እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቷል፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው ሁሉ፣ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና፤ ወልድ የሰው ልጅ ስለ ሆነም እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል። “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ። እኔ ብቻዬን ከራሴ ምንም ማድረግ አልችልም፤ የምፈርደው የምሰማውን ብቻ ነው፤ የላከኝን እንጂ የራሴን ፈቃድ ስለማልሻም ፍርዴ ትክክል ነው። “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር፣ ምስክርነቴ ተቀባይነት አይኖረውም። ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ አለ፤ እርሱ ስለ እኔ የሚሰጠውም ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ ዐውቃለሁ። “ወደ ዮሐንስ ልካችሁ ነበር፤ እርሱም ስለ እውነት መስክሯል፤ እኔ የሰው ምስክርነት የምቀበል አይደለሁም፤ ይህን የምናገረው ግን እናንተ እንድትድኑ ነው። ዮሐንስ እየነደደ ብርሃን የሚሰጥ መብራት ነበረ፤ እናንተም ለጥቂት ጊዜ በብርሃኑ ደስ ልትሠኙ ወደዳችሁ። “እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የላቀ ምስክር አለኝ፤ እንድፈጽመው አብ የሰጠኝ፣ እኔም የምሠራው ሥራ አብ እንደ ላከኝ ይመሰክራል። የላከኝ አብ ራሱ ስለ እኔ መስክሯል፤ እናንተም ከቶ ድምፁን አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፤ የላከውንም ስላላመናችሁ ቃሉ በእናንተ አይኖርም። በእነርሱ የዘላለም ሕይወትን የምታገኙ እየመሰላችሁ፣ መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ፤ እነዚሁ መጻሕፍት ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ እናንተ ግን፣ ሕይወት እንዲኖራችሁ ወደ እኔ መምጣት አትፈልጉም። “እኔ ከሰው ክብር አልቀበልም፤ ነገር ግን እናንተን ዐውቃችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርም ፍቅር በልባችሁ እንደሌለ ዐውቃለሁ። እኔ በአባቴ ስም መጥቼ አልተቀበላችሁኝም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ ግን ትቀበሉታላችሁ። እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትሰጣጡ፣ ነገር ግን ከአንዱ አምላክ የሚመጣውን ክብር የማትፈልጉ ከሆነ፣ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? “ከሳሻችሁ ተስፋ የጣላችሁበት ሙሴ እንጂ፣ እኔ በአብ ፊት የምከስሳችሁ አይምሰላችሁ፤ ሙሴን ብታምኑ ኖሮ፣ እኔን ባመናችሁ ነበር፤ ምክንያቱም እርሱ የጻፈው ስለ እኔ ነው። እርሱ የጻፈውን ካላመናችሁ፣ እኔ የምናገረውን እንዴት ታምናላችሁ?”
ዮሐንስ 5 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 5
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 5:25-47
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች