ትንቢተ ኤርምያስ 39
39
የኢየሩሳሌም በጠላት እጅ መውደቅ
1ሴዴቅያስ በይሁዳ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር መጥቶ በኢየሩሳሌም ላይ ከበባ አደረገ። 2ሴዴቅያስ በነገሠ በዐሥራ አንደኛው ዓመት፥ በአራተኛው ወር፥ በዘጠነኛው ቀን የከተማይቱ ቅጽሮች ተጣሱ።
3የኢየሩሳሌም ከተማ በተያዘች ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ባለ ሥልጣኖች መጥተው በመካከለኛው ቅጽር በር ስፍራ ስፍራቸውን ያዙ፤ ከእነርሱም መካከል፥ ኔርጋልሻሬጼር፥ ሣምጋር ነቦ፥ ሣርሰኪምና ሌላው ኔርጋልሻሬጼርና እንዲሁ ሌሎችም ይገኙባቸዋል።
4ንጉሥ ሴዴቅያስና ወታደሮቹ ሁሉ የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ በሌሊት ከከተማይቱ ወጥተው ለማምለጥ ሞከሩ፤ በቤተ መንግሥቱ የአትክልት ቦታ በኩል አድርገው ሁለቱን ቅጽሮች በሚያገናኘው መውጫ በር አቋርጠው ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ አቅጣጫ አመለጡ። 5ነገር ግን የባቢሎን ሠራዊት ከኋላቸው ተከትሎ በማሳደድ በኢያሪኮ አጠገብ በሚገኝ ሜዳ ላይ ደረሱበትና ሴዴቅያስን ማረኩት፤ ከዚህ በኋላ ወደ ንጉሥ ናቡከደነፆር አመጡት፤ በዚያን ጊዜ ንጉሥ ናቡከደነፆር በሐማት ግዛት ሪብላ ተብላ በምትጠራ ከተማ ውስጥ ነበር፤ ንጉሥ ናቡከደነፆርም እዚያው በሴዴቅያስ ላይ የፍርድ ውሳኔ አስተላለፈበት። 6ይኸውም በሪብላ ንጉሥ ሴዴቅያስ ዐይኑ እያየ ልጆቹ እንዲገደሉ ተደረገ፤ የይሁዳ ባለሥልጣኖችም ሁሉ ሞት ተፈረደባቸው። 7ከዚህም ሁሉ በኋላ የሴዴቅያስን ዐይኖች አወጣ፤ ወደ ባቢሎንም ለመውሰድ በነሐስ ሰንሰለት አሰረው። 8ባቢሎናውያንም የኢየሩሳሌምን ቅጽር ሁሉ አፈረሱ፤ ቤተ መንግሥቱንና የሕዝቡን መኖሪያ ቤት ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፤ 9በመጨረሻም የባቢሎን ንጉሥ የክብር ዘቡ አዛዥ ናቡዛርዳን በከተማ የቀሩትን ሕዝብና ቀደም ብለው ወደ እርሱ ከድተው የገቡትንም ሁሉ በአንድነት ሰብስቦ በእስረኛነት ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤ 10ምንም ሀብት ያልነበራቸውን ድኾች ብቻ በይሁዳ ምድር ተወ፤ ለእነርሱም የወይን ተክል ቦታዎችንና የሚያርሱት መሬት ሰጣቸው።
የኤርምያስ መፈታት
11ናቡከደነፆር የክብር ዘብ አዛዡን ናቡዛርዳንን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ 12“ሂድ፥ ኤርምያስን ፈልገህ አግኘውና ተገቢውን ጥንቃቄ አድርግለት፤ እርሱ የሚፈልገውን ሁሉ አድርግለት እንጂ በምንም ነገር እንዳትጐዳው።” 13ስለዚህም ናቡዛርዳን፥ ናቡሻዝባንና ኔርጋልሻሬጼር ተብለው ከሚጠሩትና ከሌሎችም የባቢሎን ባለ ሥልጣኖች ጋር ሆኖ፥ 14ታስሬበት ከነበረው በቤተ መንግሥቱ ግቢ ከሚገኘው ዘብ ጠባቂዎች ክፍል እንድወጣ አስደረገ፤ እኔም የሳፋን የልጅ ልጅ በሆነው በአሒቃም ልጅ በገዳልያ እጅ ወደ ቤቴ ተወሰድኩ፤ እኔም ከሕዝቤ ጋር በዚያ ኖርኩ።
ለአቤሜሌክ የተሰጠ ተስፋ
15በቤተ መንግሥቱ አደባባይ በእስራት ላይ ሳለሁ የእግዚአብሔር ቃል ወደኔ መጣ፤ 16የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ እንዲህ ብዬ እንድነግረው አዘዘኝ፦ “ልክ ከዚህ በፊት እንደ ተናገርኩት በዚህች ከተማ ላይ ብልጽግናን ሳይሆን ጥፋትን አመጣለሁ፤ በዚህችም ከተማ ሆነህ ይህ ሁሉ ሲፈጸም በዐይንህ ታያለህ፤ 17ነገር ግን በዚያን ቀን እኔ እግዚአብሔር አንተን አድንሃለሁ፤ ለምትፈራቸው ጠላቶችህ ተላልፈህ አትሰጥም፤ 18እኔ በሰላም ስለምጠብቅህ አትሞትም፤ በእኔ ስለ ታመንክ በሕይወት ትተርፋለህ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 39: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997