ትንቢተ ኤርምያስ 36
36
ባሮክ የተጠቀለለውን ብራና ማንበቡ
1የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በይሁዳ በነገሠ በአራተኛው ዓመት እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ #2ነገ. 24፥1፤ 2ዜ.መ. 36፥5-7፤ ዳን. 1፥1-2። 2“እኔ እግዚአብሔር አንተን ማናገር ከጀመርኩበት ማለትም ኢዮስያስ ከነገሠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስለ እስራኤል፥ ስለ ይሁዳ ሕዝብና ስለ ሌሎችም ሕዝቦች ሁሉ የነገርኩህን ቃል ሁሉ በብራና ጻፈው፤ 3የይሁዳ ሕዝብ በእነርሱ ላይ ላመጣ ያቀድኩትን ጥፋት በሚሰሙበት ጊዜ ምናልባት ከክፉ ሥራቸው ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም በደላቸውንና ኃጢአታቸውን ይቅር እላለሁ።”
4ስለዚህም የኔሪያን ልጅ ባሮክን ጠርቼ እግዚአብሔር የነገረኝን ቃል ሁሉ አንድ በአንድ እየነገርኩት በሚጠቀለል ብራና ጻፈው፤ 5ከዚህም በኋላ ለባሮክ የሚከተለውን መመሪያ ሰጠሁት፦ “ከእንግዲህ ወዲህ ወደ ቤተ መቅደስ ለመግባት አይፈቀድልኝም፤ 6ነገር ግን በሚቀጥለው ጊዜ ሕዝቡ በመጾም ላይ ሳሉ አንተ ወደዚያ እንድትሄድ እፈልጋለሁ፤ እግዚአብሔር ለእኔ የነገረኝን ቃል ሁሉ አንድ በአንድ እየነገርኩህ በሚጠቀለል ብራና ላይ የጻፍከውን ሁሉ ድምፅህን ከፍ አድርገህ አንብብላቸው፤ ከገጠር ከተሞቻቸው የመጡ የይሁዳ ሕዝብ ጭምር ሁሉም በሚሰሙበት ቦታ ይህን አድርግ፤ 7እግዚአብሔር አስፈሪ በሆነው ቊጣና መዓቱ ሕዝቡን እንደሚቀጣ የተናገረ በመሆኑ ምናልባት በመጸጸት ከክፉ ሥራቸው ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ይለምኑት ይሆናል።” 8ስለዚህም ባሮክ ልክ እኔ እንደ ነገርኩት በቤተ መቅደስ የእግዚአብሔርን ቃል አነበበ።
9የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር የኢየሩሳሌም ሕዝብና ከይሁዳ ከተሞች የመጡት ሕዝብ ከእግዚአብሔር ምሕረትን ለማግኘት የጾም ጊዜ አወጁ። 10ሕዝቡም ለማዳመጥ በሚችልበት ሁኔታ ባሮክ እኔ የነገርኩትን በብራና ጽፎት የነበረውን ቃል ሁሉ አነበበላቸው። በቤተ መቅደስ ውስጥ ይህን ያደረገው በጸሐፊው በሳፋን ልጅ በገማርያ ክፍል በኩል ዘልቆ ነበር፤ ክፍሉም የሚገኘው ወደ ቤተ መቅደስ ከሚያስገባው አዲስ የቅጽር በር አጠገብ በላይኛው አደባባይ በኩል አለፍ ብሎ ነበር።
በተጠቀለለ ብራና የተጻፈው ቃል ለባለሥልጣኖች እንደ ተነበበላቸው
11የሳፋን የልጅ ልጅ የነበረው የገማርያ ልጅ ሚክያስ እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል ሁሉ ባሮክ ከብራናው ሲያነብ ሰማ። 12እርሱም በቤተ መንግሥት ወደሚገኘው ባለሥልጣኖች ወደሚገኙበት ወደ ጸሐፊው ክፍል ሄደ፤ ጸሐፊው ኤሊሻማዕ፥ የሸማዕያ ልጅ ደላያ፥ የዓክቦር ልጅ ኤልናታን፥ የሳፋን ልጅ ገማርያ፥ የሐናንያ ልጅ ሴዴቅያስ ሌሎችም ባለ ሥልጣኖች እዚያ ተቀምጠው ነበር። 13ሚክያስም ባሮክ ለሕዝቡ ሲያነብላቸው የሰማውን ቃል ሁሉ ነገራቸው፤ 14ከዚህ በኋላ ባለ ሥልጣኖቹ ሁሉ ባሮክ ለሕዝቡ ያነበበውን የብራና ጥቅል ይዞ እንዲመጣ ይነግረው ዘንድ ይሁዲን ላኩ፤ (ይሁዲ የነታንያ ልጅ ሲሆን፥ ነታንያ የሸሌምያ ልጅ፥ ሸሌምያም የኩሺ ልጅ ነው፤) ባሮክም የብራናውን ጥቅል ይዞ ወደ እነርሱ መጣ፤ 15እነርሱም “በል ተቀመጥና ጽሑፉን አንብብልን!” አሉት፤ ባሮክም እንደታዘዘው አደረገ። 16አንብቦ ከጨረሰም በኋላ ከመደንገጣቸው የተነሣ እርስ በርሳቸው ተያይተው ባሮክን “ይህን ጉዳይ ለንጉሡ ማስታወቅ አለብን” አሉት፤ 17ከዚያ በኋላ “ይህን ነገር እንዴት እንደ ጻፍከው ንገረን፤ ይህን የጻፍከው ኤርምያስ በቃል እየነገረህ ነውን?” ሲሉ ጠየቁት።
18ባሮክም “በእርግጥ ቃሉን አንድ በአንድ የነገረኝ ኤርምያስ ነው፤ እኔም በዚህ ብራና ላይ በቀለም ጻፍኩት” አላቸው።
19እነርሱም “አንተና ኤርምያስ ወደ አንድ ስፍራ ሄዳችሁ መደበቅ አለባችሁ፤ ያላችሁበትንም ቦታ ማንም ሰው አይወቅ” አሉት።
ንጉሡ የብራናውን ጥቅል ማቃጠሉ
20ባለ ሥልጣኖቹም የብራናውን ጥቅል በጸሐፊው በኤሊሻማዕ ክፍል አኖሩት፤ ወደ ንጉሥም አደባባይ ሄደው የሆነውን ነገር ሁሉ አሳወቁት፤ 21ንጉሡም የብራናውን ጥቅል ያመጣለት ዘንድ ይሁዲን አዘዘው፤ እርሱም ብራናውን ከኤሊሻማ ክፍል ወስዶ ለንጉሡና በዙሪያው ቆመው ለነበሩት ባለ ሥልጣኖች ሁሉ አነበበላቸው። 22በዘጠነኛው ወር ወራቱም ክረምት ስለ ነበረ ንጉሡ የክረምትን ወራት በሚያሳልፍበት ቤተ መንግሥት እሳት በሚነድበት ምድጃ ፊት ለፊት ተቀምጦ ነበር፤ 23ይሁዲም ሦስት ወይም አራት ዐምድ ያኽል አንብቦ በጨረሰ ቊጥር ንጉሡ የተነበበለትን ብራና በመቊረጫ ቈራርጦ እሳት ውስጥ ይጥለው ነበር፤ በዚህም ዐይነት የብራናውን ጥቅል በሙሉ አቃጠለው። 24ንጉሡም ሆነ መኳንንቱ ይህን ሁሉ ከሰሙ በኋላ ምንም ዐይነት ፍርሀት አልተሰማቸውም ወይም በሐዘን ልብሳቸውን አልቀደዱም። 25ኤልናታን፥ ደላያና ገማርያ ንጉሡ የብራናውን ጥቅል እንዳያቃጥል ቢለምኑትም እንኳ ሊያዳምጣቸው አልፈለገም። 26ከዚህ በኋላ ልዑሉን ይረሕምኤልን ከዐዝርኤል ልጅ ሠራያና ከዐብድኤል ልጅ ከሸሌምያ ጋር ሆኖ እኔንና ባሮክን እንዲይዝ አዘዘው፤ እኛ ግን እግዚአብሔር ሰወረን።
ኤርምያስ እንደገና የጻፈው ቃል
27-28እኔ እየነገርኩት ባሮክ የጻፈውን የብራና ጥቅል ንጉሥ ኢዮአቄም ካቃጠለው በኋላ ሌላ የሚጠቀለል ብራና ወስጄ የቀድሞውን ቃል እንደገና እንድጽፈው እግዚአብሔር አዘዘኝ። 29ለንጉሡም እንዲህ ብዬ እንድነግረው አዘዘኝ፦ “እነሆ አንተ የብራናውን ጥቅል አቃጥለሃል፤ ‘የባቢሎን ንጉሥ መጥቶ ይህችን ምድርና በእርስዋ የሚኖሩትን ሕዝብ፥ እንዲሁም እንስሶችን ሁሉ እንደሚያጠፋ ትንቢት የተናገርከው ስለምንድን ነው?’ ብለህ ኤርምያስን ጠይቀኸዋል፤ 30ንጉሥ ኢዮአቄም ሆይ! እነሆ እግዚአብሔር ስለ አንተ የሚለው ይህ ነው፦ ‘ከዘርህ በዳዊት መንግሥት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ከቶ አይኖርም፤ ሬሳህም የትም ተጥሎ ለቀን ፀሐይ ሐሩርና ለሌሊት ቊር የተጋለጠ ይሆናል፤ 31ስለ ፈጸማችሁት ኃጢአት አንተን ራስህን፥ ልጆችህንና መኳንንትህን ሁሉ እቀጣለሁ። አንተም ሆንክ የኢየሩሳሌምና የይሁዳ ሕዝብ የሰጠኋችሁን ማስጠንቀቂያ ከምንም አልቈጠራችሁትም፤ ከዚህም የተነሣ አስቀድሞ ላመጣው ያቀድኩትን መቅሠፍት ሁሉ በእናንተ ላይ አመጣባችኋለሁ።’ ”
32ስለዚህ ሌላ የብራና ጥቅል ወስጄ ለጸሐፊዬ ለባሮክ ሰጠሁት፤ እርሱም በቃል የነገርኩትን ሁሉ ጻፈበት፤ በዚህ ዐይነት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም ባቃጠለው ብራና ተጽፎ የነበረውን ጻፈ፤ ሌሎችም ብዙ ተመሳሳይ ቃሎች ተጨምረውበታል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 36: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997