የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 35

35
ኤርምያስና ሬካባውያን
1የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በይሁዳ በነገሠ ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ #2ነገ. 23፥36—24፥6፤ 2ዜ.መ. 36፥5-7። 2“ወደ ሬካባውያን ቤተሰብ አባሎች ሂድና አነጋግራቸው፤ ከዚያም በኋላ በቤተ መቅደስ ካሉት ክፍሎች ወደ አንዱ አስገብተህ የሚጠጡት የወይን ጠጅ አቅርብላቸው፤” 3ስለዚህ እኔ የኤርምያስን ልጅ የአዛንያን፥ የሐባዲንያን ልጅ፥ ወንድሞቹንና ልጆቹን ሁሉ የሬካባውያንን ቤተሰብ በሙሉ ወሰድኩ። 4እነርሱንም ወደ ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ሰው የአግዳልያ ልጅ የሐናን ልጆች ወደሚኖሩበት ክፍል አመጣኋቸው፤ ክፍሉም ከባለ ሥልጣኖቹ ክፍል ቀጥሎ ከበር ጠባቂው ከሸሉም ልጅ ከማዕሴያ ክፍል በላይ ነው። 5በወይን ጠጅ የተሞሉ ማንቈርቈርያና ጽዋዎችን በሬካባውያን ፊት አስቀምጬ “እስቲ የወይን ጠጅ ጠጡ” አልኳቸው።
6እነርሱ ግን እንዲህ ሲሉ መለሱልኝ፦ “እኛ የወይን ጠጅ አንጠጣም፤ የሬካብ ልጅ የነበረው አባታችን ኢዮናዳብ እኛም ሆንን ዘሮቻችን ሁሉ ምንም ዐይነት የወይን ጠጅ እንዳንጠጣ አዞናል። 7እንዲሁም መኖሪያ ቤት መሥራት፥ እርሻ ማረስ፥ የወይን ተክል ቦታዎችን ይዘን መንከባከብ እንደማይገባን ነግሮናል፤ እንደ እንግዶች በዚህች ምድር ለብዙ ጊዜ መቀመጥ እንችል ዘንድ በድንኳን መኖር እንደሚገባን አዞናል። 8ኢዮናዳብ የሰጠንን ትምህርት ሁሉ ተቀብለናል፤ እኛም ሆንን ሚስቶቻችን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም የወይን ጠጅ አንጠጣም፤ 9መኖሪያ ቤት ሳንሠራ በድንኳን እንኖራለን፤ የወይን ተክል ቦታዎችና የእህል እርሻዎችም አይኖሩንም፤ 10በድንኳን ኖረናል፤ የቀድሞ አባታችን ኢዮናዳብ ላዘዘን ቃል ሁሉ በሙሉ ልብ ታዛዦች ሆነናል። 11ነገር ግን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር መጥቶ አገሪቱን በወረረ ጊዜ ከባቢሎናውያንና ከሶርያውያን ሠራዊት ሸሽተን እናመልጥ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ለመምጣት ወስነናል፤ አሁንም በኢየሩሳሌም የምንኖረው ስለዚህ ነው።”
12-13ከዚህም በኋላ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም ሕዝብ እንድሄድና እንዲህ ብዬ እንዳዛቸው ነገረኝ፦ “ትምህርትን ተቀብላችሁ ለቃሌ ለመታዘዝ አትችሉምን? 14የኢዮናዳብ ዘሮች እንኳ የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ አባታቸው ያዘዛቸውን ቃል በመጠበቅ እነሆ እስከ አሁን ድረስ ምንም ዐይነት የወይን ጠጅ አይቀምሱም፤ እኔ ግን ሁልጊዜ በመደጋገም እነግራችኋለሁ፤ እናንተ ልትታዘዙኝ አልፈለጋችሁም፤ 15አገልጋዮቼ የሆኑትን ነቢያትን ወደ እናንተ ደጋግሜ ልኬአለሁ፤ እነርሱም ከክፉ ሥራችሁ ተመልሳችሁ ቅን የሆነውን ነገር እንድትሠሩ ነግረዋችኋል፤ ለባዕዳን አማልክት እንዳትሰግዱና የእነርሱም አገልጋዮች እንዳትሆኑ አስጠንቅቀዋችኋል፤ ለእናንተና ለቀድሞ አባቶቻችሁ በሰጠኋችሁ ምድር መኖር ትችሉ ዘንድ ይህን ሁሉ አዘዝኳችሁ፤ እናንተ ግን እኔን ለማዳመጥም ሆነ ለምነግራችሁ ቃል ትኲረት ልትሰጡት አልፈለጋችሁም። 16የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብ ዘሮች የቀድሞ አባታቸው ያዘዛቸውን ሁሉ ፈጽመዋል፤ እናንተ ሕዝቤ ግን አልታዘዛችሁልኝም። 17ስለዚህም እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር አደርስባችኋለሁ ብዬ የተናገርኩትን ጥፋት ሁሉ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች በሆናችሁት ሁሉ ላይ አመጣባችኋለሁ፤ ይህንንም የማደርገው ስነግራችሁ ባለማዳመጣችሁና ስጠራችሁም መልስ ባለመስጠታችሁ ነው።”
18ከዚህ በኋላ እኔ ኤርምያስ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ለሬካባውያን ወገን የተናገረውን ቃል እንዲህ ብዬ ገለጥኩላቸው፦ “የቀድሞ አባታችሁ ኢዮናዳብ የሰጣችሁን ትእዛዝ ሁሉ ፈጽማችኋል፤ ትምህርቱንም ሁሉ ተከትላችኋል፤ ያዘዛችሁንም ሁሉ አድርጋችኋል፤ 19ስለዚህም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ከዘሩ ምንጊዜም እኔን የሚያገለግል ሰው አይጠፋም።’ ”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ