ዮሐንስ 19:31-42

ዮሐንስ 19:31-42 NASV

ዕለቱ ለሰንበት መዘጋጃ ቀን ነበር። አይሁድ፣ የተሰቀሉት ሰዎች ሬሳ በሰንበት ቀን በመስቀል ላይ እንዳይውል ስለ ፈለጉና ያም የተለየ ሰንበት ስለ ነበር፣ የተሰቀሉት ሰዎች ጭናቸው ተሰብሮ በድናቸው እንዲወርድ ጲላጦስን ለመኑት። ስለዚህም ወታደሮቹ መጥተው ከክርስቶስ ጋራ ተሰቅሎ የነበረውን የመጀመሪያውን ሰው ጭን ሰበሩ፤ ደግሞም የሌላውን ጭን ሰበሩ። ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን ሞቶ ስላገኙት ጭኖቹን አልሰበሩም፤ ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ የኢየሱስን ጐን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውሃ ፈሰሰ። ይህን ያየው ሰው ምስክርነቱን ሰጥቷል፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ እውነትን እንደሚናገርም ያውቃል፤ እናንተም እንድታምኑ ይመሰክራል። ይህም የሆነው፣ መጽሐፍ፣ “ከዐጥንቱ አንድም አይሰበርም” ያለው እንዲፈጸም፣ ሌላውም መጽሐፍ፣ “የወጉትም ያዩታል” ስለሚል ነው። ከዚህ በኋላ የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስን በድን ለመውሰድ ጲላጦስን ለመነው፤ ዮሴፍም አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር። እርሱም ጲላጦስን ካስፈቀደ በኋላ መጥቶ በድኑን ወሰደ። ከዚህ ቀደም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስ አንድ መቶ ሊትር ያህል የሚመዝን የከርቤና የአደስ ቅልቅል ይዞ መጣ። እነርሱም የኢየሱስን በድን ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋራ ከተልባ እግር በተሠራ ጨርቅ ከፈኑት። ኢየሱስ በተሰቀለበት ቦታም የአትክልት ስፍራ ነበር፤ በአትክልቱም ስፍራ ማንም ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር። ዕለቱ ለአይሁድ የሰንበት መዘጋጃ ቀን ስለ ነበርና መቃብሩም ቅርብ ስለ ነበር ኢየሱስን በዚያ ቀበሩት።