በመጨረሻም ጲላጦስ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው። ወታደሮቹም ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት፤ እርሱም የራሱን መስቀል ተሸክሞ በአራማይክ “ጎልጎታ” ተብሎ ወደሚጠራው “የራስ ቅል” ወደተባለው ቦታ ወጣ። በዚያም ሰቀሉት፤ ከርሱም ጋራ ሁለት ሰዎች፣ አንዱን በዚህ በኩል፣ ሌላውን በዚያ በኩል፣ ኢየሱስንም በመካከል አድርገው ሰቀሉ። ጲላጦስም ጽሑፍ ጽፎ በመስቀሉ ላይ አንጠለጠለው፤ ጽሑፉም፣ “የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ነበር። ኢየሱስ የተሰቀለበት ቦታ ከከተማው አጠገብ ስለ ነበር ብዙዎቹ አይሁድ ጽሑፉን አነበቡት፤ ጽሑፉም፣ በአራማይክና በላቲን፣ በግሪክም ነበር። የአይሁድ የካህናት አለቆች ጲላጦስን በመቃወም፣ “እርሱ፣ ‘የአይሁድ ንጉሥ ነኝ’ እንዳለ ጻፍ እንጂ ‘የአይሁድ ንጉሥ’ ብለህ አትጻፍ” አሉት። ጲላጦስም፣ “በቃ፤ የጻፍሁትን ጽፌአለሁ” ብሎ መለሰ። ወታደሮቹ ኢየሱስን ከሰቀሉ በኋላ፣ እጀ ጠባቡ ሲቀር፣ ልብሱን ወስደው ለእያንዳንዱ አንድ አንድ እንዲዳረስ ለአራት ተከፋፈሉት፤ እጀ ጠባቡም ከላይ እስከ ታች አንድ ወጥ ሆኖ ያለ ስፌት የተሠራ ነበር። ስለዚህ፣ “ዕጣ ተጣጥለን ለሚደርሰው ይድረስ እንጂ አንቅደደው” ተባባሉ። ይህም የሆነው፣ “ልብሴን ተከፋፈሉት፤ በእጀ ጠባቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው። ወታደሮቹ ያደረጉትም ይህንኑ ነው። በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱና የእናቱ እኅት፣ እንዲሁም የቀለዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር። በዚያም ኢየሱስ እናቱንና የሚወድደውም ደቀ መዝሙር አጠገቧ ቆሞ ሲያያቸው እናቱን፣ “አንቺ ሴት ሆይ፤ ልጅሽ ይኸው” አላት፤ ደቀ መዝሙሩንም፣ “እናትህ ይህችው” አለው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይህ ደቀ መዝሙር ወደ ቤቱ ወሰዳት። ከዚያም ኢየሱስ ሁሉ ነገር እንደ ተፈጸመ ዐውቆ፣ የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም፣ “ተጠማሁ” አለ። በዚያም የኮመጠጠ ወይን የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሰፍነግ በወይን ጠጅ ነክረው፣ በሂሶጵ ዘንግ ወደ አፉ አቀረቡለት፤ ኢየሱስም ኮምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ፣ “ተፈጸመ” አለ፤ ራሱን አዘንብሎ፣ መንፈሱን አሳልፎ ሰጠ።
ዮሐንስ 19 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 19
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 19:16-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos