ትንቢተ ኤርምያስ 37
37
ሴዴቅያስ ለኤርምያስ ያቀረበው ጥያቄ
1የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የኢዮስያስን ልጅ ሴዴቅያስን የኢዮአቄም ልጅ በነበረው በኢኮንያን ምትክ በይሁዳ ላይ አነገሠው። #2ነገ. 24፥17፤ 2ዜ.መ. 36፥10። 2ሴዴቅያስም ሆነ መኳንንቱ ወይም ሕዝቡ እግዚአብሔር በነቢዩ በኤርምያስ አማካይነት ለተናገረው ቃል ታዛዦች አልሆኑም።
3ንጉሥ ሴዴቅያስ የሼሌምያን ልጅ የሁካልንና የማዕያን ልጅ ካህኑን ሶፎንያስን ወደ እኔ ወደ ኤርምያስ ልኮ “ስለ ሕዝባችን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ጸልይ” ብለው እንዲጠይቁኝ አደረገ። 4እኔም ገና ወደ እስር ቤት አልገባሁም ነበር፤ ከዚህም የተነሣ በሕዝቡ ፊት በነጻ እመላለስ ነበር። 5በዚያን ጊዜ የባቢሎን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከበበ፤ ነገር ግን የግብጽ ሠራዊት ድንበሩን አልፎ መምጣቱን በሰማ ጊዜ ወደ ኋላው አፈገፈገ።
6-7ከዚህ በኋላ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሴዴቅያስ በመልእክተኞቹ አማካይነት እንዲህ ብዬ እንድነግረው አዘዘኝ፦ “እነሆ አንተን ለመርዳት መጥቶ የነበረው የግብጽ ሠራዊት ወደ አገሩ ወደ ግብጽ በመመለስ ላይ ነው። 8ከዚያ በኋላ ባቢሎናውያን ተመልሰው ይመጣሉ፤ አደጋም ጥለው ከተማይቱን ይይዛሉ፤ በእሳትም ያቃጥሉአታል፤ 9እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ባቢሎናውያን ተመልሰው ይሄዳሉ’ ብላችሁ ራሳችሁን አታታሉ፤ እነርሱ ተመልሰው አይሄዱም። 10መላውን የባቢሎን ሠራዊት ድል ብትነሡ እንኳ ከእነርሱ ተርፈው በድንኳን ያረፉ ቊስለኞች እንደገና በማንሰራራት ተነሥተው ከተማይቱን በእሳት አቃጥለው ያወድሟታል።”
ኤርምያስ ተይዞ መታሰሩ
11የግብጽ ሠራዊት መቃረቡ እንደ ተሰማ የባቢሎን ሠራዊት ወደ ኋላ አፈግፍጎ ነበር፤ 12እኔም ከቤተሰቤ የሚደርሰኝን የርስት ክፍያ ለመቀበል ወደ ብንያም ግዛት ለመሄድ ከኢየሩሳሌም ተነሣሁ። 13ነገር ግን ከብንያም ቅጽር በር እንደ ደረስኩ የዘብ ጠባቂዎች አለቃ የሆነው ስሙ ዪሪያ ተብሎ የሚጠራ የሐናንያ የልጅ ልጅ የሆነው የሼሌምያ ልጅ “ከድተህ ወደ ባቢሎናውያን ልትሄድ ነው!” ብሎ አስቆመኝ።
14እኔም “አንተ እንደምትለው እኔ ከድቼ የምሄድ ሰው አይደለሁም!” ብዬ መለስኩለት፤ ዪሪያ ግን ሊያዳምጠኝ አልፈለገም፤ ይልቁንም አስሮ ወደ ባለ ሥልጣኖች ወሰደኝ፤ 15እነርሱም በብርቱ ተቈጥተው ካስደበደቡኝ በኋላ የእስር ቤት እንዲሆን አድርገውት ወደነበረው ወደ ጸሐፊው ወደ ዮናታን ቤት ውስጥ አስገብተው ዘጉብኝ፤ 16በዚያም ምድር ቤት ውስጥ በሚገኝ ክፍል ለብዙ ጊዜ ቈየሁ።
17ዘግየት ብሎም ንጉሥ ሴዴቅያስ መልእክተኛ ልኮ አስወሰደኝና በቤተ መንግሥቱ በግል ሲያነጋግረኝ “ከእግዚአብሔር የተነገረህ የትንቢት ቃል አለን?” ብሎ ጠየቀኝ።
“አዎ፥ አለ!” ብዬ ንግግሬን በመቀጠል “አንተ ለባቢሎን ንጉሥ ተላልፈህ ትሰጣለህ” አልኩት። 18ከዚያም በኋላ እንዲህ ብዬ ጠየቅሁት፦ “እስር ቤት ታስገባኝ ዘንድ በአንተ፥ በመኳንንትህና በዚህ ሕዝብ ላይ የፈጸምኩት ወንጀል ምንድነው? 19ለመሆኑ ‘የባቢሎን ንጉሥ በአንተም ሆነ በአገርህ ላይ አደጋ አይጥልም’ ብለው የነገሩህ ነቢያትህ አሁን የት አሉ? 20ስለዚህ ንጉሥ ሆይ! እንድታዳምጠኝና የምጠይቅህን እንድትፈጽምልኝ እለምንሃለሁ፤ ይኸውም እስር ቤት ወደ ሆነው ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ፤ ወደዚያ ከመለስከኝ በእርግጥ እሞታለሁ።”
21ስለዚህም ንጉሥ ሴዴቅያስ በቤተ መንግሥቱ ግቢ በሚገኘው በዘብ ጠባቂዎች ክፍል ውስጥ እንዲዘጋብኝ አዘዘ፤ እኔም በዚያ ቈየሁ፤ ዳቦ ከከተማይቱ ጨርሶ እስከ ጠፋም ድረስ ከዳቦ መጋገሪያዎች አንድ ዳቦ በየቀኑ ይሰጠኝ ነበር።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 37: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997