የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ወንጌል 20:11-23

የዮሐንስ ወንጌል 20:11-23 አማ05

መግደላዊት ማርያም እያለቀሰች፥ ከመቃብሩ በስተውጭ ቆማ ነበር፤ እያለቀሰችም ጐንበስ ብላ ወደ መቃብሩ ውስጥ ተመለከተች። የኢየሱስ አስከሬን በነበረበት ስፍራ ነጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት አንዱ በራስጌ፥ አንዱ በግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም ማርያምን፥ “አንቺ ሴት! ለምን ታለቅሻለሽ?” አሉአት። እርስዋም “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳደረጉትም አላውቅም” አለች። ይህንንም ብላ ወደ ኋላዋ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስ መሆኑን ግን አላወቀችም። ኢየሱስ፥ “አንቺ ሴት ስለ ምን ታለቅሺአለሽ፤ ማንንስ ትፈልጊአለሽ?” አላት። እርስዋም አትክልተኛው መስሎአት፥ “ጌታ ሆይ! አንተ ወስደኸው እንደ ሆነ የት እንዳኖርከው እባክህ ንገረኝ፤ እኔ እወስደዋለሁ” አለችው። ኢየሱስም “ማርያም!” አላት። እርስዋም ወደ እርሱ ዞር ብላ በዕብራይስጥ ቋንቋ “ረቡኒ!” አለችው፤ ትርጓሜውም “መምህር ሆይ!” ማለት ነው። ኢየሱስ “ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሂጂና ‘እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፥ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ ብሎአል’ ብለሽ ንገሪያቸው” አላት። ስለዚህ መግደላዊት ማርያም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሄዳ ጌታን እንዳየችና እርሱም ምን እንዳላት ነገረቻቸው። በዚያው በሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እሑድ ማታ ደቀ መዛሙርቱ የአይሁድን ባለሥልጣኖች በመፍራት፥ በራፎቹን ዘግተው፥ በቤት ውስጥ ተሰብስበው ነበር፤ በሮቹ ተዘግተው ሳለ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ተሰበሰቡበት ቤት ገባ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። ይህንንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንደገና “ሰላም ለእናንተ ይሁን! አብ እኔን እንደ ላከኝ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው። ይህን ብሎ እፍ አለባቸውና “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ እናንተ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ብትሉ ይቅር ይባልላቸዋል፤ እናንተ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ባትሉ ግን፥ ይቅር አይባልላቸውም” አላቸው።