የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ወንጌል 10:14-30

የዮሐንስ ወንጌል 10:14-30 አማ05

መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ እኔ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ በጎቼም እኔን ያውቁኛል። እኔ እነርሱን የማውቃቸው አብ እኔን እንደሚያውቀኝና እኔም አብን እንደማውቀው ዐይነት ነው፤ እኔ ስለ በጎቼ ሕይወቴን አሳልፌ እሰጣለሁ። በዚህ መንጋ ውስጥ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት ይገባኛል፤ እነርሱ ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ ይሆናል። “እንደገና መልሼ እወስዳት ዘንድ ሕይወቴን የምሰጥ ስለ ሆንኩ አብ እኔን ይወደኛል። ሕይወቴን በፈቃዴ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ የሚወስዳት ማንም የለም፤ ሕይወቴን ለመስጠትና መልሼም ለመውሰድ ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልኩት ከአባቴ ነው።” ከዚህ ንግግር የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደገና መለያየት ሆነ። ከእነርሱም ብዙዎቹ፥ “እርሱ ጋኔን አለበት፤ አብዶአል፤ ስለምን ትሰሙታላችሁ?” አሉ። ሌሎች “ይህ ንግግር ጋኔን ካለበት ሰው አንደበት የሚወጣ አይደለም፤ ጋኔን የዕውርን ዐይን ማብራት ይችላልን?” አሉ። በኢየሩሳሌም የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል የሚከበርበት ጊዜ ደረሰ፤ ወቅቱም ክረምት ነበር፤ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ በሰሎሞን መተላለፊያ ይመላለስ ነበር። በዚያን ጊዜ አይሁድ በዙሪያው ተሰብስበው፥ “እስከ መቼ በጥርጣሬ ታቈየናለህ? አንተ መሲሕ እንደ ሆንክ በግልጥ ንገረን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ ነግሬአችኋለሁ፤ እናንተ ግን አታምኑም፤ በአባቴ ስም የምሠራው ሥራ ስለ እኔ ይመሰክራል። እናንተ ግን ከበጎቼ መንጋ ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል። እኔ የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ስለዚህ ከቶ አይጠፉም፤ ከእኔ እጅ ማንም ነጥቆ አይወስዳቸውም። እነርሱን ለእኔ የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል። ከአባቴ እጅ እነርሱን ነጥቆ መውሰድ የሚችል ማንም የለም። እኔና አብ አንድ ነን።”

Free Reading Plans and Devotionals related to የዮሐንስ ወንጌል 10:14-30