ትንቢተ ኤርምያስ 48
48
የሞአብ መጥፋት
1የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ስለ ሞአብ የሚለው ይህ ነው፦
“ነቦ ስለምትደመሰስ፥
ለነቦ ሕዝብ ወዮላቸው!
ቂርያታይም በጠላት እጅ ትወድቃለች፤
ብርቱ የሆኑ ምሽጎችዋም ይደመሰሳሉ፤
ሕዝብዋም በዕፍረት ላይ ይወድቃሉ። #ሕዝ. 25፥8-11፤ ሶፎ. 2፥8-11።
2የሞአብ ክብር ያልፋል፤
ሰዎች ሐሴቦንን ለመጣል ያሤራሉ፤
‘ኑ ከእንግዲህ በሕዝብነት እንዳትታወቅ እናጥፋት’ ይላሉ፤
እናንተም የማድሜን ሰዎች ሆይ! ሰይፍ ስለሚያሳድዳችሁ
ጸጥ እንድትሉ ትደረጋላችሁ።
3በሖሮናይም ላይ በሚደርሰው ውድመትና ጥፋት የሚሰማውን
ጩኸት አድምጡ።
4“ሞአብ ተደምስሳለች፤
ልጆችዋም ጩኸትን ያሰማሉ።
5ወደ ሉሒት ሲወጡ ምርር ብለው እያለቀሱ ይወጣሉ፤
ወደ ሖሮናይም ቊልቊለት ሲወርዱ
በውድመቱ ምክንያት የጭንቀት ድምፅ ያሰማሉ።
6እርስ በርሳቸውም ‘ሕይወታችሁን ለማትረፍ በፍጥነት ሩጡ!
በበረሓም እንደሚኖር የሜዳ አህያ ብረሩ!’ ይባባላሉ።
7“የሞአብ ሕዝብ ሆይ! በኀይላችሁና በሀብታችሁ ብዛት ተማምናችሁ ነበር፤
አሁን ግን እነሆ እናንተ ራሳችሁ እንኳ ትማረካላችሁ፤
ከሞሽ ተብሎ የሚጠራው ጣዖት ከልዑላን መሳፍንትና ከካህናቱ ጋር ተማርኮ ይወሰዳል።
8እግዚአብሔር እንደ ተናገረ
አጥፊው በከተሞች ሁሉ ላይ ይመጣል፤
አንድም የሚያመልጥ ከተማ የለም።
ሸለቆውንና ሜዳውን እንዳልነበሩ ያደርጋል።
9ጠፍ እንድትሆን በሞአብ አገር ላይ ጨው ነስንሱባት፤
ከተሞችዋም ሰው የማይኖርባቸው ባድማ ይሆናሉ።”
10ቸል በማለት የእግዚአብሔርን ሥራ ከልብ የማይፈጽም ሰው የተረገመ ይሁን! እግዚአብሔር በሚያዘውም ጊዜ ሰይፉን ከደም የሚከለክል የተረገመ ይሁን!
የሞአብ ከተሞች መደምሰሳቸው
11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከዕቃ ወደ ዕቃ ሳይገለባበጥ ከአተላው ጋር አብሮ የቈየ የወይን ጠጅ ጣዕሙ እንዳለ ይቈያል፤ መዓዛውም አይለወጥም፤ እንደዚሁም የሞአብ ሕዝብ አገራቸው ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ሳይታወኩ ኖረዋል፤ ተማርከውም አይታወቁም። 12አንድ ሰው የወይን ጠጅን ከአንድ ዕቃ ወደ ሌላ ዕቃ ገልብጦ ባዶውን ዕቃ እንደሚሰብር፥ እኔም ሞአብን የሚያወድምና ሕዝብዋን የሚያፈልስ ሰው የምልክበት ጊዜ በእርግጥ ተቃርቦአል። 13እስራኤላውያን ይታመኑበት በነበረው በቤቴል በተተከለው ጣዖት እንዳፈሩ፥ ሞአባውያንም ከሞሽ ተብሎ በሚጠራው ጣዖታቸው ያፍራሉ።”
14“የሞአብ ሰዎች ሆይ! ‘እኛ ተዋጊ አርበኞችና
በጦርነት የተፈተንን ወታደሮች ነን’ ብላችሁ ስለምን ትመካላችሁ?
አጥፊው መጥቶአል፤
15ሞአብና ከተሞችዋማ እነሆ ተደምስሰዋል፤
የሚያስደስቱ ወጣቶችዋም ለመታረድ ወርደዋል።
እኔ ንጉሡ ይህን ተናግሬአለሁ ስሜም ‘የሠራዊት አምላክ’ ነው።
16የሞአብ ጥፋት ተቃርቦአል፤
የመፈራረሻዋም ጊዜ ፈጥኖ ይደርሳል።
17“ዝናዋን የምታውቁና በአቅራቢያዋ የምትኖሩ ሕዝቦች ሁሉ
‘የሥልጣን ምልክት የሆነው የተከበረው ኀይልዋ፥ በትረ መንግሥትዋ
እንዴት ተሰበረ’ በማለት ዋይ! ብላችሁ አልቅሱላት!
18ምሽጎችዋም ፍርስራሽ ሆነው እንዲቀሩ የሚያደርግ
ሞአብን የሚደመስሳት እነሆ እዚህ ስለ አለ፥
በዲቦን ከተማ የምትኖሩ ሁሉ ከክብር ቦታችሁ ወርዳችሁ
በምድር ትቢያ ላይ ተቀመጡ፤
19በዓሮዔር የምትኖሩ ሁሉ፥
በመንገድ ዳር ቆማችሁ ተጠባበቁ፤
የሚሸሹትን ወንዶችና የሚያመልጡትን ሴቶች ሁሉ በመጠየቅ፥
የሆነውን ነገር ሁሉ ዕወቁ።
20ሞአብ ፈራርሳ በዕፍረት ስለ ወደቀች
ዋይ ዋይ ብላችሁ አልቅሱላት፤
ባድማ መሆንዋንም በአርኖን ወንዝ አጠገብ ተናገሩ።
21-24“በደጋማ ቦታ በተቈረቈሩት፥ ሖሎን፥ ያህጻ፥ ሜፋዓት፥ ዲቦን፥ ነቦ፥ ቤትዲብላታይም፥ ቂርያታይም፥ ቤትጋሙል፥ ቤትመዖን፥ ቀሪዮትና ቦጽራ ተብለው በሚጠሩትና፥ በሩቅም በቅርብም በሚገኙት በሞአብ ከተሞች ሁሉ ላይ የቅጣት ፍርድ መጥቶአል፤ 25የሞአብ መከላከያ ኀይል ተሰብሮአል፤ ሥልጣንዋም ተገፎአል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
የሞአብ መዋረድ
26እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በእኔ ላይ ስለ ታበየች ሞአብን አጠጥታችሁ አስክሩአት፤ በትፋቷ ላይ ትንከባለል፤ ሕዝብም ይሳቅባት፤ 27ሞአብ ሆይ! እስራኤል ከሌቦች ጋር የተያዘች ባትሆንም እንኳ አንቺ እርስዋን መሳለቂያ አድርገሽ ስለ እርስዋ በተናገርሽ ቊጥር ራስሽን ትነቀንቂ ነበር።
28“የሞአብ ነዋሪዎች ሆይ! ከተሞቻችሁን ለቃችሁ በገደል አፋፍ ጎጆዋን እንደምትሠራ እንደ ርግብ በመሆን በቋጥኞች መካከል ኑሩ። 29ሞአብ በከፍተኛ ኲራት፥ ራሷን ከፍ ከፍ በማድረግ በትዕቢተኛነት፥ በመጀነንና በልበ ደንዳናነት የተወጠረች መሆንዋን ሰምቼአለሁ። 30እኔ የእርስዋን ዕብሪተኛነት ዐውቃለሁ፤ ፉከራዋና ሥራዋ ከንቱ ናቸው። 31ለሞአብ ዋይ፥ ዋይ እልላታለሁ፤ ለሞአባውያን ሁሉ ድምፄን ከፍ ከፍ አድርጌ እጮኻለሁ፥ ለቂርሔሬስ ሰዎች የሐዘን ለቅሶ አለቅሳለሁ። 32ለያዕዜር ሕዝብ ከማለቅሰው ይበልጥ ለሲብማ ሕዝብ እየጮኽኩ አለቅሳለሁ፤ የሲብማ ከተማ ሆይ! እንቺ ቅርንጫፎችዋ ሙት ባሕርን አልፎ እስከ ያዜር እንደሚደርስ የወይን ተክል ነሽ፤ ነገር ግን በጐመራው ፍሬሽና በወይን ዘለላሽ ላይ አጥፊው መጥቷል። 33ደስታና ሐሴት ለምለም ከሆነችው ከሞአብ ምድር ተወስደዋል፤ ከወይን መጭመቂያዎች ሁሉ የወይን ጠጅ እንዳይፈስስ አድርጌአለሁ፤ የደስታ ድምፅ እያሰማ የሚጨምቅ የለም፤ ድምፅ የሚሰማ ቢሆንም የሚሰማው ድምፅ ግን የደስታ ድምፅ አይደለም።
34“የሐሴቦንና የዔልዓሌ ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይጮኻሉ፤ ጩኸታቸውም እስከ ያሀጽ ተሰምቶአል፤ ከጾዓር እስከ ሖሮናይምና ዔግላት ሺሊሺያ ድረስ ተሰምቶአል፤ የኒምሪም ውሃ እንኳ ደርቆአል። 35በሞአብ መስገጃ ቦታዎች መሥዋዕት የሚያቀርቡትንና ለአማልክታቸው የሚያጥኑትን አጠፋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።
36“በሞአብና በቂርሔሬስ የሚኖሩ ሕዝብ የነበራቸውን ሁሉ በማጣታቸው ምክንያት በዋሽንት ተመርተው እንደሚያለቅሱ ሰዎች አለቅስላቸዋለሁ። 37የሞአብ ሕዝብ በሰገነቶች ላይና በመንገዶች ላይ ሆነው ያለቅሳሉ፤ ወንዶች ጢማቸውን ይቈረጣሉ፤ ሕዝቡም ራሳቸውን ይላጫሉ፤ እጆቻቸውን ይበጣሉ፤ ማቅም ይለብሳሉ። 38ሞአብን እንደማይፈለግ ዕቃ ስለ ሰበርኳት በቤት ሰገነቶች ላይና በሕዝብ አደባባዮች ሁሉ ከለቅሶ በቀር ሌላ የሚሰማ ነገር የለም። 39በሞአብ ላይ ምን ዐይነት አስደንጋጭ ሁናቴ ደርሶ ነው የምታለቅሰው? እንዴትስ በዕፍረት ጀርባዋን ትሰጣለች? ስለዚህም ለጐረቤቶችዋ ሁሉ መሳለቂያና አስደንጋጭ ሆናለች።”
40ክንፉን ዘርግቶ ወደ ታች እንደሚወረወር ንስር በሞአብ ላይ የሚያንዣብብ ጠላት መምጣቱን እግዚአብሔር ተናገረ፤ 41ከተሞችና ምሽጎች ሁሉ ይያዛሉ፤ በዚያን ጊዜ የሞአብ ወታደሮች በምጥ እንደ ተያዘች ሴት ሆነው በፍርሃት ይጨነቃሉ፤ 42ሞአብ በእኔ ላይ ስለ ታበየች ትደመሰሳለች፤ ከእንግዲህ ወዲህ በመንግሥትነት አትታወቅም። 43የሞአብ ሕዝብ ሆይ፥ “ሽብር፥ የሚያሰናክል ጒድጓድና ወጥመድ ይጠብቃችኋል፤” ይላል እግዚአብሔር። 44“ከሽብር የሚያመልጠው፥ ጒድጓድ ውስጥ ይገባል፤ ከጒድጓድ ዘሎ የሚወጣውም ሁሉ በወጥመድ ይያዛል፤ ሞአብን የምቀጣበትን ቀን አመጣባታለሁ” ይላል እግዚአብሔር። 45በሽሽት የደከሙ ስደተኞች በሐሴቦን ጥላ ሥር ተጠልለዋል፤ ይህም የሆነው እሳት ከሐሴቦን፥ ነበልባልም ከሲሆን ቤቶች ወጥቶ የሞአብን ግንባር ቀደም ሠራዊትና ደጋፊ መሪዎችዋን አቃጥሎአል። 46ለሞአብ ሕዝብ ወዮላችሁ! ካሞሽ ለተባለው ጣዖት የሚሰግዱ ሕዝብ ተደመሰሱ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም ተማርከው ተወሰዱ።
47“ሆኖም የሞአብን ንብረት የምመልስበት ጊዜ ይመጣል፤” ይላል እግዚአብሔር፤ ስለ ሞአብ የተወሰነው ፍርድ እዚህ ላይ ይጠናቀቃል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 48: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997