የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 24

24
1“ሁሉን የሚችል አምላክ ፍርድ የሚሰጥበትን ጊዜ ለምን አይወስንም?
የእርሱ ታማኞችስ የፍርዱን ቃል
እስከ መቼ ይጠባበቃሉ?
2“ክፉ ሰዎች ድንበር ያፈርሳሉ።
በጎችንም እየሰረቁ ያሰማራሉ።
3የድኻ አደጉን አህያ ይቀማሉ፤
ባልዋ የሞተባትን ሴት ንብረት የሆነውንም በሬ፥ በመያዣ ስም ይወስዳሉ።
4ድኾችን በመጸየፍ ከየመንገዱ ያባርራሉ፤
ከፊታቸውም ሸሽተው እንዲደበቁ ያደርጋሉ።
5“ድኾች በበረሓ እንዳሉ የሜዳ አህዮች
ለልጆቻቸው ምግብ ለመፈለግ ወጥተው ይንከራተታሉ፤
6ተቀጥረውም የሌላ ሰው መከር ሰብሳቢ ይሆናሉ፤
የክፉ ሰው ንብረት በሆነ የወይን አትክልት ቦታ ይቃርማሉ።
7ሌሊቱን ሙሉ ራቁታቸውን ተኝተው ያድራሉ፤
ብርድ የሚከላከሉበትም ልብስ የላቸውም።
8በተራራ ላይ በሚዘንበው ዝናብ ሰውነታቸው ይረሰርሳል፤
መጠለያም አጥተው ቋጥኝ ተጠግተው ያድራሉ።
9“አባቱ የሞተበት ልጅ አገልጋይ እንዲሆናቸው የእናቱን ጡት አስጥለው ይነጥቃሉ፤
የችግረኛውንም ልጅ የዕዳ መያዣ አድርገው ይወስዳሉ።
10ድኾች ምንም ልብስ ሳይኖራቸው ራቁታቸውን ወደ ሥራ ይሰማራሉ።
በመከር ወራት ነዶ ተሸክመው እያጋዙ እነርሱ ይራባሉ።
11በክፉ ሰዎች የአትክልት ቦታ ከወይራ ፍሬ ዘይት ያወጣሉ፤
ከወይን ዘለላም የወይን ጠጅን ይጠምቃሉ፤
እነርሱ ግን ይጠማሉ።
12በየከተማው ለመሞት የሚያጣጥሩ ሰዎች ይቃትታሉ፤
የቈሰሉትም ሰዎች ርዳታ በመጠየቅ ይጮኻሉ።
እግዚአብሔር ግን በእነርሱ ላይ የተሠራውን ግፍ አልተመለከተም።
13“ብርሃንን የሚጠሉ ሰዎች አሉ፤
ብርሃንም ምን እንደ ሆነ ስለማያውቁ የብርሃንን መንገድ አይከተሉም።
14ነፍሰ ገዳይ ገና ሳይነጋ በማለዳ ተነሥቶ፥ ድኾችንና ችግረኞችን ይገድላል፤
በሌሊትም ለስርቆት ይሰማራል።
15አመንዝራ ሰው የቀኑን መምሸት ይጠባበቃል፤
ማንም ሰው እንዳያየው ፊቱን ይሸፍናል።
16ሌቦች በሌሊት ቤት ሰርስረው ለስርቆት ይገባሉ፤
ቀን ግን ተሸሽገው ይውላሉ።
ብርሃንንም ይጠላሉ።
17የጨለማ ሽብር ስለሚያስደስታቸው
ለሁሉም ድቅድቅ ጨለማ ማለዳቸው ነው።”
18“ሆኖም እነርሱ በውሃ ላይ እንደሚታይ ዐረፋ ለጥቂት ጊዜ ብቻ ይታያሉ፤
ርስታቸው የተረገመ ይሆናል፤
ወደ ወይን ተክል ቦታቸውም ማንም አይሄድም።
19በረዶ በሙቀት ቀልጦ ውሃውም በድርቅ እንደሚጠፋ፥
ኃጢአተኞችም ሞተው በሙታን ዓለም ይጠፋሉ።
20እናቶቻቸው ሁሉ ይረሱአቸዋል፤
ሥጋቸውንም ትል ይበላዋል፤
ክፉ ሰዎች አይታወሱም፤ ነገር ግን እንደ ዛፍ ይሰባበራሉ።
21ይህ ሁሉ የደረሰባቸው
እነርሱ ልጆች የሌላቸው መኻኖች ሴቶችን በመበዝበዛቸውና
ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች ምንም ርኅራኄ ባለማሳየታቸው ነው።
22ነገር ግን እግዚአብሔር በኀይሉ በሥልጣን ላይ ያሉትን ሰዎች ያስወግዳቸዋል።
ኑሮአቸው የተሳካ ቢመስልም እንኳ
የመኖር ዋስትና የላቸውም።
23እግዚአብሔር በሰላም እንዲኖሩ ቢፈቅድላቸውም እንኳ
የሚሄዱበትን መንገድ ሁሉ አተኲሮ ይመለከታል።
24ክፉ ሰዎች ለጥቂት ጊዜ ይበለጽጋሉ፤
ነገር ግን ወዲያውኑ እንደ አረም ጠውልገው ይጠፋሉ፤
እንደ እህልም ይታጨዳሉ።
25እንደዚህ አይደለም ከተባለ እኔ ሀሰተኛ መሆኔንና
የተናገርኩትም ቃል ትክክል አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ማነው?”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ