የዮሐንስ ወንጌል 2
2
ኢየሱስ በቃና ዘገሊላ በሠርግ ግብዣ ላይ መገኘቱ
1በሦስተኛው ቀን፥ በገሊላ ምድር በምትገኘው ቃና በምትባል ከተማ ሠርግ ነበረ፤ የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች። 2ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሠርጉ ተጠርተው ነበር። 3በሠርጉ ግብዣ ላይ የወይን ጠጁ ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት ኢየሱስን፦ “የወይን ጠጅ እኮ አልቆባቸዋል!” አለችው። 4ኢየሱስም “እናቴ ሆይ! ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት።
5በዚያን ጊዜ እናቱ እዚያ ለነበሩት አገልጋዮች፦ “እርሱ የሚላችሁን አድርጉ” አለቻቸው።
6አይሁድ የመንጻት ሥርዓት ስለ ነበራቸው ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ነበሩ፤ እያንዳንዱ ጋን ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ውሃ ለመያዝ ይችል ነበር። 7ኢየሱስ አገልጋዮቹን “ጋኖቹን ውሃ ሙሉአቸው” አላቸው፤ እነርሱም እስከ አፋቸው ሞሉአቸው። 8ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አገልጋዮቹን፦ “በሉ አሁን ቀድታችሁ ለግብዣው ኀላፊ ስጡት” አላቸው፤ እነርሱም ወስደው ሰጡት። 9የግብዣው ኀላፊ ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ፥ ከየት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውሃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ ስለዚህ የግብዣው ኀላፊ፥ ሙሽራውን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ 10“ሰው ሁሉ አስቀድሞ የሚያቀርበው ጥሩውን የወይን ጠጅ ነው፤ ተጋባዦቹ ከጠጡ በኋላ መናኛውን ያቀርባል፤ አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቈየህ።”
11ኢየሱስ ይህን የተአምራት ሁሉ መጀመሪያ የሆነውን ተአምር በገሊላ ምድር በቃና ከተማ አደረገ፤ በዚህም ዐይነት ክብሩን ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።
12ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከእናቱና ከወንድሞቹ፥ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በዚያም ጥቂት ቀኖች ተቀመጡ። #ማቴ. 4፥13።
ኢየሱስ በቤተ መቅደስ የሚገበያዩትን ማስወጣቱ
(ማቴ. 21፥12-13፤ ማር. 11፥15-17፤ ሉቃ. 19፥45-46)
13የአይሁድ ፋሲካ በዓል ቀርቦ ስለ ነበር ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ #ዘፀ. 12፥1-27። 14በቤተ መቅደስም በሬዎችን፥ በጎችንና ርግቦችን የሚሸጡትንና ገንዘብ ለዋጮችን ተቀምጠው ሲገበያዩ አገኘ። 15በዚህ ጊዜ የገመድ ጅራፍ አበጀና ሰዎችን ሁሉ፥ ከበጎችና ከበሬዎች ጋር ከቤተ መቅደስ አስወጣቸው፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፤ ጠረጴዛዎቻቸውንም ገለባበጠ። 16ርግብ የሚሸጡትንም ሰዎች “ይህን ሁሉ ወዲያ ውሰዱ! የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት!” አላቸው። 17በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ “ስለ ቤትህ ያለኝ ቅናት እንደ እሳት አቃጠለኝ” ተብሎ እንደ ተጻፈ አስታወሱ። #መዝ. 69፥9።
18ከዚህ በኋላ የአይሁድ ባለሥልጣኖች ኢየሱስን፦ “አንተ ይህን ለማድረግ ሥልጣን እንዳለህ ምን ተአምር ታሳየናለህ?” አሉት።
19ኢየሱስም “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱትና እኔ በሦስት ቀን መልሼ እሠራዋለሁ” አላቸው። #ማቴ. 26፥61፤ 27፥40፤ ማር. 14፥58፤ 15፥29።
20እነርሱም “ይህን ቤተ መቅደስ ለመሥራት አርባ ስድስት ዓመት ፈጅቶአል፤ ታዲያ አንተ በሦስት ቀን ውስጥ ትሠራዋለህን?” አሉት።
21ኢየሱስ ግን “ቤተ መቅደስ” ብሎ የተናገረው ስለ ሰውነቱ ነበር። 22ስለዚህ ኢየሱስ ከሞት በተነሣ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ተናግሮ እንደ ነበረ አስታወሱ፤ በዚህ ምክንያት በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈውንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ።
23ኢየሱስ በፋሲካ በዓል ጊዜ በኢየሩሳሌም ሳለ ያደረጋቸውን ተአምራት በማየታቸው ብዙ ሰዎች በእርሱ አመኑ። 24ኢየሱስ ግን ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ስለ ነበር እነርሱን አላመናቸውም፤ 25እርሱ በሰው ልብ ያለውን ሁሉ ያውቅ ስለ ነበር ስለ ሰው ማንም እንዲነግረው አያስፈልገውም ነበር።
Currently Selected:
የዮሐንስ ወንጌል 2: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997