የዮሐንስ ወንጌል 3:14-21

የዮሐንስ ወንጌል 3:14-21 አማ05

“ሙሴ በበረሓ እባብን ከፍ አድርጎ እንደ ሰቀለ እንዲሁም የሰው ልጅ ከፍ ብሎ ሊሰቀል ይገባዋል። ይህም የሚሆነው በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለምን ሕይወት እንዲያገኝ ነው። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ ስለ ወደደው አንድያ ልጁን ሰጠ። እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው፥ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም ላይ ለመፍረድ አይደለም። “በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ስላላመነ ቀድሞውኑ ተፈርዶበታል። “ፍርዱም ይህ ነው፦ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ። ክፉ ነገር የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ ክፉ ሥራውም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። እውነት የሆነውን ነገር የሚያደርግ ግን ወደ ብርሃን ይመጣል፤ ወደ ብርሃን የሚመጣውም ያደረገው ነገር በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት መሆኑ በግልጥ እንዲታይ ነው።”