የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 38

38
ኤርምያስ በደረቅ ጒድጓድ ውስጥ መጣሉ
1የማታን ልጅ ሰፋጥያ፥ የፓሽሑር ልጅ ገዳልያ፥ የሼሌምያ ልጅ የሁካልና የመልክያ ልጅ ፓሽሑር እግዚአብሔር የነገረኝን ቃል ሁሉ ለሕዝቡ ማስተማሬን ሰሙ፤ 2የተናገርኩትም ቃል ይህ ነበር፦ “በከተማይቱ የሚቀሩ ሁሉ በጦርነት፥ በረሀብ ወይም በወረርሽኝ ይሞታሉ፤ ወደ ባቢሎናውያን ሄዶ እጁን የሚሰጥ ግን አይገደልም፤ እርሱ ሕይወቱን ለማትረፍ ያመልጣል።” 3እንደገናም አስረዳቸው ዘንድ እግዚአብሔር የነገረኝ ቃል እንዲህ የሚል ነበር፦ “እኔ ይህችን ከተማ ለባቢሎናውያን ሠራዊት አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱም በቊጥጥራቸው ሥር ያደርጉአታል።”
4ከዚህ በኋላ መኳንንቱ ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉት፦ “ይህ ሰው ሞት ይገባዋል፤ በእንደዚህ ያለ አነጋገር እየተናገረ በከተማይቱ የቀሩት ወታደሮች ወኔ እንዳይኖራቸው አድርጎአል፤ በከተማይቱ ሰው ሁሉ ላይ የሚያደርገው ይኸው ነው፤ ሕዝቡን ለመጒዳት እንጂ ለመርዳት የሚፈልግ ሰው አይደለም።”
5ንጉሥ ሴዴቅያስም “እነሆ እርሱ በእጃችሁ ነው፤ የፈለጋችሁትን ብታደርጉበት ልከለክላችሁ አልችልም” ሲል መለሰላቸው። 6ስለዚህም እኔን ይዘው በቤተ መንግሥቱ አደባባይ በሚገኘው ወደ ንጉሥ ልጅ ወደ መልክያ የውሃ ጒድጓድ ውስጥ በገመድ ቊልቊል በመልቀቅ ወደ ታች አወረዱኝ፤ በጒድጓዱም ውስጥ ጭቃ እንጂ ውሃ አልነበረበትም፤ እኔም በጭቃው ውስጥ ሰመጥሁ።
7የሆነ ሆኖ አቤሜሌክ ተብሎ የሚጠራ በቤተ መንግሥቱ ያገለግል የነበረ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ እኔን ወደ ጒድጓድ ውስጥ እንደ ከተቱኝ ሰማ፤ በዚያን ጊዜ ንጉሡ በብንያም ቅጽር በር ሸንጎ ተቀምጦ ነበር፤ 8ስለዚህም አቤሜሌክ ወደ ንጉሡ ዘንድ ሄዶ እንዲህ አለው፦ 9“ንጉሥ ሆይ! እነዚህ ሰዎች ታላቅ በደል ፈጽመዋል፤ እነሆ ኤርምያስን ጒድጓድ ውስጥ ከተውታል፤ በከተማይቱ ምግብ ስለሌለ እዚያው በረሀብ መሞቱ ነው።” 10ከዚህም በኋላ ንጉሡ ኢትዮጵያዊውን አቤሜሌክን “ከዚህ ሠላሳ ሰዎች ይዘህ ሂድና ነቢዩ ኤርምያስን ከመሞቱ በፊት ከውሃው ጒድጓድ አውጡት” ሲል አዘዘው። 11ስለዚህም አቤሜሌክ ሰዎቹን አስከትሎ ሄደ፤ ወደ ቤተ መንግሥቱ ዕቃ ግምጃ ቤትም ገብቶ ወፍራም ጨርቅና አሮጌ ልብስ አገኘ፤ እርሱንም በገመድ አስሮ ሰደደልኝ። 12ገመዱ እንዳይጐዳኝ ጨርቁን በብብቴ ውስጥ እንዳስረው ነገረኝ፤ እኔም እንደዚሁ አደረግሁ፤ 13እነርሱም ከዚያ ጒድጓድ ውስጥ በዚያው ገመድ ስበው አወጡኝና በቤተ መንግሥቱ ግቢ በሚገኘው በዘብ ጠባቂዎች ክፍል ውስጥ ዘጉብኝ።
ሴዴቅያስ የኤርምያስን ምክር መጠየቁ
14ንጉሥ ሴዴቅያስ ልኮ ወደ እርሱ አስጠራኝና በቤተ መቅደሱ ሦስተኛ በር አጠገብ እንዲህ አለኝ፦ “እነሆ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ ነው፤ አንዳች ነገር ሳትደብቅ እንድትነግረኝ እፈልጋለሁ።”
15እኔም “እውነቱን ብነግርህ አትገድለኝምን? መቼም ብመክርህ ልታዳምጠኝ አትፈልግም” አልኩት።
16ስለዚህም ንጉሥ ሴዴቅያስ “እኔ አልገድልህም፤ ለሚገድሉህም ሰዎች አሳልፌ ላልሰጥህ ሕይወትን በሰጠን በሕያው እግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ!” በማለት በምሥጢር ቃል ገባልኝ።
17ከዚህም በኋላ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ስለ እርሱ ያለውን ሁሉ እንዲህ ብዬ ነገርኩት፦ “የባቢሎን ንጉሥ ለላካቸው ባለ ሥልጣኖች እጅህን ብትሰጥ ሕይወትህ ትተርፋለች፤ ይህችም ከተማ ከመቃጠል ትድናለች፤ አንተና ቤተሰብህም ሁሉ ከጥፋት ትድናላችሁ፤ 18ለእነርሱ እጅህን ባትሰጥ ግን ይህች ከተማ ለባቢሎናውያን ተላልፋ ትሰጣለች፤ እነርሱም ያቃጥሉአታል፤ አንተም ማምለጥ አትችልም።”
19ንጉሡም “እኔ እኮ የምፈራው ከእኛ ከድተው ወደ ባቢሎን የገቡትን የአገራችንን ሰዎች ነው፤ ለእነርሱ አሳልፈው የሰጡኝ እንደ ሆነ ያሠቃዩኛል” ሲል መለሰልኝ።
20እኔም እንዲህ አልኩት፦ “አይዞህ! ለእነርሱ ተላልፈህ አትሰጥም፤ እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል እንድትሰማ እለምንሃለሁ፤ ለአንተም መልካም ነገር ይሆንልሃል፤ ሕይወትህም ከጥፋት ትድናለች። 21እጅህን ለመስጠት እምቢ ብትል ግን እግዚአብሔር ለእኔ የገለጠልኝ ራእይ አለ፤ 22ይኸውም በይሁዳ ቤተ መንግሥት የቀሩት ሴቶች ሁሉ ወደ ባቢሎናውያን ባለ ሥልጣኖች ተወስደው በሚሄዱበት ጊዜ እንዲህ ይሉሃል፦
‘የቅርብ ወዳጆችህ አስተውሃል፤
እነርሱም በአንተ ላይ ሠልጥነውብሃል፤
አሁን ግን እግርህ ማጥ ውስጥ ስለ ገባ ጥለውህ ሄደዋል።’ ”
23በተጨማሪም እንዲህ አልኩት፦ “ሚስቶችህና ልጆችህ ሁሉ ወደ ባቢሎናውያን ይወሰዳሉ፤ አንተም በባቢሎን ንጉሥ ተይዘህ እስረኛ ትሆናለህ፤ ከእነርሱ እጅ ከቶ አታመልጥም፤ ይህችም ከተማ በእሳት ተቃጥላ ትወድማለች።”
24ሴዴቅያስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እንዳትሞት ይህን የተነጋገርነውን ነገር ማንም አይወቅ፤ 25ባለ ሥልጣኖቹ እኔ ከአንተ ጋር መነጋገሬን የሰሙ እንደ ሆነ መጥተው ምን እንደ ተባባልን ይጠይቁሃል፤ ሁሉን ነገር ባትነግራቸው እንገድልሃለን ብለው ያስፈራሩሃል፤ 26ስለዚህ ‘በዚያ እንዳልሞት እንደገና ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ’ እያልኩ ስለምነው ነበር ብለህ ንገራቸው።” 27ከዚያም በኋላ ባለ ሥልጣኖቹ መጥተው ጠየቁኝ፤ እኔም ልክ ንጉሡ ያለኝን ብቻ ነገርኳቸው፤ እኔና ንጉሡ ስንወያይ የሰማ ማንም ስላልነበረ ከዚያ በኋላ ጥያቄአቸውንም አቆሙ፤ 28እኔም ኢየሩሳሌም እስከ ተያዘችበት ጊዜ ድረስ በቤተ መንግሥቱ ግቢ በሚገኘው በዘብ ጠባቂዎች ክፍል ውስጥ ተዘግቶብኝ ቈየሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ