ትንቢተ ኤርምያስ 49

49
ስለ ዐሞን የተነገረ ትንቢት
1እግዚአብሔር ስለ ዐሞን እንዲህ ይላል፦ “እስራኤል ወንዶች ልጆች የሉትምን? ወራሾች የሉትምን? ታዲያ ሚልኮም የተባለውን ጣዖት የሚያመልኩ ወገኖች የጋድን ነገድ አስለቅቀው በከተሞቹ የሰፈሩት ለምንድን ነው? #ሕዝ. 21፥28-32፤ 25፥1-7፤ አሞጽ 1፥13-15፤ ሶፎ. 2፥8-11። 2ስለዚህ የአሞን ከተማ በሆነችው በራባ ላይ የጦርነት ክተት ጥሪ ድምፅ የማሰማበት ጊዜ ይመጣል፤ እርስዋ፥ በፍርስራሽ ክምር የተሞላች ባድማ ትሆናለች፤ መንደሮችዋም በእሳት ይቃጠላሉ፤ ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን አስቀድመው እነርሱን የበዘበዙአቸውን መልሰው ይበዘብዛሉ። 3የዐይ ከተማ ስለ ፈረሰች አልቅሱ! በራባ ከተማ አካባቢ መንደሮች የምትኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ጮክ ብላችሁ አልቅሱ! ሚልኮም የተባለው ጣዖት ከካህናቱና ከረዳቶቹ ጋር ተማርኮ የሄደ ስለ ሆነ ማቅ ለብሳችሁ በቅጥሮችዋ መካከል ወዲያና ወዲህ እያላችሁ አልቅሱ! 4እየቀነሰ በሚሄደው ኀይላችሁ የምትመኩት ለምንድን ነው? እናንተ እምነተቢስ ሕዝብ ሆይ! ‘አደጋ የሚጥልብኝ ማነው?’ ብላችሁ በሀብታችሁ ክምችት ተመክታችኋል። 5እኔ ከሁሉም አቅጣጫ ሽብር አመጣባችኋለሁ፤ ሁላችሁም ትሸሻላችሁ፤ ሁሉም ወደፊቱ ሸሽቶ ስለሚበታተን የሸሹትን ስደተኞች የሚሰበስብ አይገኝም። 6ነገር ግን ከጊዜ በኋላ የአሞናውያንን ንብረት እመልሳለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
ስለ ኤዶም የተነገረ ቃል
7የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኤዶም የተናገረው ይህ ነው፦ “የቴማን ከተማ ሕዝብ ከዚህ በፊት የነበራቸውን ጥበብ አጥተዋልን? አማካሪዎቻቸውስ ምክር መስጠት አቅቷቸዋልን? የነበራቸውስ ጥበብ የት ደረሰ? #ኢሳ. 34፥5-17፤ 63፥1-6፤ ሕዝ. 25፥12-14፤ 35፥1-5፤ ሚል. 1፥2-5። 8የዔሳውን ዘር በምቀጣበት ጊዜ መከራን ስለማመጣባቸው፥ የደዳን ከተማ ሕዝብ ሆይ! ወደ ኋላ ተመልሳችሁ ሩጡ! በዋሻም ተሸሸጉ! 9ሰዎች የወይን ዘለላ በሚለቅሙበት ጊዜ በወይኑ ተክል ላይ ጥቂት ቃርሚያ ይተዋሉ፤ ወንበዴዎችም በሌሊት በመጡ ጊዜ የሚፈልጉትን ያኽል ብቻ ይወስዳሉ፤ 10እኔ ግን የዔሳውን ዘር በፍጹም አራቊታቸዋለሁ። የሚሸሸጉበትንም ስፍራ አጋልጣለሁ፤ ስለዚህም ከእንግዲህ ወዲህ የሚሸሸጉበት ስፍራ ማግኘት አይችሉም፤ ልጆቻቸው፥ ዘመዶቻቸውና ጐረቤቶቻቸው ይጠፋሉ፤ እነርሱም አይኖሩም። 11በመካከላችሁ ያሉትን አባቶቻቸውና እናቶቻቸው የሞቱባቸውን ልጆች ተዉአቸው እኔ በሕይወት አኖራቸዋለሁ። ባሎቻቸው የሞቱባቸውም ሴቶች በእኔ ይተማመኑ።
12“እንግዲህ መቀጣት የማይገባቸው ሰዎች እንኳ የቅጣቱን ጽዋ ገፈት የሚቀምሱ ከሆነ እናንተ ያለ ቅጣት የምታመልጡ ይመስላችኋልን? አይደለም፤ እናንተም ከቅጣቱ ጽዋ መጠጣት አለባችሁ። 13የቦጽራ ከተማ አስፈሪ ምድረ በዳ ሆና እንደምትቀር እኔ በራሴ ምዬአለሁ፤ ሕዝብ ሁሉ መቀለጃ ያደርጋታል፤ ስሟንም እንደ ርግማን ይቈጥሩታል። በአቅራቢያዋ ያሉ መንደሮች ሁሉ ለዘለዓለም ፍርስራሾች ሆነው ይቀራሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
14አንድ መልእክት ከእግዚአብሔር ሰምቼአለሁ፤ “በኤዶም ሕዝብ ላይ አደጋ ለመጣል ተሰብሰቡ! ለጦርነትም ተነሡ!” ብሎ የሚናገር መልእክተኛ ወደ ሕዝቦች ተልኮአል። 15“አሁን እንግዲህ በመንግሥታት መካከል ታናሽ፥ በሰዎችም መካከል የተናቅሽ አደርግሻለሁ። 16አለታማው ገደል ላይ የምትኖሪ፥ እስከ ተራራማው ጫፍ ድረስ የምትደርሽ ሆይ! ተፈሪነትሽና የልብሽ ኲራት አታለውሻል፤ ምንም እንኳ መኖሪያሽን እንደ ንስር ጎጆ ብታደርጊ እኔ ከዚያ ላይ አወርድሻለሁ ይላል እግዚአብሔር።”
17እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ኤዶም የምታስደነግጥ ትሆናለች፤ በዚያ በኩል ሲያልፍ የሚያያት ሁሉ ይደነግጣል፤ በደረሰባት ጥፋትም ይገረማል። 18ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸው ከሚገኙ ከተሞች ጋር በተደመሰሱ ጊዜ የደረሰባቸው ጥፋት እንዲሁ በተመሳሳይ በኤዶምም ላይ ይደርሳል። ዳግመኛም በዚያ ሰፍሮ የሚኖር ከቶ አይገኝም። #ዘፍ. 19፥24-25። 19አንበሳ ጥቅጥቅ ካለው ከዮርዳኖስ ጫካ ወጥቶ ለምለም ወደ ሆነው ወደ በጎች መሰማርያ መስክ እንደሚመጣ እኔም በድንገት መጥቼ የኤዶም መሪዎችን አባርራለሁ፤ ከዚህ በኋላ የምመርጠውን እሾማለሁ፤ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ሊጠይቀኝ የሚደፍር ማን ነው? በፊቴ ቆሞ የሚቋቋመኝስ መሪ ማን ነው? 20ስለዚህም በኤዶም ሕዝብ ላይ ያቀድኩትንና በቴማን ከተማ ሕዝብ ላይ ላደርግ የፈለግኹትን ስሙ፤ ልጆቻቸው እንኳ እንደ በግ ግልገሎች እየተጐተቱ ይወሰዳሉ፤ በእነርሱም ምክንያት የሚያያቸው ሁሉ ይደነግጣል። 21የኤዶም አወዳደቅ ዜና ሲሰማ ምድር ትናወጣለች፤ የድንጋጤውም ጩኸት ከዚያ አልፎ እስከ ቀይ ባሕር ይሰማል። 22ጠላት በቦጽራ ላይ ክንፉን በስፋት ዘርግቶ ወደ ታች እንደሚወርድ ንስር በመሆን ጉብ ይልባታል፤ በዚያን ጊዜ የኤዶም ወታደሮች በምጥ ተይዛ በፍርሃት እንደምትጨነቅ ወላድ ሴት ይሆናሉ።
ስለ ደማስቆ የተነገረ ትንቢት
23“የሐማትና የአርፋድ ከተማ ነዋሪዎች የደማስቆን የጥፋት ወሬ ስለ ሰሙ ግራ ተጋቡ፤ ወደ ላይና ወደ ታች እንደሚናወጥ ባሕር የእነርሱም ልብ ተሸበረ። #ኢሳ. 17፥1-3፤ አሞጽ 1፥3-5፤ ዘካ. 9፥1። 24የደማስቆ ሕዝብ ተዳከሙ፤ ለመሸሽ ወደ ኋላ ተመለሱ ፍርሀትም ያዛቸው፤ የምጥ ጣር እንደ ያዛትም ሴት ተጨነቁ። 25ያቺ ዝነኛዋና አስደሳችዋ ከተማ እንዴት ባዶዋን ቀረች? 26በዚያን ቀን የዚያች ከተማ ወጣቶች በከተማይቱ መንገዶች ላይ ይገደላሉ፤ ወታደሮችዋም ይደመሰሳሉ። 27የደማስቆን ቅጽር ሁሉ በእሳት አጋያለሁ፤ የንጉሥ ቤንሀዳድንም ቤተ መንግሥት በእሳት አቃጥላለሁ፤ እኔ የሠራዊት አምላክ ይህን ተናግሬአለሁ።”
በቄዳርና በሐጾር ነገዶች ላይ የተነገረ ትንቢት
28የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ድል ስላደረጋቸው ስለ ቄዳርና ስለ ሐጾር መንግሥታት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ተነሡ፤ በቄዳር ሕዝብ ላይ ዝመቱ፤ የምሥራቅንም ሕዝብ አጥፉ! 29ድንኳኖቻቸውን፥ መንጋዎቻቸውን፥ መጋረጃዎቻቸውንና ዕቃዎቻቸውን ሁሉ ውሰዱ፤ ግመሎቻቸውን ለራሳችሁ ውሰዱ። ‘በዙሪያው ሽብር ተነሥቷል’ ብለው ይጮኻሉ።”
30የሐጾር ነዋሪዎች እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በእናንተ ላይ ስለ መከረባችሁና ክፉ ዕቅድ ስላቀደባችሁ ርቃችሁ ሽሹ፤ በጥልቁም ዋሻ ተደበቁ።”
31እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ተነሡ! መዝጊያና መወርወሪያ ሳይኖረው ብቸኛ ሆኖ ወደሚኖርና ተዝናንቶ በሰላም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ ዝመቱ። 32ግመሎቻቸውና ከብቶቻቸው ይማረካሉ፤ የግንባራቸውን ግራና ቀኝ የተላጩትን ሁሉ በየአቅጣጫው እበትናቸዋለሁ፤ ከየአቅጣጫውም መከራ አመጣባቸዋለሁ።” 33ስለዚህም ሐጾር ለዘለዓለሙ ቀበሮዎች ብቻ የሚኖሩባት ምድረ በዳ ሆና ትቀራለች፤ ዳግመኛም በዚያ ሰፍሮ የሚኖር ሕዝብ ከቶ አይገኝም።
ስለ ዔላም የተነገረ ትንቢት
34ሴዴቅያስ በይሁዳ ላይ እንደ ነገሠ ወዲያውኑ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ስለ ዔላም አገር ተናገረኝ፤ እንዲህም አለኝ፦ 35“ዔላምን ይህን ያኽል ኀያል እንድትሆን ያደረጋችኹትን የዔላምን የጦር ኀይል እሰብራለሁ። 36ከየአቅጣጫውም የሚመታት ነፋስ በዔላም ላይ አስነሣለሁ፤ ሕዝቧንም በየስፍራው እበትናለሁ፤ በዚህም ዐይነት የእርስዋ ስደተኞች የማይኖሩበት አገር አይገኝም። 37የዔላም ሕዝብ ሕይወታቸውን ሊያጠፉ የሚፈልጉትን ጠላቶቻቸውን እንዲፈሩ አደርጋለሁ። በእነርሱም ላይ ለጥፋታቸው ምክንያት የሆነው ኀይለኛ ቊጣዬን አመጣባቸዋለሁ፤ እስኪያልቁ ድረስ በጦርነት እንዲሳደዱ አደርጋለሁ። 38ንጉሣቸውንና መሪዎቻቸውን አጠፋለሁ፤ ዙፋኔንም በዚያ እዘረጋለሁ። 39ሆኖም የዔላምን ንብረት የምመልስበት ጊዜ ይመጣል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ