ዮሐንስ 20:11-23
ዮሐንስ 20:11-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ማርያም ግን ከመቃብሩ ውጭ ቆማ ታለቅስ ነበር፤ እያለቀሰችም መቃብሩን ለማየት ጐንበስ አለች። የኢየሱስ ሥጋ በነበረበት ቦታ፣ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት አንዱ በራስጌ ሌላው በግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ?” ብለው ጠየቋት። እርሷም፣ “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አላውቅም” አለች። ይህን ብላ ዘወር ስትል ኢየሱስ በዚያው ቆሞ አየች፤ ኢየሱስ መሆኑን ግን አላወቀችም። እርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊአለሽ?” አላት። እርሷም የአትክልቱ ቦታ ጠባቂ መስሏት፣ “ጌታዬ፤ አንተ ወስደኸው ከሆነ፣ እባክህ እንድወስደው፣ የት እንዳኖርኸው ንገረኝ” አለችው። ኢየሱስም፣ “ማርያም” አላት። እርሷም፣ ወደ እርሱ ዘወር ብላ በአራማይክ ቋንቋ፣ “ረቡኒ!” አለችው፤ ትርጕሙም “መምህር ሆይ” ማለት ነው። ኢየሱስም፣ “ገና ወደ አብ ስላላረግሁ፣ አትንኪኝ፤ ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፣ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ’ ብሏል ብለሽ ንገሪአቸው” አላት። መግደላዊት ማርያምም፣ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥታ፣ “ጌታን እኮ አየሁት!” አለች፤ እርሱ ያላትንም ነገረቻቸው። በዚያ ዕለት፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን በምሽት፣ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን በመፍራት በሮቹን ቈልፈው ተሰብስበው ሳለ፣ ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርትም ጌታን ባዩት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው። ኢየሱስም እንደ ገና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን! አብ እኔን እንደ ላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው። ይህን ካለ በኋላም፣ እፍ አለባቸውና እንዲህ አላቸው፤ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። የሰዎችን ኀጢአት ይቅር ብትሉ፣ ኀጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል፤ ኀጢአታቸውን ይቅር ባትሉ ግን፣ ይቅር አይባልላቸውም።”
ዮሐንስ 20:11-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስ ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም፦ “አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ?” አሉአት። እርስዋም፦ “ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም” አለቻቸው። ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም። ኢየሱስም፦ “አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ” አለችው። ኢየሱስም፦ “ማርያም” አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ፦ “ረቡኒ” አለችው፤ ትርጓሜውም፦ “መምህር ሆይ” ማለት ነው። ኢየሱስም፦ “ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፦ ‘እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ’ ብለሽ ንገሪአቸው” አላት። መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች። ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፦ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። ኢየሱስም ዳግመኛ፦ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ” አላቸው። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና፦ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል” አላቸው።
ዮሐንስ 20:11-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ማርያም ግን ከመቃብሩ በስተውጭ እያለቀሰች ቆማ ነበረ፤ እያለቀሰችም ወደ መቃብሩ ጐንበስ ብላ ተመለከተች። ሁለት መላእክትንም ነጭ ልብስ ለብሰው የጌታችን የኢየሱስ ሥጋ በነበረበት ቦታ አንዱ በራስጌ፥ አንዱም በግርጌ ተቀምጠው አየች። እነዚያ መላእክትም፥ “አንቺ ሴት፥ ምን ያስለቅስሻል?” አሉአት፤ እርስዋም፥ “ጌታዬን ከመቃብር ውስጥ ወስደውታል፤ ወዴትም እንደ ወሰዱት አላውቅም” አለቻቸው። ይህንም ተናግራ ወደ ኋላዋ መለስ ስትል ጌታችን ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ጌታችን ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም። ጌታችን ኢየሱስም፥ “አንቺ ሴት፥ ምን ያስለቅስሻል? ማንንስ ትሺያለሽ?” አላት፤ እርስዋ ግን የአትክልት ቦታ ጠባቂ መስሎአት፥ “ጌታዬ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆነ ሄጄ ወደ እኔ እንዳመጣውና ሽቱ እንድቀባው ወዴት እንደ አኖርኸው ንገረኝ” አለችው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ማርያም!” አላት፤ እርስዋም መለስ ብላ በዕብራይስጥ ቋንቋ፥ “ረቡኒ!” አለችው፤ ትርጓሜዉም “መምህር” ማለት ነው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “አትንኪኝ፤ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞች ሂጂና፦ ወደ አባቴ፥ ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬ፥ ወደ አምላካችሁም አርጋለሁ አለ ብለሽ ንገሪአቸው” አላት። ማርያም መግደላዊትም ሄደች፤ ጌታን እንደ አየች፥ ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረቻቸው። ያም ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ስለ ፈሩ ተሰብስበው የነበሩበት ቤት ደጁ ተቈልፎ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንና ጎኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ጌታችንን ባዩት ጊዜ ደስ አላቸው። ጌታችን ኢየሱስም ዳግመኛ እንዲህ አላቸው፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እኔን እንደ ላከኝ እንዲሁ እኔ እናንተን እልካችኋለሁ።” ይህንም ብሎ እፍ አለባቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኀጢኣታቸውን ይቅር ያላችሁላቸው ይሰረይላቸዋል፤ ይቅር ያላላችኋቸው ግን አይሰረይላቸውም።”
ዮሐንስ 20:11-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
መግደላዊት ማርያም እያለቀሰች፥ ከመቃብሩ በስተውጭ ቆማ ነበር፤ እያለቀሰችም ጐንበስ ብላ ወደ መቃብሩ ውስጥ ተመለከተች። የኢየሱስ አስከሬን በነበረበት ስፍራ ነጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት አንዱ በራስጌ፥ አንዱ በግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም ማርያምን፥ “አንቺ ሴት! ለምን ታለቅሻለሽ?” አሉአት። እርስዋም “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳደረጉትም አላውቅም” አለች። ይህንንም ብላ ወደ ኋላዋ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስ መሆኑን ግን አላወቀችም። ኢየሱስ፥ “አንቺ ሴት ስለ ምን ታለቅሺአለሽ፤ ማንንስ ትፈልጊአለሽ?” አላት። እርስዋም አትክልተኛው መስሎአት፥ “ጌታ ሆይ! አንተ ወስደኸው እንደ ሆነ የት እንዳኖርከው እባክህ ንገረኝ፤ እኔ እወስደዋለሁ” አለችው። ኢየሱስም “ማርያም!” አላት። እርስዋም ወደ እርሱ ዞር ብላ በዕብራይስጥ ቋንቋ “ረቡኒ!” አለችው፤ ትርጓሜውም “መምህር ሆይ!” ማለት ነው። ኢየሱስ “ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሂጂና ‘እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፥ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ ብሎአል’ ብለሽ ንገሪያቸው” አላት። ስለዚህ መግደላዊት ማርያም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሄዳ ጌታን እንዳየችና እርሱም ምን እንዳላት ነገረቻቸው። በዚያው በሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እሑድ ማታ ደቀ መዛሙርቱ የአይሁድን ባለሥልጣኖች በመፍራት፥ በራፎቹን ዘግተው፥ በቤት ውስጥ ተሰብስበው ነበር፤ በሮቹ ተዘግተው ሳለ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ተሰበሰቡበት ቤት ገባ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። ይህንንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንደገና “ሰላም ለእናንተ ይሁን! አብ እኔን እንደ ላከኝ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው። ይህን ብሎ እፍ አለባቸውና “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ እናንተ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ብትሉ ይቅር ይባልላቸዋል፤ እናንተ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ባትሉ ግን፥ ይቅር አይባልላቸውም” አላቸው።
ዮሐንስ 20:11-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። እያለቀሰችም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት ነጭ ልብስ የለበሱ መላእክትም፥ የኢየሱስን ሥጋ አስተኝተውበት በነበረበት ስፍራ፥ አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም “አንቺ ሴት! ስለምን ታለቅሻለሽ?” አሉአት። እርሷም “ጌታዬን ወስደውታል፤ ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም፤” አለቻቸው። ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ነገር ግን ኢየሱስ እንደሆነ አላወቀችም። ኢየሱስም “አንቺ ሴት! ስለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርሷም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት “ጌታ ሆይ! አንተ ወስደኸው እንደሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ፤ እኔም እወስደዋለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ማርያም!” አላት። እርሷ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ “ረቡኒ!” አለችው፤ ትርጓሜውም “መምህር ሆይ!” ማለት ነው። ኢየሱስም “ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ ‘እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ፤’ ብለሽ ንገሪአቸው፤” አላት። መግደላዊት ማርያም ሄደችና ጌታን እንዳየችው፥ ይህንንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች። በዚያው ከሳምንቱ የመጀመሪያው በሆነው ቀን፥ በመሸ ጊዜ፥ ደቀመዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ይህንንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። ኢየሱስም ዳግመኛ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ፤” አላቸው። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኀጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል፤” አላቸው።