የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ መግቢያ

መግቢያ
ነቢዩ ኤርምያስ የኖረው ከክርስቶስ ልደት በፊት በሰባተኛው ምእት ዓመት መጨረሻና በስድስተኛው ምእት ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ላይ ነው፤ ኤርምያስ በዚህ በረጅም ጊዜ አገልግሎቱ፥ በጣዖት አምልኮአቸውና በኃጢአታቸው ምክንያት በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ከባድ ጥፋት እንደሚደርስባቸው ያስጠነቅቃቸው ነበር፤ ከተናገራቸውም ትንቢቶች መካከል በሕይወት ዘመኑ የሚከተሉትን ሲፈጸሙ አይቷል። ኤርምያስ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ይዞ፥ ከተማይቱንና ቤተ መቅደሱን ማፈራረሱንና የይሁዳ ንጉሥ ከአብዛኛው ሕዝቡ ጋር በምርኮ ወደ ባቢሎን መወሰዱን አይቷል። በተጨማሪ ኤርምያስ፥ ሕዝቡ ከስደት እንደሚመለሱና የእስራኤል መንግሥትም እንደሚቋቋም አስቀድሞ ተናግሮአል።
ትንቢተ ኤርምያስ በአራት ክፍሎች ሊከፈል ይችላል፦
1. በኢዮስያስ፥ በኢዮአቄም፥ በዮአኪንና በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት ለይሁዳ ሕዝብና ለመሪዎቻቸው ከእግዚአብሔር የተላለፈ ቃል።
2. የተለያዩ የትንቢት ቃላትንና በኤርምያስ ሕይወት የተፈጸሙትን ዋና ዋና ነገሮችን ጨምሮ፥ ከኤርምያስ ጸሐፊ ከባሮክ ማስታወሻ ላይ የተገኙ ሰነዶች።
3. ለተለያዩ ባዕዳን ሕዝቦች ከእግዚአብሔር የተላለፈ የትንቢት ቃል።
4. ስለ ኢየሩሳሌም መያዝና ሕዝቡ ተማርከው ወደ ባቢሎን ስለ መወሰዳቸው የሚናገር ተጨማሪ ታሪካዊ መግለጫ።
ኤርምያስ ሕዝቡን በጋለ ስሜት የሚወድና በእነርሱ ላይ የጥፋትን ፍርድ ለማስተላለፍ እጅግ የሚጠላ ሰው ነበር። በነቢይነት እንዲያገለግል እግዚአብሔር ስለ ጠራው በመጨነቁ ምክንያት የገለጠው ጥልቅ ሐዘን በመጽሐፉ ውስጥ በብዙ ቦታ ተጠቅሶአል፤ የእግዚአብሔር ቃል በልቡ ውስጥ እንደ እሳት በመሆኑ አፍኖ ሊያስቀረው አለመቻሉንም ገልጦአል።
በዚህ መጽሐፍ ከሰፈሩት ታላላቅ የትንቢት ቃሎች አንዳንዶቹ፥ ችግር ከተሞላበት ከኤርምያስ ዘመን አልፈው፥ እግዚአብሔር የሚሰጣቸው አዲሱ ቃል ኪዳን ተግባራዊ የሚሆንበትን ጊዜ የሚያመለክቱ ናቸው። አዲሱም ቃል ኪዳን በሕዝቡ ልብ ስለሚጻፍ የሚያስታውሳቸው አስተማሪ ሳያስፈልጋቸው ይጠብቁታል ም. 31፥31-34።
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
እግዚአብሔር ኤርምያስን መምረጡ (1፥1-19)
እግዚአብሔር የይሁዳንና የእስራኤልን ሕዝብ የሚቀጣ መሆኑ (2፥1—25፥38)
በሐሰተኞች ነቢያት ላይ የኤርምያስ ተቃውሞ (26—29)
እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ ምድራቸው የሚመልስ መሆኑ (30—33)
የኤርምያስ የተለያዩ አገልግሎቶች (34—38)
ስለ ኢየሩሳሌም መውደቅና በይሁዳ ስለ ተከሠቱ ሁኔታዎች (39—42)
ኤርምያስ በምድረ ግብጽ (43—44)
ለባሮክ የተላከ መልእክት (45)
ነቢዩ ስለ ተለያዩ ሕዝቦች የተናገረው ትንቢት (46—51)
ስለ ኢየሩሳሌም መውደቅ የተነገረ ተጨማሪ ዘገባ (52)

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ