የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 28

28
ጥበብን በማሞገስ የቀረበ ቅኔ
1“በእውነቱ ማዕድን ተቈፍሮ ብር የሚወጣበትና
ወርቅ የሚጣራበት ቦታ አለ።
2ብረት ከመሬት ይገኛል፤
መዳብም ከማዕድን ድንጋይ ቀልጦ ይወጣል።
3ሰዎች ጨለማን በማስወገድ
እስከ መሬቱ ጥልቀት ዘልቀው በመግባት
ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ውስጥ በመግባት
በድቅድቅ ጨለማው ውስጥ የማዕድን ድንጋይ ይፈልጋሉ።
4ሰው ከሚኖርበት ቦታ ርቀው፥
የሰው እግር ረግጦት ወደማያውቅ ስፍራ ይደርሳሉ።
እዚያም ጥልቅ ጒድጓድ ይቈፍራሉ፤
በገመድም ላይ እየተንጠለጠሉ፥ ከሰው ተለይተው ብቻቸውን ይሠራሉ።
5ምድር ለምግብ የሚሆን እህል ታበቅላለች።
ውስጥዋ በእሳት ቀልጦ ይገለባበጣል።
6ሰንፔር የተባለው ዕንቊ በድንጋዮችዋ ውስጥ ይገኛል፤
በዐፈርዋም ውስጥ ወርቅ ይገኛል።
7ወደ ማዕድኑ የሚወስደውን መንገድ ጭልፊት አያውቀውም፤
የአሞራም ዐይን አላየውም።
8ክፉ አውሬዎች ያን ቦታ አልረገጡትም፤
አንበሳም በዚያ በኩል አላለፈም።
9“ሰው መሬትን ሲቆፍር እጆቹን በሰላ ድንጋይ ላይ ያኖራል።
ተራራዎችንም ከመሠረታቸው ይገለብጣል።
10አለትን ሰንጥቆ መሿለኪያ መንገድ ያበጃል፤
ውድ የሆኑ የማዕድን ድንጋዮችንም ያገኛል።
11የወንዞቹን ምንጮች ይገድባል፤
በምድር ውስጥ የተደበቀውንም ሀብት ያገኛል።
12ታዲያ፥ ጥበብ ከየት ትገኛለች?
ማስተዋልስ ቦታዋ የት ነው?
13“ጥበብ ሕይወት ያላቸው ፍጥረቶች በሚኖሩባት ምድር አትገኝም፤
እውነተኛ ዋጋዋንም የሚያውቅ ሰው የለም።
14‘ውቅያኖስ በእኔ ውስጥ የለችም’ ይላል፤
‘ባሕሩም ከእኔ ጋር አይደለችም’ ይላል።
15ጥበብ በንጹሕ ወርቅ አትገዛም፤
ዋጋዋም በብር አይተመንም።
16ጥበብ ኦፊር ከሚባል ወርቅና፥ መረግድና
ሰንፔር ከሚባሉ ዕንቆች የከበረች ናት።
17ወርቅና የጠራ መስተዋት አይስተካከሉአትም፤
ከንጹሕ ወርቅ በተሠራ ጌጥም አትለወጥም።
18የከበሩ ዛጐልና አልማዝ ከጥበብ ጋር አይወዳደሩም።
የጥበብ ዋጋ ከሉልም በላይ ነው።
19‘ቶጳዝዮን’ የተባለ የኢትዮጵያ ዕንቊ አይተካከላትም፤
እጅግ በጠራ ወርቅም አትገመትም።
20ታዲያ፥ ጥበብ ከየት ትመጣለች?
ማስተዋልስ ከወዴት ትገኛለች?
21“ከሕያው ፍጡር ሁሉ የተሰወረች ናት፤
በሰማይ የሚበሩ ወፎች እንኳ ፈልገው አያገኙአትም።
22ጥፋትና ሞት
‘ስለ እርስዋ የምናውቀው፥
በወሬ ብቻ ነው’ ይላሉ።
23“ወደ ጥበብ የሚወስደውን መንገድና
መኖሪያ ቦታዋንም የሚያውቅ
እግዚአብሔር ብቻ ነው።
24እርሱም የምድርን ዳርቻ ሁሉ ይመለከታል፤
ከሰማይ በታች ያለውን ሁሉ ያያል።
25የነፋስን ኀይል በመሠረተ ጊዜ፥
የውቅያኖስን ውሃ በሰፈረ ጊዜ፥
26ዝናብና ለነጐድጓዳዊ መብረቅ ሥርዓትን በደነገገ ጊዜ፥
27እግዚአብሔር ጥበብን ተመለከታት
ገምግሞም አከበራት፤
መርምሮም አጸናት።
28“በዚያን ጊዜ ሰውን
‘እነሆ፥ ጥበብ ማለት እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤
ማስተዋልም ማለት ከክፋት መራቅ ነው’ ብሎታል።” #መዝ. 111፥10፤ ኢሳ. 1፥7፤ 9፥10።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ