የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 50

50
ስለ ባቢሎን መያዝ የተነገረ ትንቢት
1ስለ ባቢሎንና ስለ ሕዝብዋ እግዚአብሔር በነቢዩ በኤርምያስ አማካይነት የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ #ኢሳ. 13፥1—14፥23፤ 47፥1-15።
2“ለአሕዛብ ሁሉ በማወጅ ወሬውን ንገሩ!
አርማ አንሥታችሁ ዜናውን አስታውቁ!
ከቶ ምሥጢር አድርጋችሁ አታስቀሩ!
እነሆ ባቢሎን ተያዘች፤ ቤል የተባለው ጣዖት
እንዲያፍር ተደረገ፤
‘ማርዱክ’ የተባለ ጣዖቷም ተሰባብሮአል፤
የባቢሎን ጣዖቶች አፍረዋል፤
አጸያፊ ምስሎችዋም ተሰባብረዋል።
3በባቢሎን ላይ አደጋ ጥሎ ምድረ በዳ
የሚያደርጋት ሕዝብ ከሰሜን በኩል ተነሥቶባታል፤
ሰውም እንስሳውም ጥሎአት ይሸሻል፤
የሚኖርባትም የለም።”
የእስራኤል መመለስ
4እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ዘመኑና ጊዜው ሲደርስ የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ በአንድነት ሆነው እኔን አምላካቸውን ፍለጋ እያለቀሱ ይመጣሉ፤ 5ወደ ጽዮን የሚያደርሰውን መንገድ ይጠይቃሉ፤ አቅጣጫውንም ተከትለው ይጓዛሉ፤ ከእኔም ጋር ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ያደርጋሉ፤ ከቶም አያፈርሱትም።
6“ሕዝቤ እንደ ጠፉ በጎች ሆነዋል፤ ጠባቂዎቻቸውም አሳቱአቸው፤ በተራራ ላይ ባዝነው እንዲቀሩም አደረጉአቸው፤ ከተራራ ወደ ኰረብታ እንደሚባዝኑ በጎች ተንከራተቱ፤ ማደሪያቸውንም ረሱ። 7በጎች የአውሬ ሰለባ እንደሚሆኑ እነርሱንም ያገኛቸው ሁሉ አደጋ ጣለባቸው፤ ጠላቶቻቸውም ‘እኛ እኮ ምንም አልበደልንም፤ ይህ ሁሉ ጥፋት በእነርሱ ላይ የደረሰባቸው የቀድሞ አባቶቻቸው ተስፋ አድርገውበት በኖሩት አምላክ ላይ በማመፃቸው ምክንያት ነው፤ እነርሱም እንደ አባቶቻቸው ለእርሱ ታማኞች ሆነው መኖር ይገባቸው ነበርና ነው።’
8“የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ከባቢሎን ሸሽታችሁ ውጡ! አገሪቱን ለቃችሁ ሂዱ! መንጋውን እንደሚመራ የፍየል አውራ ሁኑ! #ራዕ. 18፥4። 9እኔ ከወደ ሰሜን የተባበሩ ሕዝቦች በባቢሎን ላይ እንዲዘምቱ አነሣሣለሁ፤ በእርስዋም ላይ አደጋ ይጥሉባታል፤ ከዚያም ትያዛለች፤ የእነርሱም ቀስቶች ተወርውረው ዒላማቸውን እንደማይስቱ እንደ ሠለጠኑ ወታደሮች ቀስቶች ናቸው። 10ባቢሎን ትመዘበራለች፤ በዝባዥዎችዋም እስከሚበቃቸው ድረስ ያገኙትን ሁሉ ይወስዳሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
የባቢሎን አወዳደቅ
11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የባቢሎን ሕዝብ ሆይ! ሕዝቤን፥ በመበዝበዛችሁ ደስታና ሐሴት በማድረግ ፈንጥዛችሁ ነበር፤ በመስክ ላይ እንደምትፈነጭ ጊደር ተቀናጥታችሁ፥ እንደ ሰንጋ ፈረሶችም አሽካክታችሁ ነበር፤ 12አሁን ግን ታላቂቱ ከተማችሁ በጣም ታፍራለች፤ እናት አገራችሁም ትዋረዳለች፤ ከመንግሥታት ሁሉ ያነሰች ትሆናለች። ውሃ የማይገኝባት ሆና ወደ ምድረ በዳነት ትለወጣለች። 13ከቊጣዬ የተነሣ በባቢሎን መኖር የሚችል የለም፤ ፈራርሳ ትቀራለች፤ በአጠገብዋ የሚያልፍ ሁሉ ይደነቃል፤ ይደነግጣልም።
14“እናንተ ቀስተኞች ባቢሎንን ለመውጋት ዙሪያዋን ክበቡ፤ በእኔ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት ስለ ሠራች ፍላጾቻችሁንም ሁሉ በባቢሎን ላይ ወርውሩ፤ ለፍላጾቻችሁ አትሳሱ። 15በከተማይቱ ዙሪያ በማቅራራት ደንፉ! እነሆ ባቢሎን እጅዋን ሰጥታለች፤ ግንቦችዋ ተጥሰዋል፤ ቅጽሮችዋም ፈራርሰዋል፤ ባቢሎናውያንን እበቀላለሁ፤ እናንተም ተበቀሉአቸው፤ በሌሎች ላይ የፈጸሙትን ጭካኔ በእነርሱም ላይ ፈጽሙባቸው፤ 16ዘሪውንና መከር ሰብሳቢውን ከባቢሎን አስወግዱ፤ በዚያች አገር የሚኖር እያንዳንዱ የውጪ ዜጋ አደጋ የሚጥልባትን ሠራዊት በመፍራት ወደ ወገኑ ይመለሳል፤ ወደ አገሩም ይሸሻል።”
የእስራኤል መመለስ
17እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የእስራኤል ሕዝብ አንበሳ እያባረረ እንደሚበትናቸው በጎች ሆነዋል፤ በመጀመሪያ አውሬ ያደነውን ሁሉ ቦጫጭቆ እንደሚበላ የአሦር ንጉሥ እነርሱን ፈጃቸው፤ ከዚያም በኋላ አንበሳ አጥንትን እንደሚቈረጣጥም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አደቀቃቸው። 18ስለዚህ እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ የአሦርን ንጉሠ ነገሥት እንደቀጣሁ፥ ናቡከደነፆርንና አገሩን ጭምር እቀጣለሁ። 19የእስራኤልንም ሕዝብ ወደ ምድራቸው እመልሳለሁ፤ በቀርሜሎስ ተራራና በባሳን አውራጃ የሚበቅለውን ሁሉ ይመገባሉ፤ በኤፍሬምና በገለዓድ ከሚበቅለውም እህል የፈለጉትን ያኽል ይመገባሉ፤ 20በዚያን ጊዜ እኔ ከእስራኤልና ከይሁዳ መንግሥታት እንዲተርፉ ያደረግኋቸውን ሰዎች ይቅር ስለምል ኃጢአትና በደል ተፈልጎ አይገኝባቸውም።”
የእግዚአብሔር ፍርድ በባቢሎን ላይ
21እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በምራታይምና በፈቆድ ሕዝብ ላይ አደጋ ጣሉ፤ ግደሉ፤ አጥፉአቸውም፤ እኔ የማዛችሁን ሁሉ አድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 22በምድሪቱም የጦርነት ድምፅ ተሰምቶአል፤ ታላቅ ጥፋትም ደርሷል። 23የዓለምን ሕዝብ እንደ መዶሻ ታደቅ የነበረችው ባቢሎን እርስዋ ራስዋ ደቃለች፤ በዚያች አገር ላይ የደረሰው በሕዝቦች ዘንድ ምንኛ አስደንጋጭ ነው? 24ባቢሎን ሆይ! በራስሽ ላይ ባጠመድሽው ወጥመድ ሳታውቂው ተያዝሽበት፤ ተይዘሽ የተጋለጥሽውም እግዚአብሔርን ስለ ተዳፈርሽ ነው። 25እግዚአብሔር የመሣሪያ ግምጃ ቤቱን ከፍቶ የቊጣ ጦር መሣሪያውን አወጣ፤ ይህንንም ያደረገው የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር በከለዳውያን ምድር የሚሠራው ሥራ ስላለው ነው። 26ከየአቅጣጫው ዝመቱባት፤ እህልዋ የተከማቸበትን ጐተራ ሁሉ ክፈቱ፤ ምርኮውንም እንደ እህል ምርት ቈልሉት፤ ምንም ነገር ሳትተዉ አገሪቱን አጥፉ! 27ወታደሮቻቸውን፥ ወደ ማረጃ ቦታ ወርደው እንደሚታረዱ የዕርድ ኰርማዎች ወስዳችሁ ግደሉ፤ የሚቀጡበት ጊዜ ስለ ደረሰ ለባቢሎን ሕዝብ ወዮላቸው!
28“የባቢሎን ምርኮኞችና በባቢሎን የነበሩ ስደተኞች ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። አምላካችን እግዚአብሔር በባቢሎናውያን ላይ ስለሚበቀለው በቀል የሚናገሩትን አድምጡ።”
29እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ቀስት መደገን የሚችሉትን ቀስተኞች በባቢሎን ላይ ይዘምቱ ዘንድ ጥሩአቸው፤ ከተማይቱን ይክበቡ፤ ማንም እንዳያመልጥ ተጠባበቁ፤ የክፉ ሥራዋንም ዋጋ ክፈሉአት፤ በሌሎች ላይ የፈጸመችውንም ግፍ በእርስዋም ላይ ፈጽሙባት፤ እርስዋ በእስራኤል ቅዱስ በእኔ ላይ ተዳፍራለች፤ #ራዕ. 18፥6። 30ስለዚህ ጐልማሶችዋ በከተማይቱ መንገዶች ይገደላሉ፤ ወታደሮችዋም ሁሉ በዚያው ጊዜ ይደመሰሳሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።
31“ትዕቢተኛይቱ ባቢሎን ሆይ! እኔ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በአንቺ ላይ እነሣለሁ፤ አንቺንም የምቀጣበት ጊዜ ደርሶአል። 32አንቺ ትዕቢተኛይቱ ተሰናክለሽ ትወድቂአለሽ፤ ደግፎ የሚያነሣሽም አይኖርም፤ ከተሞችሽን በእሳት አቃጥላለሁ፤ በዙሪያሽም ያለው ነገር ሁሉ ይደመሰሳል።”
33የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ ተጨቊነዋል፤ ማርከው የወሰዱአቸውም ሁሉ አጥብቀው ይዘዋቸዋል፤ ሊለቁአቸውም አልፈለጉም። 34ነገር ግን ታዳጊያቸው ብርቱ ነው፤ ስሙም የሠራዊት አምላክ ነው፤ እርሱ ራሱ ይረዳቸዋል፤ ሰላምን በምድር ላይ ያወርድላቸዋል፤ በባቢሎን ሕዝብ ላይ ገና መከራን ያመጣባቸዋል።”
35እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በባቢሎን፥ በሕዝቦችዋ፥ በመሪዎችዋና በጥበበኞችዋ ላይ ሰይፍ ይመዘዝ!
36ሟርተኞቻቸው ሞኞች ይሆኑ ዘንድ ወታደሮቻቸውም በፍርሃት ይርበደበዱ ዘንድ
ሰይፍ በእነርሱ ላይ ይመዘዝ!።
37በፈረሶቻቸው፥ በሠረገሎቻቸውና በቅጥር ወታደሮቻቸው ላይ
ሰይፍ ይመዘዝ! እነርሱም እንደ ሴቶች ይሁኑ፤
በሀብታሞቹ ላይ ሰይፍ መዛችሁ ሀብታቸውን ሁሉ ዝረፉ!
38ባቢሎን በአጸያፊና ሰውን በሚያሳብድ ጣዖት የተሞላች ስለ ሆነች
ወንዞችዋ ሁሉ ይድረቁ።
39“ስለዚህ የዱር አራዊት ከቀበሮችና ከሰጎኖች ጋር በባቢሎን ይኖራሉ፤ እንዲሁም እስከ መቼም ድረስ ከትውልድ እስከ ትውልድ የሰው መኖሪያ አትሆንም። #ራዕ. 18፥2። 40ሰዶምንና ገሞራን በአካባቢያቸው ካሉ ከተሞች ጋር በደመሰስኩ ጊዜ እንደሆነው እንዲሁም በባቢሎን ማንም እንደገና ሰፍሮ መኖር አይችልም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። #ዘፍ. 19፥24-25። 41እነሆ ሕዝብ ከሰሜን እየመጣ ነው፥
ኀያል ሕዝብና ብዙ ነገሥታት
ከምድር ዳርቻ እየተንቀሳቀሱ
42ቀስታቸውንና ሰይፋቸውን ይዘዋል፤
እነርሱ ምሕረት የሌላቸው ጨካኞች ናቸው፤
ፈረሶቻቸውን ሲጋልቡ፥ ድምፃቸው እንደሚተም ባሕር ነው፤
ባቢሎን ሆይ! እነርሱ በአንቺ ላይ አደጋ ለመጣል
ለዘመቻ ተዘጋጅተው እንደሚመጡ ሰዎች ወደ አንቺ እየመጡ ነው።
43የባቢሎን ንጉሥ ይህን ወሬ ሲሰማ
እጁ ሽባ ሆኖ ተንጠልጥሎ ይቀራል፤
በምጥ እንደ ተያዘች ሴት ይጨነቃል።
44“በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ከሚገኘው ጥቅጥቅ ካለ ደን ወደ ለምለም መስክ እንደሚወጣ አንበሳ፥ እኔ እግዚአብሔር መጥቼ ባቢሎናውያን ድንገት ከከተማቸው ወጥተው እንዲባረሩ አደርጋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እኔ የምመርጠውን እሾማለሁ፤ ታዲያ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ሊጠይቀኝ የሚደፍር ማነው? የሚቋቋመኝስ መሪ ማን ነው? 45አሁን እንግዲህ እግዚአብሔር በባቢሎናውያን ላይ የመከረውን ምክርና በከለዳውያን ምድር ላይ ያቀደውን ዕቅድ ስሙ፤ ልጆቻቸው እንኳ እንደ በግ ግልገሎች ተጐትተው ይወሰዳሉ፤ በእነርሱም ምክንያት መሰማሪያቸው አስደንጋጭ ይሆናል። 46የባቢሎን መያዝ ዜና ሲሰማ ምድር ትናወጣለች፤ ጩኸትዋም በሕዝቦች መካከል ይሰማል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ