ዮሐንስ 10:14-30
ዮሐንስ 10:14-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ እነርሱም ያውቁኛል፤ ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው ነው። ሕይወቴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህ ጕረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት አለብኝ። እነርሱም ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። መልሼ ለማንሣት ሕይወቴን አሳልፌ ስለምሰጥ አባቴ ይወድደኛል። ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ አሳልፌ ለመስጠትም ሆነ ለማንሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልሁትም ከአባቴ ነው።” ከዚህም ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ተፈጠረ። ብዙዎቹም፣ “ጋኔን ያደረበት እብድ ነው፤ ለምን ትሰሙታላችሁ?” አሉ። ሌሎች ግን፣ “ይህ ጋኔን ያደረበት ሰው ንግግር አይደለም፤ ጋኔን የዐይነ ስውርን ዐይን መክፈት ይችላልን?” አሉ። በኢየሩሳሌምም የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ጊዜውም ክረምት ነበረ፤ ኢየሱስም በቤተ መቅደስ ግቢ፣ በሰሎሞን መመላለሻ ያልፍ ነበር፤ አይሁድም ከብበውት፣ “እስከ መቼ ልባችንን አንጠልጥለህ ታቈየናለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንህ በግልጽ ንገረን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔ ነግሬአችሁ ነበር፤ እናንተ ግን አታምኑም፤ በአባቴ ስም የማደርጋቸው ታምራትም ስለ እኔ ይናገራሉ፤ እናንተ ግን በጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም፤ በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል፤ እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ ከቶ አይጠፉም፤ ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም። እነርሱን የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፤ ከአባቴም እጅ ማንም ሊነጥቃቸው አይችልም። እኔና አብ አንድ ነን።”
ዮሐንስ 10:14-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ እኔ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ በጎቼም እኔን ያውቁኛል። እኔ እነርሱን የማውቃቸው አብ እኔን እንደሚያውቀኝና እኔም አብን እንደማውቀው ዐይነት ነው፤ እኔ ስለ በጎቼ ሕይወቴን አሳልፌ እሰጣለሁ። በዚህ መንጋ ውስጥ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት ይገባኛል፤ እነርሱ ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ ይሆናል። “እንደገና መልሼ እወስዳት ዘንድ ሕይወቴን የምሰጥ ስለ ሆንኩ አብ እኔን ይወደኛል። ሕይወቴን በፈቃዴ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ የሚወስዳት ማንም የለም፤ ሕይወቴን ለመስጠትና መልሼም ለመውሰድ ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልኩት ከአባቴ ነው።” ከዚህ ንግግር የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደገና መለያየት ሆነ። ከእነርሱም ብዙዎቹ፥ “እርሱ ጋኔን አለበት፤ አብዶአል፤ ስለምን ትሰሙታላችሁ?” አሉ። ሌሎች “ይህ ንግግር ጋኔን ካለበት ሰው አንደበት የሚወጣ አይደለም፤ ጋኔን የዕውርን ዐይን ማብራት ይችላልን?” አሉ። በኢየሩሳሌም የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል የሚከበርበት ጊዜ ደረሰ፤ ወቅቱም ክረምት ነበር፤ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ በሰሎሞን መተላለፊያ ይመላለስ ነበር። በዚያን ጊዜ አይሁድ በዙሪያው ተሰብስበው፥ “እስከ መቼ በጥርጣሬ ታቈየናለህ? አንተ መሲሕ እንደ ሆንክ በግልጥ ንገረን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ ነግሬአችኋለሁ፤ እናንተ ግን አታምኑም፤ በአባቴ ስም የምሠራው ሥራ ስለ እኔ ይመሰክራል። እናንተ ግን ከበጎቼ መንጋ ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል። እኔ የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ስለዚህ ከቶ አይጠፉም፤ ከእኔ እጅ ማንም ነጥቆ አይወስዳቸውም። እነርሱን ለእኔ የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል። ከአባቴ እጅ እነርሱን ነጥቆ መውሰድ የሚችል ማንም የለም። እኔና አብ አንድ ነን።”
ዮሐንስ 10:14-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤ የእኔ የሆኑትን መንጋዎችን አውቃለሁ፤ የእኔ የሆኑትም ያውቁኛል። አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን አውቀዋለሁ፤ ለበጎችም ቤዛ አድርጌ ሰውነቴን አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህ ቦታ ያይደሉ ሌሎች በጎችም አሉኝ፤ እነርሱንም ወደዚህ አመጣቸው ዘንድ ይገባኛል፤ ቃሌንም ይሰሙኛል፤ ለአንድ እረኛም አንድ መንጋ ይሆናሉ። ስለዚህም፤ አብ ይወድደኛል፥ እንደ ገና አስነሣት ዘንድ እኔ ነፍሴን እሰጣለሁና። ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ ነገር ግን እኔ በፈቃዴ እሰጣታለሁ፤ እኔ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ እወስዳት ዘንድ ሥልጣን አለኝና፤ ይህንም ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።” ስለዚህም ነገር አይሁድ እንደገና እርስ በርሳቸው ተለያዩ። ከእነርሱም ብዙዎች፥ “ጋኔን ይዞት ያብዳል፤ ለምንስ ታዳምጡታላችሁ?” አሉ። ሌሎችም ይህ ነገር ጋኔን ከያዘው ሰው የሚገኝ አይደለም፤ ጋኔን የዕዉሮችን ዐይን ማብራት ይችላልን?” አሉ። በዚያም ወራት በኢየሩሳሌም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ክረምትም ነበር። ጌታችን ኢየሱስም በቤተ መቅደስ በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ይመላለስ ነበር። አይሁድም እርሱን ከብበው፥ “እስከ መቼ ድረስ ሰውነታችንን ታስጨንቀናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “አታምኑኝም እንጂ ነገርኋችሁ፤ እኔ በአባቴ ስም የምሠራው ሥራ እርሱ ምስክሬ ነው። እናንተ ግን አታምኑኝም፤ እንደ ነገርኋችሁ ከበጎች ውስጥ አይደላችሁምና። የእኔ የሆኑ በጎች ግን ቃሌን ይሰሙኛል፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል። እኔም የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘለዓለሙም አይጠፉም፤ ከእጄም የሚነጥቃቸው የለም። እነርሱን የሰጠኝ አባቴ እርሱ ከሁሉ ይበልጣልና፤ ከአባቴም እጅ መንጠቅ የሚችል የለም። እኔና አብ አንድ ነን።”
ዮሐንስ 10:14-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንድሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎቼ አኖራለሁ። ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ። ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል። እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።” እንግዲህ ከዚህ ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ሆነ። ከእነርሱም ብዙዎች፦ “ጋኔን አለበት አብዶአልም፤ ስለ ምንስ ትሰሙታላችሁ?” አሉ። ሌሎችም፦ “ይህ ጋኔን ያለበት ሰው ቃል አይደለም፤ ጋኔን የዕውሮችን ዓይኖች ሊከፍት ይችላልን?” አሉ። በኢየሩሳልውምም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ክረምትም ነበረ። ኢየሱስም በመቅደስ በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ይመላለስ ነበር። አይሁድም እርሱን ከበው፦ “እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሪ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን” አሉት። ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል፦ “ነገርኋችሁ አታምኑምም እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተ ግን እንደ ነገርኋችሁ ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። እኔና አብ አንድ ነን።”
ዮሐንስ 10:14-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ የእራሴን በጎች አውቃለሁ፤ የእራሴም በጎች ያውቁኛል። አብም እንደሚያውቀኝ፥ እኔም አብን እንደማውቀው፤ ነፍሴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ማምጣት ይገባኛል፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ አንድም መንጋ ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። መልሼ ለመውሰድ ነፍሴን አሳልፌ ስለምሰጥ አብ ይወደኛል። እኔ ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። አሳልፌ ለመስጠት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ ለመውሰድም ሥልጣን አለኝ፤ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።” ከእነኚህ ቃላት የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደገና መለያየት ሆነ። ከእነርሱም ብዙዎች “ጋኔን አለበት፤ አብዶአልም፤ ለምንስ ትሰሙታላችሁ?” አሉ። ሌሎችም “ይህ ጋኔን ያለበት ሰው ቃል አይደለም፤ ጋኔን የዐይነ ሥውሮችን ዐይን ሊከፍት ይችላልን?” አሉ። በኢየሩሳሌምም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ወቅቱም የብርድ ጊዜ ነበር። ኢየሱስም በመቅደስ፥ በሰሎሞን ታዛ ይመላለስ ነበር። አይሁድም እርሱን ከብበው “እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሬ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንህ በግልጥ ንገረን፤” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ነገርኋችሁ፤ ነገር ግን አታምኑም፤ እኔ በአባቴ ስም የማደርጋቸው ሥራዎች ስለ እኔ ይመሰክራሉ፤ እናንተ ግን ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘለዓለምም አይጠፉም፤ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፤ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። እኔና አብ አንድ ነን።”