የዮሐንስ ወንጌል 19:31-42

የዮሐንስ ወንጌል 19:31-42 አማ05

ከዚህ በኋላ የአይሁድ ባለሥልጣኖች፥ የተሰቀሉትን ሰዎች ጭን ሰብረው፥ አስከሬናቸውን ከመስቀል እንዲያወርዱአቸው ጲላጦስን ለመኑት፤ ይህንንም ያደረጉበት ምክንያት የሰንበት ዝግጅት ቀን ስለ ነበረና ያ ሰንበትም ትልቅ በዓል ስለ ሆነ፥ በሰንበት ቀን ሥጋቸው በመስቀል ላይ እንዳይሆን ነበር። ስለዚህ ወታደሮቹ ሄደው፥ ከኢየሱስ ጋር የተሰቀሉትን ሰዎች ጭን ሰበሩ፤ ወደ ኢየሱስ በሄዱ ጊዜ ግን፥ እርሱ ቀደም ብሎ እንደ ሞተ አይተው፥ ጭኑን አልሰበሩም። ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ፥ ጐኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውኑ ከጐኑ ደምና ውሃ ወጣ። ይህን ያየ፥ እናንተ እንድታምኑ መሰከረ፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ የሚናገረውም እውነት እንደ ሆነ፥ እርሱ ያውቃል። ይህም የሆነው፥ “ከእርሱ አንድ አጥንት እንኳ አይሰበርም” የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው። ደግሞም በሌላው የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል “ያንን የወጉትን ያዩታል” ይላል። የአይሁድ ባለሥልጣኖችን በመፍራት በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስን አስከሬን ለመውሰድ ጲላጦስን ለመነ። ጲላጦስም ፈቀደለት። ስለዚህ ዮሴፍ ሄዶ አስከሬኑን ወሰደ። ከዚህ በፊት በሌሊት ወደ ኢየሱስ ሄዶ የነበረው ኒቆዲሞስም አንድ መቶ ነጥርየሚያኽል የከርቤና የሬት ቅልቅል ይዞ መጣ። ሁለቱ ሰዎች የኢየሱስን አስከሬን ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቶ ጋር በቀጭን ልብስ ከፈኑት። ኢየሱስ ተሰቅሎ በነበረበት ቦታ አንድ የአትክልት ስፍራ ነበረ፤ በዚያም የአትክልት ስፍራ ውስጥ ማንም ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር። የሰንበት ዝግጅት ቀን ስለ ነበረና መቃብሩም ቅርብ ስለ ነበረ የኢየሱስን አስከሬን እዚያ ቀበሩት።