ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ሆኖ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻገረ፤ ማዶ ወደ ነበረውም የአትክልት ስፍራ ገቡ። ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ በዚያ ስለሚገናኝ፣ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ቦታውን ያውቅ ነበር። ይሁዳም ወታደሮችን እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩ አገልጋዮችን እየመራ ወደ አትክልቱ ስፍራ መጣ፤ እነርሱም ችቦ፣ ፋኖስና የጦር መሣሪያ ይዘው ነበር። ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወጣና፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” አላቸው። እነርሱም፣ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ከእነርሱ ጋራ ቆሞ ነበር። ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” ባለ ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው መሬት ላይ ወደቁ። እንደ ገናም፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ኢየሱስም መልሶ፣ “ ‘እርሱ እኔ ነኝ’ ብያችኋለሁ እኮ፤ እኔን የምትፈልጉ ከሆነ፣ እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው” አለ፤ ይህ የሆነው፣ “ከሰጠኸኝ ከእነዚህ አንድም አልጠፋብኝም” ብሎ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው። ሰይፍ ይዞ የነበረው ስምዖን ጴጥሮስም፣ ሰይፉን መዝዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ ቀኝ ጆሮ ቈረጠ፤ የባሪያውም ስም ማልኮስ ይባል ነበር። ኢየሱስም ጴጥሮስን፣ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ! አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣምን?” አለው። ወታደሮቹም ከአዛዣቸውና ከአይሁድ አገልጋዮች ጋራ በመሆን ኢየሱስን ያዙት፤ አስረውም፣ በመጀመሪያ የቀያፋ አማት ወደ ነበረው ወደ ሐና አመጡት፤ ቀያፋም የዓመቱ ሊቀ ካህናት ነበር። ቀያፋም ለሕዝቡ ሲባል አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል ብሎ አይሁድን የመከረ ነበር። ስምዖን ጴጥሮስና አንድ ሌላ ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉት። ይህም ደቀ መዝሙር በሊቀ ካህናቱ ይታወቅ ስለ ነበር፣ ከኢየሱስ ጋራ ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ገባ፤ ጴጥሮስ ግን ከበሩ ውጭ ቀረ። በሊቀ ካህናቱ የታወቀው ሌላው ደቀ መዝሙርም ተመለሰና በር ጠባቂዋን አነጋግሮ ጴጥሮስን ይዞት ገባ። በር ጠባቂዋም ጴጥሮስን፣ “አንተ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱም፣ “አይደለሁም” አለ። ብርድ ስለ ነበር ባሮቹና ጠባቂዎቹ ባያያዙት የከሰል ፍም ዙሪያ ለመሞቅ ቆመው ሳሉ፣ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋራ ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር። በዚያ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ለዓለም በግልጽ ተናግሬአለሁ፤ አይሁድ በተሰበሰቡበት ምኵራብ፣ በቤተ መቅደስም ሁልጊዜ አስተምሬአለሁ፤ በስውር የተናገርሁት የለም። ለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ እነሆ፤ የተናገርሁትን እነርሱ ያውቃሉ።” ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ፣ አጠገቡ ቆመው ከነበሩት ጠባቂዎች አንዱ፣ “ለሊቀ ካህናቱ የምትመልሰው እንዲህ ነውን?” ብሎ በጥፊ መታው። ኢየሱስም፣ “ክፉ ተናግሬ ከሆነ ክፉ መናገሬን መስክር፤ እውነት ከተናገርሁ ግን ለምን ትመታኛለህ?” አለው።
ዮሐንስ 18 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 18
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 18:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች