የዮሐንስ ወንጌል 5:25-47

የዮሐንስ ወንጌል 5:25-47 አማ05

እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ የሞቱ ሰዎች የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ ጊዜውም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም ሁሉ በሕይወት ይኖራሉ። አብ ራሱ የሕይወት ምንጭ እንዲሆን አድርጎታል። የሰው ልጅ በመሆኑም ፍርድ እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል። በዚህ ነገር አትደነቁ፤ በመቃብር ውስጥ ያሉት ሁሉ የእርሱን ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል። መልካም የሠሩ ከሞት ተነሥተው በሕይወት ይኖራሉ፤ ክፉ የሠሩ ግን ከሞት ተነሥተው ይፈረድባቸዋል። “እኔ በራሴ ሥልጣን ምንም ማድረግ አልችልም፤ ነገር ግን ከአብ የሰማሁትን እፈርዳለሁ፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ የራሴን ፈቃድ ስለማላደርግ ፍርዴ ትክክል ነው። “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክርነቴ እውነት አይደለም። ነገር ግን ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ አለ፤ እርሱም ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክርነት እውነት መሆኑን ዐውቃለሁ። እናንተ ወደ ዮሐንስ መልእክተኞች ልካችሁ ነበር፤ እርሱም ስለ እውነት መስክሮአል። ይህንንም ማለቴ እንድትድኑ ነው እንጂ እኔ የሰው ምስክርነት ስላስፈለገኝ አይደለም። ዮሐንስ እንደሚነድና እንደሚበራ መብራት ነበረ፤ እናንተም ለጥቂት ጊዜ በእርሱ ብርሃን ለመደሰት ፈለጋችሁ። እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የበለጠ ምስክር አለኝ፤ ምስክሬም አባቴ እንድሠራው የሰጠኝ ሥራ ነው፤ ይህም የምሠራው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራል። የላከኝም አብ፥ ራሱ ስለ እኔ መስክሮአል፤ እናንተ ግን ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፤ መልኩንም ከቶ አላያችሁም። እርሱ የላከውን ስለማታምኑ የእርሱ ቃል በእናንተ ዘንድ አይኖርም። እናንተ በቅዱሳት መጻሕፍት የዘለዓለምን ሕይወት የምታገኙ ስለሚመስላችሁ እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው። ይሁን እንጂ እናንተ ሕይወትን ለማግኘት ወደ እኔ መምጣት አትፈልጉም። “እኔ ክብርን ከሰው አልፈልግም። እናንተ ከልባችሁ እግዚአብሔርን የማታፈቅሩ መሆናችሁን ዐውቃለሁ። እኔ በአባቴ ስም መጣሁ፤ እናንተ ግን አልተቀበላችሁኝም፤ ሌላ በራሱ ስም ቢመጣ ግን ትቀበሉታላችሁ። እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብርን የምትፈልጉ ከአንዱ ከእግዚአብሔር የሚገኘውን ክብር ግን የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? እኔ በአባቴ ፊት የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ፥ ተስፋ የምታደርጉበት ሙሴ ነው። ሙሴን ብታምኑ ኖሮ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና እኔንም ባመናችሁ ነበር። እርሱ የጻፈውን ካላመናችሁ ግን የእኔን ቃል እንዴት ታምናላችሁ?”