ትንቢተ ኤርምያስ 40

40
ከገዳልያ ጋር የኤርምያስ አኗኗር
1የክብር ዘብ አዛዡ ናቡዛርዳን እኔን በራማ ነጻ ከለቀቀኝ በኋላ እግዚአብሔር ተናገረኝ፤ ከዚያ በፊት እኔ እዚያ የተወሰድኩት አሁን ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ በመማረክ ታስረው ወደ ባቢሎን ከተወሰዱት ሕዝብ ሁሉ ጋር በሰንሰለት ታስሬ ነበር።
2የክብር ዘብ አዛዡ እኔን ገለል አድርጎ ለብቻ እንዲህ አለኝ፦ “አምላክህ እግዚአብሔር ይህችን ምድር እንደሚያጠፋት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር፤ 3አደርጋለሁ ብሎ ያቀደውን ሁሉ እነሆ አሁን ፈጽሞታል፤ ይህም ሁሉ የሆነው እናንተ ኃጢአት በመሥራታችሁና ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛችሁ ምክንያት ነው። 4እነሆ እኔ በእጅህ ላይ ያለውን ሰንሰለት ፈትቼ ነጻ አደርግሃለሁ፤ ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን ለመውረድ ብትፈልግ እንደ ወደድክ አድርግ፤ እኔም ለአንተ እንክብካቤ አደርግልሃለሁ፤ ወደዚያ ለመሄድ ካልፈለግህ ግን መቅረት ትችላለህ፤ እነሆ አገሪቱ በሞላ በፊትህ ስለ ሆነች ወደ መረጥከው ቦታ መሄድ ትችላለህ።”
5እኔም መልስ ሳልሰጥ ናቡዛርዳን “እንግዲያውስ የሳፋን የልጅ ልጅ ወደ ሆነው ወደ አሒቃም ልጅ ወደ ገዳልያ ዘንድ ሂድ፤ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ገዳልያን የይሁዳ ከተሞች ገዢ አድርጎ ሾሞታል፤ ስለዚህም ከእርሱ ጋር ሆነህ በሕዝቡ መካከል መኖር ትችላለህ፤ ወይም ይጠቅመኛል ብለህ ወደምታስበው ስፍራ ሁሉ መሄድ ትችላለህ።” ከዚያም በኋላ ልዩ ስጦታና ይዤው የምሄደውንም ስንቅ ሰጥቶ አሰናበተኝ። 6እኔም ከገዳልያ ጋር ለመኖር ወደ ምጽጳ ሄድኩ፤ እዚያም በምድሪቱ ላይ በቀሩት ሕዝብ መካከል አብሬ ኖርኩ።
ገዳልያ የይሁዳ ገዢ ሆኖ መሾሙ
(2ነገ. 25፥22-24)
7ከይሁዳ የጦር መኰንኖችና ወታደሮች ጥቂቶቹ ገና እጃቸውን አልሰጡም ነበር፤ እነርሱም የባቢሎን ንጉሥ ገዳልያን በሀገሪቱ ላይ ገዢ አድርጎ እንደ ሾመውና ወደ ባቢሎን ሳይወሰዱ በሀገሪቱ ለቀሩት ድኾች ኀላፊ ያደረገው መሆኑን ሰሙ፤ 8ስለዚህ የነታንያ ልጅ እስማኤል፥ የቃሬሐ ልጆች ዮሐናንና ዮናታን፥ የታንሑሜት ልጅ ሠራያ፥ ከነጦፋ የዔፋይ ልጆች፥ ከማዕካም የዛንያ ከሰዎቻቸው ሁሉ ጋር በምጽጳ ወደሚገኘው ወደ ገዳልያ መጡ። 9ገዳልያም እንዲህ ሲል ማለላቸው፦ “በእውነት ቃል ልግባላችሁ፤ ለባቢሎናውያን እጃችሁን ስለ መስጠት ምንም የሚያስፈራችሁ ነገር የለም፤ በዚህች ምድር ሰፍራችሁ ኑሮአችሁን መሥርቱ፤ ለባቢሎን ንጉሥ ገብሩ፤ ለእናንተም ሁሉ ነገር መልካም ይሆንላችኋል፤ #2ነገ. 25፥22-24። 10እኔም በዚህቹ በምጽጳ ከእናንተ ጋር ስለምኖር ባቢሎናውያን በሚመጡበት ጊዜ የእናንተ ወኪል ሆኜ እቆምላችኋለሁ፤ እናንተ ግን በምትኖሩባቸው መንደሮች ሁሉ የወይኑን ዘለላ፥ የወይራውን ዘይትና የሌላውን ተክል ፍሬ ሰብስባችሁ አከማቹ” 11ይህ በዚህ እንዳለ በሞአብ፥ በዐሞን፥ በኤዶምና በሌሎችም አገሮች የሚኖሩ እስራኤላውያን የባቢሎን ንጉሥ ጥቂት የአይሁድ ቅሪቶችን ማስቀረቱንና ለእነርሱም ገዳልያን ገዢ አድርጎ መሾሙን ሰሙ፤ 12ስለዚህም ተበታትነው የሚኖሩባቸውን ስፍራዎች ሁሉ ትተው ወደ ይሁዳ ተመለሱ፤ በምጽጳ ወደሚገኘው ወደ ገዳልያም መጥተው እጅግ ብዙ የሆነ የወይን ዘለላና የሌላውንም ተክል ፍሬ በመሰብሰብ አከማቹ።
የገዳልያ መገደል
(2ነገ. 25፥25-26)
13ከዚህ በኋላ ዮሐናንና ቀደም ብለው እጃቸውን ያልሰጡ የጦር አለቆች ሁሉ በምጽጳ ወደሚገኘው ወደ ገዳልያ መጥተው፥ 14“እስማኤል አንተን እንዲገድልህ የዐሞን ንጉሥ በዐሊስ የላከው መሆኑን አታውቅምን?” ብለው ጠየቁት። ገዳልያ ግን ይህን አላመነም፤ 15ከዚህም በኋላ ዮሐናን በምጽጳ በግል እንዲህ አለው፦ “ይህን ያደረገ ማን እንደ ሆነ ሳይታወቅ ሄጄ እስማኤልን ልግደለው፤ እንዴት እርሱ አንተን ሊገድልህ ይደፍራል? እርሱ ከገደለህ እኮ በዙሪያህ ለተሰበሰቡት አይሁድ መበታተን ምክንያት ይሆናል፤ በይሁዳ ምድር ከምርኮ በቀሩትም ሕዝብ ላይ ታላቅ ጥፋትን ያመጣል።”
16ገዳልያ ግን “ስለ እስማኤል የምትለው ሁሉ እውነት አይደለምና ከቶ ይህን አታድርግ” ሲል መለሰለት።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ