ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቄድሮን ሸለቆ ማዶ ሄደ፤ እዚያ ወደነበረውም የአትክልት ቦታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ገባ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እዚያ ቦታ ዘወትር ይሰበሰቡ ስለ ነበር አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ያን ቦታ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ይሁዳ አንድ የወታደሮች ጭፍራ፥ እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩትን የዘብ ኀላፊዎችን አስከትሎ ወደዚያ ቦታ መጣ፤ እነርሱም ፋኖስና ችቦ፥ የጦር መሣሪያም ይዘው ነበር። ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወደ እነርሱ ወጣ ብሎ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ እንፈልጋለን” አሉት። እርሱም “እኔ ነኝ!” አላቸው። አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። ኢየሱስ “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈገፈጉና በምድር ላይ ወደቁ። ኢየሱስም “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ሲል እንደገና ጠየቃቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ እንፈልጋለን” አሉ። እርሱም “እኔ ነኝ ብዬአችኋለሁ፤ እንግዲህ የምትፈልጉት እኔን ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አለ። ይህም የሆነው፥ “አባት ሆይ፥ ከሰጠኸኝ ሰዎች አንዱን እንኳ አላጠፋሁም” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው። ስምዖን ጴጥሮስ ሰይፍ ይዞ ስለ ነበረ መዘዘና የካህናት አለቃውን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የአገልጋዩም ስም “ማልኮስ” ይባል ነበር። ኢየሱስ ግን ጴጥሮስን፥ “ሰይፍህን ወደ አፎቱ ክተተው፤ አብ የሰጠኝን የመከራ ጽዋ የማልጠጣው ይመስልሃልን?” አለው። ከዚህ በኋላ ወታደሮቹና አዛዣቸው፥ የአይሁድ የዘብ ኀላፊዎችም ኢየሱስን ይዘው አሰሩት። በመጀመሪያ ወደ ሐና ወሰዱት፤ ሐና በዚያ ዓመት የካህናት አለቃ ለነበረው ለቀያፋ ዐማቱ ነበር። ቀያፋ “አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ቢሞት የተሻለ ነው” ሲል የአይሁድ ባለሥልጣኖችን የመከረ ነው። ስምዖን ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉት፤ ያ ሌላው ደቀ መዝሙር በካህናት አለቃው ዘንድ የታወቀ ነበር፤ ስለዚህ ከኢየሱስ ጋር ወደ ካህናት አለቃው ግቢ ገባ፤ ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ አጠገብ ቆሞ ነበር፤ በካህናት አለቃው የታወቀው ደቀ መዝሙር መጣና ለበረኛይቱ ልጃገረድ ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው፤ በረኛይቱም ልጃገረድ ጴጥሮስን “አንተም ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱ ግን “አይደለሁም” አለ። ጊዜው ብርድ ስለ ነበረ አገልጋዮቹና የዘብ ኀላፊዎች የከሰል እሳት አንድደው ቆመው ይሞቁ ነበር፤ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቃው ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ለሰው ሁሉ በግልጥ ተናገርኩ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኲራብም ሆነ በቤተ መቅደስ፥ ዘወትር አስተማርኩ፤ በስውር የተናገርኩት ምንም ነገር የለም፤ ታዲያ፥ ስለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? ስናገራቸው የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ የተናገርኩትን እነርሱ ያውቃሉ።” ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ እዚያ ቆመው ከነበሩት የዘብ ኀላፊዎች አንዱ፥ “ለካህናት አለቃው የምትመልሰው እንዲህ ነውን?” ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። ኢየሱስም “ክፉ ቃል ተናግሬ እንደ ሆነ ክፉ መናገሬን መስክር፤ የተናገርኩት ትክክል ከሆነ ግን ስለምን ትመታኛለህ?” አለው።
የዮሐንስ ወንጌል 18 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 18:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች