የዮሐንስ ወንጌል 2:13-22

የዮሐንስ ወንጌል 2:13-22 አማ05

የአይሁድ ፋሲካ በዓል ቀርቦ ስለ ነበር ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ በቤተ መቅደስም በሬዎችን፥ በጎችንና ርግቦችን የሚሸጡትንና ገንዘብ ለዋጮችን ተቀምጠው ሲገበያዩ አገኘ። በዚህ ጊዜ የገመድ ጅራፍ አበጀና ሰዎችን ሁሉ፥ ከበጎችና ከበሬዎች ጋር ከቤተ መቅደስ አስወጣቸው፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፤ ጠረጴዛዎቻቸውንም ገለባበጠ። ርግብ የሚሸጡትንም ሰዎች “ይህን ሁሉ ወዲያ ውሰዱ! የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት!” አላቸው። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ “ስለ ቤትህ ያለኝ ቅናት እንደ እሳት አቃጠለኝ” ተብሎ እንደ ተጻፈ አስታወሱ። ከዚህ በኋላ የአይሁድ ባለሥልጣኖች ኢየሱስን፦ “አንተ ይህን ለማድረግ ሥልጣን እንዳለህ ምን ተአምር ታሳየናለህ?” አሉት። ኢየሱስም “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱትና እኔ በሦስት ቀን መልሼ እሠራዋለሁ” አላቸው። እነርሱም “ይህን ቤተ መቅደስ ለመሥራት አርባ ስድስት ዓመት ፈጅቶአል፤ ታዲያ አንተ በሦስት ቀን ውስጥ ትሠራዋለህን?” አሉት። ኢየሱስ ግን “ቤተ መቅደስ” ብሎ የተናገረው ስለ ሰውነቱ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ከሞት በተነሣ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ተናግሮ እንደ ነበረ አስታወሱ፤ በዚህ ምክንያት በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈውንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ።