በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲሰቀል ጲላጦስ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ መስቀሉን ተሸክሞ፥ “የራስ ቅል” ወደሚባለው ስፍራ ወጣ፤ ይህ ስፍራ በዕብራይስጥ ቋንቋ “ጎልጎታ” ይባላል፤ እዚያ ሰቀሉት፤ ኢየሱስን በመካከል አድርገው፥ ከእርሱ ጋር ሌሎችንም ሁለት ሰዎች በግራና በቀኝ ሰቀሉ። ጲላጦስ “የናዝሬቱ ኢየሱስ፥ የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ጽሑፍ ጽፎ በመስቀሉ ራስጌ ላይ አኖረው። ኢየሱስ የተሰቀለበት ስፍራ ለከተማ ቅርብ ስለ ነበር፥ ከአይሁድ ብዙዎቹ ጽሑፉን አነበቡት፤ ጽሑፉም የተጻፈው በዕብራይስጥ፥ በላቲንና በግሪክ ቋንቋ ነበር። የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን፥ “አንተ ‘የአይሁድ ንጉሥ’ ብለህ አትጻፍ፤ ነገር ግን ‘ይህ ሰው እኔ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ’ ብሎአል ብለህ ጻፍ” አሉት። ጲላጦስ ግን “የጻፍኩትን ጽፌአለሁ” ሲል መለሰ። ወታደሮቹ ኢየሱስን ከሰቀሉት በኋላ፥ ልብሶቹን ወስደው፥ ለእያንዳንዱ ወታደር አንድ ክፍል እንዲደርስ በአራት ከፋፈሉአቸው፤ እጀ ጠባቡንም እንዲሁ አደረጉ፤ ነገር ግን እጀ ጠባቡ ሳይሰፋ፥ ከላይ እስከ ታች ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበር፤ ስለዚህ ወታደሮቹ “ለማን እንደሚደርስ ለማወቅ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ፥ አንቅደደው” ተባባሉ። ይህም የሆነው፥ “ልብሴን ተከፋፈሉ፤ በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉ” የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው፤ ወታደሮቹም እንዲሁ አደረጉ። በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱና የእናቱ እኅት፥ የቀልዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር፤ ኢየሱስ እናቱንና የሚወደውን ደቀ መዝሙር አጠገቡ ቆመው ባያቸው ጊዜ፥ እናቱን “እናቴ ሆይ! እነሆ፥ ልጅሽ!” አላት። ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን “እነኋት እናትህ!” አለው፤ ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አሁን ሁሉም ነገር እንደ ተፈጸመ ዐውቆ በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈውም ቃል እንዲፈጸም “ተጠማሁ!” አለ። እዚያ ሆምጣጤ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ ስለዚህ እዚያ የነበሩ ሰዎች፥ ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞሉና በሂሶጵ እንጨት አንጠልጥለው ወደ አፉ አቀረቡለት፤ ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከቀመሰ በኋላ “ተፈጸመ!” አለ። ራሱን ዘንበል አድርጎም ነፍሱን ሰጠ።
የዮሐንስ ወንጌል 19 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 19:16-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos