ትንቢተ ኤርምያስ 5
5
የኢየሩሳሌም በደል
1የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ!
“እስቲ በኢየሩሳሌም መንገዶች ሁሉ እየተዘዋወራችሁ እዩ!
ትክክለኛ ፍርድ የሚሰጥና እውነትን የሚሻ አንድ ሰው እንኳ ማግኘት ትችሉ እንደ ሆነ፥ እስቲ በየአደባባዩ ፈልጉ!
ይህ ቢሆን እኔ ለኢየሩሳሌም ምሕረት አደርግላታለሁ።
2እናንተ ‘ሕያው እግዚአብሔርን’ ብላችሁ በስሜ ትምላላችሁ፤
ነገር ግን የምትምሉት በሐሰት ነው።”
3እግዚአብሔር ሆይ ዐይኖችህ እውነትን የሚመለከቱ አይደሉምን?
አንተ ቀሠፍሃቸው፤ እነርሱ ግን ከምንም አልቈጠሩትም፤
አደቀቅሃቸው፤ እነርሱ ከስሕተታቸው መማር እምቢ አሉ፤
እልኸኝነትን አበዙ እንጂ፥ ከኃጢአታቸው መመለስ አልፈለጉም።
4ከዚህ በኋላ እኔ እንደዚህ አልኩ፥
“የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ሕግ ስላላወቁ፤
እነዚህ ድኾችና ማስተዋል የጐደላቸው ሰነፎች ናቸው፤
መንገዱንም አይከተሉም።
5እንግዲህ በሥልጣን ላይ ወዳሉት ገዢዎች ሄጄ፥ ከእነርሱ ጋር እነጋገራለሁ፤
በእርግጥ እነርሱ የእግዚአብሔርን መንገድና የአምላካቸውን ሕግ ያውቃሉ፤”
ነገር ግን እነርሱም ቢሆኑ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፀዋል፤
ለእርሱም መታዘዝ እምቢ ብለዋል።
6ሕዝቡ ብዙ ጊዜ ዐምፀው
እግዚአብሔርን ትተዋል፤
ስለዚህ ጠላቶቻቸው እንደ ዱር አንበሶች
ወይም እንደ በረሓ ተኲላዎች አደጋ ይጥሉባቸዋል፤
እነዚያም ጠላቶች በከተሞቹ ላይ ሸምቀው
ከዚያ የሚወጡትን ሰዎች ሁሉ እንደ ነብር ሆነው ይቦጫጭቁአቸዋል።
7እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ሕዝቤ እኔን ትተው ሐሰተኞች አማልክትን ያመልካሉ፤
ታዲያ እኔ የእነርሱን ኃጢአት ይቅር የምለው ለምንድን ነው?
እኔ ለሕዝቤ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ሁሉ በመስጠት እንዲጠግቡ አደረግሁ፤
እነርሱ ግን አመንዝሮች ሆኑ፤
ማደሪያቸውም በአመንዝሮች ቤት ሆነ።
8እንደ ተቀለቡ ፈረሶች በፍትወት ስለ ተቃጠሉ፥
እያንዳንዱ ከጓደኛው ሚስት ጋር መዳራት ይፈልጋል።
9ታዲያ ስለ ነዚህ ነገሮች ልቀጣቸው አይገባኝምን?
ይህንንስ የመሰለ እልኸኛ ሕዝብ ልበቀለው አይገባኝምን?
10የሕዝቤን የወይን ተክል ቈራርጠው የሚያበላሹ ጠላቶችን እልካለሁ፤
ነገር ግን ሥር መሠረታቸውን እንዲያጠፉ አላደርግም፤
ቅርንጫፎቹ የእኔ ባለመሆናቸው፥
ቈርጠው እንዲጥሉአቸው አዛለሁ።
11የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ ፈጽሞ ከድተውኛል፤
ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
እግዚአብሔር እስራኤልን መተዉ
12የእግዚአብሔር ሕዝብ በእግዚአብሔር ላይ ሐሰት በመናገር እንዲህ አሉ፦ “እግዚአብሔር ምንም አያደርገንም፤ ክፉ ነገርም አይመጣብንም፤ ጦርነትም ሆነ ራብ አያገኘንም፤ 13የእግዚአብሔር ቃል ያልተሰጣቸው ነቢያት የሚናገሩት ሁሉ ከነፋስ የሚቈጠር ስለ ሆነ የተናገሩት ሁሉ በእነርሱ ላይ ይደርስባቸዋል።” 14ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ኤርምያስ ሆይ! ሕዝቡ እንዲህ በመናገራቸው፥ ቃሌ በአፍህ እንደ እሳት ይሆናል፤ ሕዝቡም እንደ እንጨት ሆነው እሳቱ ይበላቸዋል።”
15የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እግዚአብሔር በእናንተ ላይ አደጋ የሚጥል ሕዝብ ከሩቅ ያመጣባችኋል፤ ይህም ሕዝብ ቋንቋውን የማታውቁት፥ ንግግሩንም የማታስተውሉት፥ ጥንታዊነት ያለው ብርቱ ሕዝብ ነው። 16ቀስተኞቻቸው ያለ ምሕረት የሚገድሉ ኀይለኞች ጦረኞች ናቸው። 17ሰብላችሁንና ምግባችሁን ሁሉ ጠራርገው ይበሉታል፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን ሁሉ ይገድላሉ፤ የበጎችና የከብት መንጋችሁን ሁሉ ያርዳሉ፤ የወይን ተክሎቻችሁንና የበለስ ዛፎቻችሁን ሁሉ ያጠፋሉ፤ ሠራዊታቸውም የምትተማመኑባቸውን የተመሸጉ ከተሞቻችሁን ሁሉ ያወድማሉ።
18እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ይህም ሁሉ ሲሆን በእነዚያ ቀኖች እንኳ ሕዝቤን ጨርሼ አላጠፋም፤ 19ኤርምያስ ሆይ! ሕዝቡ ‘እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ነገር ያደረሰብን ስለምድን ነው?’ ብለው በጠየቁህ ጊዜ ከእኔ ተለይተው በገዛ ምድራቸው ላይ ባዕዳን አማልክትን እንዳመለኩ ሁሉ፥ እነርሱም ራሳቸው የእነርሱ ባልሆነ አገር የባዕድ ሕዝብ አገልጋዮች መሆናቸው እንደማይቀር ንገራቸው።”
እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሰጠው ማስጠንቀቂያ
20እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ለያዕቆብ ዘሮች ለይሁዳም ሕዝብ ሁሉ ይህን ንገሩ፤ 21እናንተ ዐይን እያላችሁ የማታዩ፥ ጆሮም እያላችሁ የማትሰሙ፥ እናንተ ሞኞችና ሰነፎች የሆናችሁ ሕዝብ ሆይ! ይህን ስሙ፤ #ኢሳ. 6፥9-10፤ ሕዝ. 12፥2፤ ማር. 8፥18። 22እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ታዲያ ስለምን አታከብሩኝም? በፊቴስ ለምን አትንቀጠቀጡም፤ አሸዋን ውሃ አልፎት እንዳይሄድ ለዘለዓለሙ የባሕር ወሰን ያደረግኹት እኔ ነኝ፤ ባሕር የቱንም ያኽል ቢናወጥ፥ ማዕበል፥ ሞገዱም ቢያስገመግም፥ ወሰን የሆነውን የአሸዋ ግድብ አልፎ መሄድ አይችልም። #ኢዮብ 38፥8-11። 23እናንተ ግን እልኸኛና ዐመፀኛ ሕዝብ በመሆናችሁ፥ እኔን ትታችሁ ኰብልላችኋል። 24የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ በወቅቱ የምሰጣችሁ፥ የመከርንም ወራት በየዓመቱ የማመላልስላችሁ እኔ ነኝ፤ እናንተ ግን እኔን ማክበርን ተዋችሁ። 25በደላችሁ በረከትን አሳጣችሁ፤ የኃጢአታችሁም ብዛት መልካም ነገር እንዳታገኙ አደረገ።
26“በሕዝቤ መካከል የሚኖሩ ክፉ ሰዎች አሉ፤ እነርሱም ወፎችን በወጥመድ እንደሚይዝ ሰው ናቸው፤ ስለዚህ ሰዎችን ለማጥመድ መረባቸውን ዘርግተው ያደባሉ። 27አዳኝ ወፎችን ይዞ በወፎች ጎጆ እንደሚያሰፍር፥ እነርሱም ቤታቸውን ከብዝበዛ ባገኙት ሀብት ይሞላሉ፤ ብርቱዎችና ሀብታሞች የሆኑትም ስለዚህ ነው። 28እነርሱ እንደ ቅልብ ሰንጋ ወፍረዋል፤ ክፉ ሥራቸውም ገደብ የለሽ ሆኖአል፤ እናትና አባት የሌላቸውን ልጆች መብት አያስከብሩም፤ ለችግረኞችም ትክክለኛ ፍርድ አይፈርዱም።
29“ታዲያ እኔ እግዚአብሔር ስለዚህ ሁሉ ነገር ልቀጣቸው አይገባኝምን? እንደዚህ ያለውንስ ሕዝብ መበቀል አያስፈልገኝምን? 30አሠቃቂና አስደንጋጭ የሆነ ነገር በዚህች ምድር ላይ ተፈጽሞአል። 31ነቢያት ነን የሚሉት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ ካህናቱ በነቢያት ምክር ያስተዳድራሉ፤ ሕዝቡም ይህን ሁሉ አይቃወሙም፤ ታዲያ የዚህ ሁሉ ፍጻሜ በሚደርስበት ጊዜ ምን ይበጃችሁ ይሆን?”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 5: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997