የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 4

4
የንስሓ ጥሪ
1እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ወደ እኔ ለመመለስ ከፈለጋችሁ እነዚያን አጸያፊ ጣዖቶችን አስወግዳችሁ ለእኔ ብቻ ታማኞች ብትሆኑ፥ 2በእውነትና በቅንነት ‘ሕያው እግዚአብሔርን’ ብላችሁ ብትምሉ ሕዝቦች ይባረካሉ፤ በዚህም ይመካሉ።”
3እግዚአብሔር ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “እዳሪውን መሬት እረሱ፤ ዘራችሁን በሾኽ መካከል አትዝሩ! #ሆሴዕ 10፥12። 4እናንተ የይሁዳ ሕዝብና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሆይ! የልባችሁን ክፋት ገርዛችሁ አእምሮአችሁን በማንጻት ሁለንተናችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ይህን ባታደርጉ ግን በክፉ ሥራችሁ ምክንያት ቊጣዬ እንደ እሳት ይነዳል፤ ቊጣዬም ከነደደ ማንም ሊያጠፋው አይችልም።”
ይሁዳን ለመውረር የጠላት ዛቻ
5በምድሪቱ ሁሉ ላይ መለከት ንፉ!
ድምፃችሁንም ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ!
የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ወደተመሸጉ ከተሞች እንዲሸሹ ንገሩአቸው።
6ለጽዮን መንገዱን አመልክቱአት!
ሳትዘገዩ የደኅንነት ዋስትና ወደሚገኝበት ስፍራ ሽሹ!
እግዚአብሔር ከሰሜን በኩል መቅሠፍትና ታላቅ ጥፋት ሊያመጣ ነው።
7አንበሳ ከተሸሸገበት ደን እንደሚወጣ፥
ሕዝብን ሁሉ የሚያጠፋ ይነሣል፤
እርሱም ይሁዳን ለማጥፋት ይመጣል፤
የይሁዳ ከተሞች ይፈራርሳሉ፤
የሚኖርባቸውም አይገኝም።
8የእግዚአብሔር ብርቱ ቊጣ ከይሁዳ ስላልተለየ፥
ማቅ ለብሳችሁ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ።
9እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ቀን ንጉሡና ባለሟሎቹ ፍርሀት ያድርባቸዋል፤ ካህናት ይንቀጠቀጣሉ፤ ነቢያትም ይደነግጣሉ።”
10እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ማታለል አይሆንብህምን? ‘ሰላም ይሆንላችኋል’ ብለሃቸው ነበር፤ እነሆ አሁን ሰይፍ በአንገታቸው ላይ ተቃጥቶአል” አልኩ።
11በዚያን ጊዜ ለዚህ ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ተብሎ ይነገራቸዋል፥ “በሕዝቤ ላይ የሚያቃጥል ነፋስ በበረሓ ካሉት ኰረብቶች ተነሥቶ ይነፍስባቸዋል፤ ይህም የሚያበጥር ወይም የሚያጠራ ነፋስ አይደለም። 12በእግዚአብሔር ትእዛዝ የሚመጣ ነፋስ ስለ ሆነ ከሁሉ የበረታ ነው፤ ይህን ፍርድ በሕዝቡ ላይ የሚያስተላልፍ ራሱ እግዚአብሔር ነው።”
የይሁዳ በጠላት መከበብ
13“እነሆ የጠላት ሠራዊት እንደ ደመና አንዣቦአል፤ የጦር ሠረገሎቹ እንደ ዐውሎ ነፋስ ፈጣኖች ናቸው፤ ፈረሶቹም ከንስር ይበልጥ ይበራሉ፤ ለእኛ ወዮልን! ጠፍተናል!
14“ኢየሩሳሌም ሆይ! መዳን ከፈለግሽ ክፋትን ሁሉ ከልብሽ አጥበሽ አስወግጂ፤ ለመሆኑ የኃጢአት ሐሳብ ከአእምሮሽ የማይጠፋው እስከ መቼ ነው?
15“ከዳን ከተማና ከኤፍሬም ኰረብቶች ክፉ አዋጅ የሚያውጅ ድምፅ ይሰማል፤ 16በይሁዳ ከተሞች ላይ ጦርነትን እያወጁ ወራሪዎች ከሩቅ አገር በመምጣት ላይ መሆናቸውን ለሕዝቦች አሳውቁ! ለኢየሩሳሌም ሕዝብም ንገሩ! 17ሕዝብዋ በእግዚአብሔር ላይ ስለ ዐመፁ፥ እንደ መከር እህል ጠባቂ ኢየሩሳሌምን ጠላት ይከባታል፤” ይህን የተናገረ እግዚአብሔር ነው።
18ይሁዳ ሆይ! ይህ ሁሉ የደረሰብሽ በአካሄድሽና በክፉ ሥራሽ ምክንያት ነው፤ ይህም ሁሉ የመረረ መከራ የመጣብሽ በኃጢአትሽ ምክንያት ስለ ሆነ ወደ ሰውነትሽ ዘልቆ ልብሽን አቊስሎታል።
ኤርምያስ ለሕዝቡ ማዘኑ
19ወይ ሥቃይ! ይህን ሁሉ ሥቃይ እንዴት መታገሥ እችላለሁ!
ወይ ልቤ! የልቤ አመታት እንዴት ፈጠነ?
የጥሩምባ ድምፅና የጦርነት ድምፅ እየሰማሁ፥
ዝም ብዬ መታገሥ አልችልም።
20መቅሠፍት በመቅሠፍት ላይ ይደራረባል፤
አገሪቱ በሙሉ ፈራርሳ ጠፍ ሆናለች፤
ድንኳኖቻችን በድንገት ወደሙ፤
መጋረጃዎቻቸውም በቅጽበት ተቀደዱ።
21የሰልፍ ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብ፥
የጦርነት ድምፅ ሲያስገመግም፥
የጥሩምባም ድምፅ ሲያስተጋባ
የምሰማው እስከ መቼ ነው?
22እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ሕዝቤ እኔን የማያውቁ ሞኞች ሆነዋል፤
ማስተዋል ስለ ጐደላቸው እንደ ሕፃናት የሚታለሉ ናቸው፤
ክፉ ነገር ለመሥራት የተራቀቁ ብልኆች ናቸው፤
መልካም ነገር ማድረግ ግን ከቶ አይሆንላቸውም።”
ስለሚመጣው ጥፋት ኤርምያስ ያየው ራእይ
23ምድርን ተመለከትኩ፤
እነሆ ባድማ ሆናለች፤
ሰማይንም ተመለከትኩ፤
እነሆ ብርሃን አይታይበትም።
24ተራራዎችን ተመለከትኩ፤
እነርሱም በመንቀጥቀጥ ላይ ናቸው፤
ኰረብቶችንም አየሁ፤
እነሆ ወዲያና ወዲህ በመናጥ ላይ ናቸው።
25ሕዝብ አለመኖሩን አየሁ፤
ወፎችም በረው ጠፍተዋል።
26ለምለሚቱ ምድር ወደ በረሓነት ተለውጣለች፤
ከእግዚአብሔር ብርቱ ቊጣ የተነሣ፥
ከተሞችዋ ሁሉ ፈራርሰዋል።
27እነሆ እግዚአብሔር፥ ምድሪቱ ወደ ምድረ በዳነት እንደምትለወጥ፥ እስከ መጨረሻው ግን እንደማይደምስሳት ተነግሮአል።
28ምድር ታለቅሳለች፤
ሰማይም በጨለማ ይጋረዳል፤
ይህን እግዚአብሔር ተናግሮአል፤
ሐሳቡም አይለወጥም፤
ቊርጥ ውሳኔ አድርጎአል፤
ወደ ኋላም አይመለስም።
29ከፈረሰኞችና ከቀስት ወርዋሪዎች ድንፋታ የተነሣ፥ የከተማ ሰው ሁሉ ይሸሻል፤
አንዳንዶቹ ወደ ጫካ ይሮጣሉ፤
የቀሩት በየአለቱ ላይ ይወጣሉ፤
እያንዳንዱ ከተማ ሰው የማይኖርበት ወና ይሆናል፤
የሚኖርበትም አያገኝም።
30ለጥፋት የተዳረግሽ ኢየሩሳሌም ሆይ! ወዮልሽ!
ቀይ ልብስ የለበስሽበት ምክንያት ምንድን ነው?
ጌጣጌጥ ማድረግሽና ዐይንሽንስ መኳልሽ ለምንድነው?
ውሽሞችሽ ጠልተውሽ ሊገድሉሽ ስለሚፈልጉ
ውበትሽን የምትንከባከቢው በከንቱ ነው።
31ምጥ የያዛት ሴት የምታሰማውን ጩኸት የመሰለ ድምፅ ሰማሁ፤
የመጀመሪያ ልጅዋን የምትወልድ በካር ሴት
የምታሰማውን ድምፅ የመሰለ ኡኡታም አዳመጥኩ፤
ይህም ድምፅ ኢየሩሳሌም ትንፋሽ አጥሮአት
እጅዋን ዘርግታ “ወዮልኝ! ጠፋሁ!
እነሆ ሊገድሉኝ መጡ!” እያለች የምታሰማው ጩኸት ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ