጌቶቻቸው ነጻ ይወጣሉ።
20“በጭንቀት ላይ ላሉ ብርሃን፥
ኑሮአቸው በመራራ ሐዘን ለተመላ
ሕይወት የሚሰጣቸው ለምንድነው?
21ሞትን ለሚናፍቁና፥
ከተደበቀ ሀብት ይልቅ ፈልገው የማያገኙት
ሕይወት የሚሰጣቸው ለምንድን ነው? #ራዕ. 9፥6።
22ወደ መቃብር ሲደርሱ ደስታ ለሚሰማቸው
ሕይወት የሚሰጣቸው ለምንድን ነው?
23መንገዱ ለተሰወረበትና
እግዚአብሔር ለዘጋበት ሰው
ብርሃን የሚሰጠው ለምንድን ነው?
24በምግብ ፈንታ እቃትታለሁ፤
ጩኸቴም እንደ ፈሳሽ ውሃ ነው።
25የፈራሁት ነገር መጥቶብኛል፤
የደነገጥሁበትም ነገር ደርሶብኛል።
26በውስጤ ሁከት ብቻ ስላለ፥
ሰላም፥ ጸጥታና ዕረፍት የለኝም።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ